በኢትዮጵያ የግንባታው ዘርፍ ለብዙዎች የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር የአንድ አገር ኢኮኖሚን ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው እሙን ነው።
ነገር ግን፣ ዘርፉ በተለያዩ መሰናክሎች ከተፈተነ በአገር ምጣኔ ሀብት ላይ ተፅዕኖ ከማሳደር ጎን ለጎን፣ በዚሁ የሥራ መስክ ኑሯቸውን የሚመሩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ተጎጂ የሚሆኑበት እድል የጎላ ይሆናል።
በኢትዮጵያም የግንባታው ዘርፍ በተለያዩ ተደራራቢ ችግሮች ሳቢያ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን በርካቶች ናቸው ሲያነሱ የሚደመጡት። ለዚህ ደግሞ የግንባታ ዕቃዎች ወይም ቁሳቁሶች የመሸጫ ዋጋ በየወቅቱ ጭማሬ ማሳየቱ ዋናው ምክንያት እንደሆነ እና ሁኔታውም የሚወሰነው በዋናነት ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሬ ከዓለም ገበያ የምትሸምታቸው ግብዓቶች ዋጋ መናር ነው።
ከሌሎች የገበያ ምርቶች በተለየ የሲሚንቶ ምርት፣ የብረታ ብረት፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች እና ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ተመን ጭማሬ ማሳየት ለጦሱ ተጠቃሽ ነው ሲሉ ነጋዴዎች፣ ኮንትራክተሮች ወይም የግንባታ ሥራ ተቋራጭ ድርጅቶች ተናግረዋል።
በግንባታ ዘርፍ ላይ በኮንትራክተር ሥራ ላይ የተሰማሩት ዳዊት ኃይለማርያም እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ በአሁን ወቅት የመንገድ፣ የሕንፃ እና ሌሎች የግንባታ ዘርፎችም ጭምር እየተቀዛቀዙ መምጣታቸው የማይሸሸግ እና መታዘብ የሚቻል ሀቅ ነው።
ለዚህ ደግሞ በተለይ ካለፈው ታህሳስ ወር 2014 ወዲህ ለዘርፉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ላይ ማለትም በሲሚንቶ ምርት፣ በብረታ ብረት፣ በቆርቆሮ እና በሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችም ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ መስተዋሉ ችግር ፈጥሯል። የዋጋ ግሽበቱና የእቃዎች በተፈለገው መጠን አለመገኘት ለዘርፉ መቀዛቀዝ እና የተጀመሩ ግንባታዎችንም በሚፈለገው መጠን ለማስኬድ የሚያግድ እንቅፋት መሆኑን ይናገራሉ።
የሕንፃና የመንገድ ግንባታ በሚካሄዱበት ወቅት ለብዙ ሰዎች የሥራ እድሎች ይፈጠሩ የነበረ ቢሆንም፣ ዘርፉ መቀዛቀዙን ተከትሎ በዚያው ልክ የሥራ እድሉም እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል።
ዳዊት አክለውም፣ የግንባታው ሂደት በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ በዘርፉ ተሰማርተው የሚሠሩ ባለሙያዎችም ወደ ሌላ መስክ ሊያመሩ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው ይላሉ። መንግሥት ዘርፉ ወደ ነበረበት እንዲመለስ የግንባታ ቁሳቁስ መሸጫ ዋጋ ማረጋጋት እና የውጭ ምንዛሬውን ማረጋጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
በተጨማሪም በሁሉም አካባቢ ተንቀሳቅሶ መሥራት እንዲቻል ሰላምን ለማስፈን የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን በማነሳሳት እና ችግሮች ላይ አፅንዖት በመስጠት መፍትሄ ለማምጣት መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ለግንባታ ግብዓትነት አስፈላጊ ከሆኑ ቁሳቁሶች ውስጥ ሲሚንቶ ወሳኙና በጣም አስፈላጊው ግብዓት መሆኑ ይነገራል። ሌላው በጣም አስፈላጊ የሆነው ብረት ከውጪም በግዢ እየገባ ፍላጎትን የሚያሟላ ሲሆን፣ ሲሚንቶ ግን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ በአገር ውስጥ ምርት ነው ፍላጎቱ የሚሸፈነው። ሆኖም ግን፣ በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ካላቸው አጠቃላይ የማምረት አቅም 48 በመቶውን ብቻ እያመረቱ እንደሚገኙ መረጃዎች ያስረዳሉ።
አዲስ ማለዳ የሲሚንቶን የገበያ ሁኔታ ለማወቅ በአዲስ አበባ ከተማ ተዟዙራ ባደረገችው የገበያ ዳሰሳ፣ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከ1 ሺሕ 600 እስከ 1 ሺሕ 800 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝ አረጋግጣለች።
በሲሚንቶ ገበያ ላይ የተፈጠረው ቀውስ ይበልጥ እንዲባባስ ያደረገው ግን፣ በገበያው ላይ የሚታየው ከፍተኛ የምርት እጥረት እንደሆነ የንግድ ሱቅ ባለቤቶች ሲያነሱ ይደመጣል። ከእነዚህም የንግድ ሱቅ ባለቤቶች መካከል ዘይነባ አሊ ይገኙበታል።
ዘይነባ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በስፋት ምርቶችን ማምረት አለመቻላቸው፣ የሚመረቱ ምርቶችም በየወቅቱ መሰራጨት አለመቻላቸው ለአከፋፋዮችም ሆነ ለቸርቻሪ ነጋዴዎች ተፅእኖ እንደሚያሳድር ይናገራሉ።
በተጨማሪ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የተለያዩ የማሽን እና ሌሎች የመለዋወጫ እቃዎችን ከውጪ አገራት ገዝተው ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ ችግር መኖሩ የራሱ ተፅእኖ እንዳለው በመግለጽ፣ ይህ ሁኔታ ፋብሪካዎች በሚፈለገው መጠን ምርቶችን አምርተው ለማሰራጨት የሚቸገሩበትን ሂደት ይፈጥራል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ መንግሥት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የምርት መጠናቸውን እንዲጨምሩ በመደገፍ እና የውጭ ምንዛሬውን በማረጋጋት ረገድ በስፋ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ 20 ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች መካከል፣ በአሁኑ ወቅት በበቂ ሁኔታ ገበያው ውስጥ ምርት እያቀረቡ ያሉት የዳንጎቴ ሲሚንቶ እና ኢትዮ ሴሜንት ብቻ መሆናቸው ይነገራል።
የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ፍትሃዊ የሲሚንቶ ምርት ሥርጭት እንዲኖር እና ተገልጋዮች ያለምንም አድልዎ ምርቱን እንዲያገኙ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል። ይህንንም ለማሳካት ኹለት ጊዜ ከሲሚንቶ አምራቾች እና አከፋፋዮች ጋር እንደተወያየ ማሳወቁ አይዘነጋም።
ከብዙ ውይይቶች በኋላ የሲሚንቶ ዋጋ በነጻ ገበያ እንዲመራ የተወሰነ መሆኑ እና በሕዝቡ ላይ አላስፈላጊ ጫና በሚፈጠርበት በማንኛውም ሰዓት ሚኒስቴሩ ጣልቃ ገብቶ ገበያውን የማረጋጋት ሥልጣን እንዳለውም ተናግሯል።
ሌላው መሠረታዊ የግንባታ ግብዓት ብረታ ብረት ሲሆን፣ ካለፈው መስከረም ወር 2014 ጀምሮ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ ማሳየቱን እና በእያንዳንዱ የብረት ዝርያ ውስጥ ከ2 መቶ ብር በላይ ጭማሬ ማሳየቱን የተናገሩት በግንባታና ቁሳቁስ ሽያጭ ላይ የሚገኙት ጌታቸው ዓለሙ ናቸው።
ከሌሎች አገራት የሚገቡ ምርቶች እንዳሉ ሁሉ በኢትዮጵያ የሚመረቱ የብረታ ብረት ዝርያዎች መኖራቸውንም ጌታቸው ጠቁመዋል።
አክለውም ከአንድ ዓመት በላይ በሰሜኑ ክፍል በነበረው ጦርነት ሳቢያ እና ከውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ብረታ ብረት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች አቅማቸው ተዳክሟል ብለዋል።
ከእነዚህ ችግሮች ጋር ተደማምረው የብረታ ብረት የመሸጫ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ በግንባታው ዘርፍ ላይ ራሱን የቻለ ተፅዕኖ ማሳደሩንም አልሸሸጉም።
ጌታቸው አክለውም፣ መንግሥት ዋጋውን ከማረጋጋት ጎን ለጎን የውጭ ምንዛሬን በማረጋጋት በኢትዮጵያ ብረታ ብረት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ በማገዝ እና ጥያቄዎቻቸውን በመፍታት አብሯቸው ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ብረትን ለማምረት የሚያስችላትን ጥሬ እቃ ሙሉ ለሙሉ ከዩክሬን እንደምታስገባ፣ የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ እና ኢንዱስትሪ ምርምር እና ልማት ማዕከል ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል። ከዩክሬኑ ጦርነት በፊትም ቢሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ትልቅ ችግር እንደነበርም በዛው ተጠቅሷል።
ዘርፉ ያለበትን የውጪ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች እርስ በእርስ እንዲተጋገዙ የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ከሦስት ሳምንት በፊት ማእከሉ የተናገረ ሲሆን፣ በጥሬ እቃ ምክንያት ምርታማታነቸው ለቀነሰባቸው አምራቾች እንዲሁ፣ አንዱን ጥሬ እቃ ለአንዱ ግብዓት አድርገው እንዲጠቀሙ መስመሮች ተዘርግተዋል ተብሏል።
የሕንፃ መሣሪያዎች የመሸጫ ዋጋ በመጨመሩ በመዲናዋ የሚካሄዱ ግንባታዎች መቀዛቀዛቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው የተናገረው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሙሉጌታ ሊክዲ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ ከባለፈው ዓመት አንፃር ሲታይ፣ በሲሚንቶ ምርቶች፣ በፌሮ ብረቶች፣ በቆርቆሮ እና በሌሎች በሕንፃ መሣሪያዎች ወይም በእያንዳንዱ ቁሳቁስ ላይ ከ2 መቶ እስከ 3 መቶ ብር ጭማሬ አሳይቷል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም፣ የሕንፃ መሣሪያዎች የመሸጫ ዋጋ በየወቅቱ እያሻቀበ መምጣቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄዱ የመንገድም ሆነ ሌሎች የሕንፃ ግንባታዎች እየተቀዛቀዙ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህ ባሻገር ግንባታ የሚያከናውኑ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ከገንዘብ እጥረት ጋር በተያያዘ ሥራቸውን ለማቆም በመገደዳቸው ለዘርፉ መቀዛቀዝ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው በተጨማሪ ምክንያትነት እንደሚጠቀስ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ለሕንፃ መሣሪያዎች የዋጋ መጨመር ከውጪ ምንዛሬ እና ከሌሎች ሕገ ወጥ አሰራሮች ጋር ተያይዞ በምክንያትነት የሚነሳ ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ በዚህ ጥናት ላይ ተደግፎ የሠራቸው ሥራዎች አለመኖራቸው ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የይዞታ ማረጋገጫ እና ካርታ ለሚያቀርቡ አካላት የግንባታ ፍቃድ ከመስጠት ኃላፊነቱ ጎን ለጎን፣ የክትትል እና ቁጥጥር እንዲሁም የግንባታ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ሥራ እንዲጀምሩ ያደርጋል ተብሏል።
ከዚህ ባለፈ ባለሥልጣኑ የግንባታ ሥራዎች እንዳይቆሙ የማስገደድ ኃላፊነት የለበትም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በከተማዋ የተጓተቱ እና የቆሙ የግንባታ ሥራዎችን የመለየት ሥራ እንደተጀመረ እና በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ሙሉ መረጃ የማሰባሰብ ሂደቶች መጀመራቸውን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
ባለሥልጣኑ መረጃውን አሰባስቦ ካጠናቀቀ በኋላ ለኅብረተሰቡ ሪፖርቱን ከማሳወቅ ባለፈ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ዘርፉን ለማነቃቃት የሚያግዝ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ተነግሯል።
በተጨማሪ፣ ዘርፉ እንዲነቃቃ እና ወደነበረበት እንዲመለስ ከታሰበ መንግሥት ከባለሀብቶች ጋር በጋራ በመሥራት የግንባታ ቁሳቁሶች የመሸጫ ዋጋ ለማረጋጋት መሥራት እንዳለበት ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ከመንግሥት ባለፈ ባለሀብቶችም ሆነ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ዘርፉን ለማነቃቃት ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር፣ በከተማዋ ሕገ ወጥ ግንባታ ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ የቁጥጥር ሥራዎች እንዲያከናውኑ እና ለባለሥልጣኑ ጥቆማ በመስጠት ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ተጠይቋል።
ባለትዳር እና የአንድ ልጆ አባት እንደሆነ እና ኑሮውን ለመግፋት በግንባታ ሥራ በቀን ሠራተኛነት እንደሚሠራ የተናገረው ሰይድ እንድሪስ ነው።
ሰይድ ከጊዜ ጊዜ ውድነቱ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም እየታገለ እንደሆነ እና ቤተሰቡን ለማስተዳደር ተፈጥሯዊ ጉልበቱን በመጠቀም ከአራት ዓመት በላይ በዘርፉ በቀን ሥራ ላይ ተሰማርቶ መሥራቱን ያስረዳል።
በግንባታ ዘርፍ በቀን ሠርቶ የሚያገኘው ገቢ በድሎት የተሞላ ኑሮ ለመኖር ባያስችለውም፣ ራሱን እና ቤተሰቡን የእለት ጉርስ እየሸፈነለት እንደነበር ተናግሯል። ነገር ግን በአሁን ወቅት የግንባታው ዘርፍ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ይናገራል።
በዚህም ምክንያት የሚሠራው የቀን ሥራ ላይ ተግዳሮት እየገጠመው እንደሚገኝ እና ግንባታ የሚገነቡ ኮንትራክተሮችም በቀን ሠራተኛነት ቀጥረው የሚያሠሯቸውን ሠራተኞችን እያገዱ መሆናቸውን ሰይድ ይጠቅሳል።
አክሎም በዘርፉ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ለመሥራት ሥራ እንዳላገኘ እና እያደር በሚያሻቅበው የኑሮ ውድነት ምክንያት ለችግር መዳረጉን ይገልጻል። በተጨማሪ በቀን ሥራ በሚሠራት ገቢ የሚተዳደሩት ቤተሰቦቹም ክፉኛ መቸገራቸውን አስረድቷል።
የተለያዩ አማራጮችን ለመፍጠር እንደሚታገል ያነሳው ሰይድ፣ አማራጮችን ቢጠቀምም ቤተሰቡን ለመምራት በቂ አይደለም ብሏል። የተቀዛቀዘው የግንባታ ዘርፍ እንዲነቃቃ መንግሥት ችግሮችን ተረድቶ በትኩረት እንዲሠራባቸው ይጠይቃል። በተጨማሪም የተለያዩ ማነቆዎች በቶሎ የሚፈቱ ከሆነ ዘርፉም ወደ ነበረበት እንደሚመለስ እና የሥራ እድሎችም እንደሚፈጠሩ ያምናል። ይህም እንደሱ ቤተሰቦቻቸውን ጭምር በግንባታው ዘርፍ ላይ ተማምነው ለሚያስተዳድሩ መፍትሄ ይሆናል ሲል ስጋቱን የሚያስወግድለትን መፍትሄ ያስቀምጣል።
ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014



