መነሻ ገጽዜናወፍ በረር ዜናየቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳምን ለማነፅ የሚያስችል የ3 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፉ ተደረገ

የቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳምን ለማነፅ የሚያስችል የ3 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፉ ተደረገ

በሰሜን ጎንደር ዞን በበየዳ ወረዳ የሚገኘውን ደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ለመገንባት የሚያስችል የ3 ቢሊየን ብር ፕሮጀክት ባሳለፍነው ዕረቡ ሰኔ 8 ቀን 2014 ይፉ ተደርጓል።

ይህንን በመጀመሪያው የዜማና ድርሰት ሊቅ፣ የጥበብ እና የዕውቀት ባለቤት ቅዱስ ያሬድ ሥም የሚታነፀውን ግዙፍ ገዳም ፕሮጀክት ይፋ ያደረገው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና በተሰጠው የደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ህንፃ አሰሪ ኮሚቴ ሲሆን፤ ኮሚቴው ፕሮጀክቱን ከ5 እስከ 7 ዓመት በሚሆን ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙን አስታውቋል።

ኮሚቴው ፕሮጀክቱን ይፋ ባደረገበት መድረክ ላይ እንደተገለፀው፤ በፕሮጀክቱ የቅዱስ ያሬድን የጥበብ ሥራዎች የሚመጥን ግዙፍ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም አምስቱን ጸዋትወ ዜማና ድርሰቶቹን ጨምሮ አጠቃላይ ሥራዎቹን መሠረት ያደረገ የታሪክ፣ የፍልስፍና እና የሥነ ውበት ጥናትና ምርምር ማካሄጃ የልህቀት ማዕከል ተካተውበታል።

በተጨማሪም ኹሉንም የዜማ ትምህርቶች ያካተተ የአብነት ትምህርት ቤት፣ ሙዚየም፣ ቤተ-መጻህፍትና ዓመታዊ አገራዊ የማህሌት ትዕይንት የሚቀርብበት መድረክም በፕሮጀክቱ መካተታቸውን ኮሚቴው ጨምሮ ገልጿል።

የደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳምን ለመገንባትም ከኹለት ወራት በላይ በፈጀ የዲዛይን መረጣ ውድድር መደረጉን የተናገሩት የኮሚቴው ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አርክቴክት ተስፋ ማርያም ተሾመ፤ በመጨረሻም “ስካይ ላይን አርክቴክት ኢንጂነሪንግ” የተሰኘ ድርጅት ያቀረበው ዲዣይን የቤተክርስቲያኒቷን ትውፊት የያዘ፣ ታሪክን፣ ጥንታዊነትን እንዲሁም አካባቢያዊነትን ያካተተ ሆኖ በመገኘቱ ገዳሙን የማነፁን ሥራ እንዲያከናውን መመረጡን አስረድተዋል።

አርክቴክት ተስፋ ማርያም አክለውም፤ ፕሮጀክቱ በ6 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚያርፍ ገልፀው፤ የግንባታ ቦታውም ቅዱስ ያሬድ በተሰወረበት በሰሜን ጎንደር አገረ ስብከት በየዳ ወረዳ እንደሆነና መሬቱም ከአካባቢው ማኅበረሰብ በነፃ የተበረከተ መሆኑ ተናግረዋል።
ይህ ታላቅ ገዳም የሚገነባበት ሥፍራ የራስ ዳሽን ተራራ እና የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ አቅራቢያ መሆኑን ያነሱት አርክቴክት ተስፋ ማርያም፤ ይህም የቱሪስት ፍሰትን ከመጨመር አንፃር ከፍተኛ የሆነ አገራዊ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

ይህን ገዳም ለመገንባት ከ3 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የተገለፀ ሲሆን፤ ለዚህም የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያና አሰሪ ኮሚቴው ወደ ብሄራዊ ኮሚቴ የሚቀየርበት ይፉዊ መርሃ ግብር የፊታችን ሰኔ 19 ቀን 2014 በኤሊያና ሆቴል እንደሚካሄድ በመድረኩ ተነግሯል።

ቅዱስ ያሬድ ሚያዚያ 5 ቀን 505 በአክሱም ከተማ የተወለደ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ዜማን በፅሁፍ ያቀናበረ፣ ባለቅኔ ከመሆኑም ባሻገር ድጓ፣ ጾመድጓ፣ ዝማሬ ምሥዋዕት እና ምዕራፍ የተሰኙ አምስት የዜማ መጻሕፍት የደረሰ የዘመኑ ታላቅ ሊቅ እንደነበር ይታወቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 189 ሰኔ 11 2014

ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች