የተምች ወረርሽኝ በ111 ሺሕ ሄክታር የእርሻና የከብት ግጦሽ መሬት ላይ መከሰቱ ተገለጸ

0
1263

የተምች ወረርሽኝ በሰባት ክልሎች ከ111 ሺሕ ሄክታር በላይ በእርሻና በከብት ግጦሽ መሬት ላይ መከሰቱን ግብርና ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር በላይነህ ንጉሤ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ በሰባት ክልሎች ማለትም በኦሮሚያ ክልል፣ በደቡብ ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጋምቤላ ክልል፣ በአማራ ክልል፣ በሲዳማ ክልል እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተምች ወረርሽኝ መከሰቱን ተናግረዋል።

በተጠቀሱት ክልሎች በ25 ዞኖች፣ በ113 ወረዳዎች የተምቹ ወረርሽኝ እንደተከሰተ እና በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ የግብርና ሚኒስቴር በቴርሞ ሜትር አማካኝነት ቀድሞ መተንበይ የተቻለ ሲሆን፣ የተምቹ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ የፀረ ተባይ ኬሚካሎችን፣ የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎችን እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ወደ ክልሎች ቀድሞ መላክ መቻሉን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

በሰባቱ ክልሎች 111 ሺሕ 361 ሄክታር መሬት ውስጥ 38 ሺሕ 387 ሄክታር መሬት ላይ የፀረ ተባይ የኬሚካል ርጭት፣ 22 ሺሕ ሄክታር የሚጠጋው እንዲሁም በባህላዊ መንገድ በተሠራው ሥራ በአጠቃላይ ከ60 ሺሕ 899 ሄክታር መሬት ላይ ተባዩን ማጥፋት ተችሏል። ቢሆንም 50 ሺሕ ሄክታር መሬት የሚጠጋው የተምች ወረርሽኝ ግን በሰብሎችም ሆነ በግጦሽ መሬት ላይ ጉዳት አያደርስም ተብሎ ርጭቱ አለመካሄዱን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

በቀጣይ የክረምት ወራት መሆኑን ተከትሎ የንፋሱ አቅጣጫ ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሚያጋድልበት አዝማሚያ እንደመኖሩ መጠን፣ የተምቹ ወረርሽኝ ወደ አፋር ክልል፣ ምሥራቅ ሃረርጌ ዞን እንዲሁም ወደ አማራ ክልል በስፋት የሚስፋፋበት እድል እንዳለው ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የተምቹ ወረርሽኝ ወደ ሌሎች ክልሎች እንዳይስፋፋ መንግሥትም ሆነ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ርብርብ እንዲያደርጉ ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።

በግብርና ሚኒስቴር እና በአንድ ክልል በኩል ብቻ የተምቹን ወረርሽኝ መቆጣጠር የማይቻል በመሆኑ፣ ሁሉም ክልሎች በጥምረት ወይም በመተባበር ወደተለያዩ ቦታዎች እንዳይስፋፋ እንዲሠሩ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

በተጨማሪ፣ የፀረ ተባይ ኬሚካል የሚረጭበት አካባቢ እና ኅብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በመኖሩ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በእርሻ እና በግጦሽ መሬት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ፣ በባህላዊ መንገድ የማስወገድ ሥራ እንዲሠሩ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የተምቹ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በሰብሎች እና በግጦሽ መሬቶች ላይ ያደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ግብረ ኃይል፣ ግብርና ሚኒስቴር ሊልክ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ እና ጥናቱ ሲጠናቀቅ ሙሉ የሪፖርት መረጃውን እንደሚያሳውቁ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በተጨማሪ የፀረ ተባይ የኬሚካል ርጭቱ፣ አካባቢ እና ኅብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በመኖሩ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በእርሻ እና በግጦሽ መሬት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በባህላዊ መንገድ የማስወገድ ሥራ እንዲሠሩ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ተከስቶ የነበረውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከተደረገው ርብርብ አንፃር፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መነሻውን አድርጎ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የተስፋፋውን የተምች ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የተሠራው ሥራ ከፍተኛ ነው ያለው ሚኒስትሩ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here