ሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ በትላንትናው እለት ኳስ ለማወጣት ወደ ወንዝ የገቡ ኹለት ታዳጊዎች ህይወታቸው ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስር በተለምዶ ቀይ አፈር በሚባለው አካባቢ አደጋው ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ መድረሱ ነው የተነገረው።
የዘጠኝ እና የአስራ አራት ዓመት እድሜ ያላቸው ታዳጊዎቹ ኳስ እየተጫወቱ ሳለ ኳሱ ወደ ወንዝ ሲገባባቸው ለማውጣት በሚያርጉት ጥረት በውሃው ታፍነው መወሰዳቸውን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል።
አንዱ ታዳጊ ወዲያው ህይወት ሲያልፍ ኹለተኛው ደግሞ ሆስፒታል ከገባ በኃላ ህይወቱ ማለፉን ተነግሯል፡፡
ምክትል ኢንስፔክተር ማርቆስ የተያዘው የክረምት ወቅት በርካታ ቦታዎች ለጎርፍ ተጋላጭ መሆናቸውን እና የወንዞች ዳርቻ ጥንቃቄ ካልተደረገባቸው በርካታ ችግር ሊፈጥሩ እንሚችል በመግለፅ፤ ወላጆች እና ማህበረሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡




