ሰውነታችን በሕይወት ለመቆየት የሚያስፈልገው ዋናው ምግብ ቢሆንም፣ የይዘቱና የመጠኑ መለያየት ጤናማ ሆኖ ለረጅም ዘመን ለመቆየት የመቻላችንን ሁኔታ ይወስነዋል። የሰው ልጅ እንደሚበላው የምግብ ዓይነትና ጥራት በሽታን የመቋቋም ተፈጥሯዊ ብቃት እንደሚኖረውም ይታወቃል። አንዳንድ የምግብ ክፍሎችም በራሳቸው እንደመድኃኒት ስለሚያገለግሉ ጥቅማቸው ሰፊ እንደሆነ ይነገርላቸዋል።
በጠቃሚነታቸው ከሚታወቁ የምግብ ዓይነቶች መካከል በተለይ ለእድገት ወተትን የሚወዳደረው ባይኖርም፣ ሌሎች እንቁላልን የመሳሰሉ የሰውነት ገንቢዎችም ጥቅማቸው የጎላ እንደሆነ ይታመናል። በዓለማችን ባሉ በየትኛውም አካባቢ ባሉ የተገለሉም ሆኑ የሠለጠኑ ማኅበረሰቦች ውስጥ ወተትም ሆነ እንቁላል የማይበላበት ስለመኖሩ የሚታወቅ መረጃ የለም።
እንቁላልን ስናነሳ እንደምትጥለው እንስሳ ዓይነት የተለያየ ቢሆንም፣ ከአነስተኞቹ ወፎች በስተቀር የሰጎን ጭምር ለምግብነት ይውላል። የአሳ እንቁላል፣ የአዞና ኤሊ እንዲሁም የእባብ እንቁላል ጭምር በተለያዩ ማኅበረሰቦች ዘንድ ተወዳጅ ምግብ እንደሆኑ ይነገራል።
ስለእንቁላል ይህን ያህል ያልናችሁ፣ ከላይ በርዕሱ እንደጠቆምናችሁ እስከዛሬ ለምግብነት ጥቅም ይሰጣል ከሚባልለት በላይ ለልብ ጤንነት ወሳኝ መሆኑ የተረጋገጠበት ጥናት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ነው። እንደ ጥናቱ ከሆነ በቀን ቢያንስ አንድ እንቁላል የሚመገብ ሰው በልብ በሽታ የመጠቃቱ እድል ዝቅተኛ እንደሚሆን ነው።
በቻይና ተመራማሪዎች በተካሄደው በዚህ ጥናት፣ በተለምዶ ለብዙ ነገሮች ጥቅም አለው የሚባለው የእንቁላል ጠቀሜታ በምርምር የተረጋገጠበት ነው ተብሏል። በውስጡ ፕሮቲን፣ ሚኒራሎችንና ቫይታሚኖችን የመሳሰሉ የተለያዩ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን እንደያዘ የሚነገርለት እንቁላልን አዘውትሮ መመገብ ከልብ ጤና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው መረጋገጡን ሄልዝ 24 የተባለው የዜና አውታር ዘግቦታል።
እንደናሙና በተመረጡ በ4 ሺሕ 780 ሰዎች ላይ የተካሄደው ጥናት፣ እንቁላል ለልብ ሕመም እንዳንጋለጥ በማድረግ ልብ ድካምን ከመሳሰሉ የልብ ሕመሞች እንደሚጠብቀን አሳውቋል። በደም ውስጥ ያሉ ለሰውነታችን እድገት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች በተገቢው መንገድ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እንቁላል ውስጥ ያሉ የተለያዩ ውህዶች እጅግ ጠቃሚ ናቸው ተብሏል።
በየቀኑ እንቁላልን መመገብ ለልብ ሕመም ይጠቅማል የሚለው የአሁኑ ዓይነት የጥናት ውጤት ይፋ ከመሆኑ በፊት ስለእንቁላል የነበረ አመለካከት የተዛባ እንደሆነ ተመላክቷል። የልብ ድካም እያልን የምናውቀው የዓለማችን ገዳይ በሽታ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል። የደም ማስተላላፊያ ትቦዎችንና ልብን የሚያጠቃው ይህ በሽታ በተጠራቀመ ስብ ሳቢያ የሚከሰት እንደመሆኑ ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን ያላቸው ምግቦች በሽታውን ያስከትላሉ ተብሎ ይታመን ነበር።
እንደ ሳይንሳዊው ጥናቱ ከሆነ ግን፣ በቀን አንድ እንቁላልን አመጣጥኖ የሚመገብ ሰው ጤናማ እንደሚሆን ቢረጋገጥም፣ አብዝቶ መብላቱ ግን ጠቃሚ ነው ማለት እንደማይቻል ነው።
ሠሞኑን ይፋ በተደረገው በዚህ በቻይኖቹ ጥናት እስከቅርብ ይታመን የነበረው ትክክል ሳይሆን በተቃራኒው እንደሆነና ይብሱኑም እንቁላል በየቀኑ ሳይበዛ የሚወሰድ ከሆነ ለጤናችን እንደሚጠቅመን ነው። ይህ የተባለው በየቀኑ የሚመገቡ አልፎ አልፎ ከሚመገቡት የተሻለ የልብ በሽታን የመቋቋም ብቃት እንደሚኖራቸው ስለታወቀ ነው ተብሏል።
የጥናቶች መጣረስ
ስለእንቁላል የተካሄደው ይህ የአሁኑ ምርምር የመጀመሪያ አይደለም። ከዚህ ቀደም በቻይናም በአሜሪካም የተካሄደ ሲሆን፣ የግኝቱ ውጤት ግን የተለያየ ነው። ከአራት ዓመት በፊት ቻይና ውስጥ በተደረገ ጥናት በየቀኑ በአማካይ አንድ እንቁላልን የሚመገቡ ሰዎች ከማይመገቡት ያነሰ ለልብ በሽታ ሊጋለጡ እንደሚችሉ የተመላከተበት ነበር። ከዓመት በኋላ በፈረንጆቹ 2019 አሜሪካን አገር በተደረገ ሌላ ጥናት ደግሞ በተቃራኒው ቢያንስ ግማሽ እንቁላልን በየቀኑ መመገብ ለልብ በሽታ የመጋለጥ እድልን እንደሚጨምር የሚያሳይ ነበር።
የኹለቱን ጥናቶች ውጤት እርስ በርስ መጣረሱን ያዩ የቻይና ተመራማሪዎች፣ ልዩነቱን ለማጥራት በማሰብ ነበር ሰፋ ያለ ናሙናን በመውሰድ ጥናቱን ለማካሄድ የሞከሩት። ልዩነቱ የመጣው ከእንቁላሉ ዓይነት ይሁን ወይም ለናሙና ከተመረጡት የማኅበረሰብ ክፍሎች ልዩነት፤ የተባለ ነገር የለም። ሆኖም የአሁኑ ምርምር የቀደመውን የቻይናውን ግኝት የደገፈ ሆኖ ተመዝግቧል።
የቤጂንጉ ፔኪንግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በቻይና የታካሚዎች መረጃ ከሚከማችበት ባዮ ባንክ የሚገኙ የ4 ሺሕ 779 ሰዎችን መረጃ በመውሰድ ጥናቱን አካሂደዋል። ከእነዚህ መካከል 3ሺሕ 401 የሚሆኑት የልብ ችግር ያለባቸው ሲሆኑ፣ የተቀሩት ደግሞ ምንም ዓይነት ከልብ ጋር የተገናኘ ሕመምም ሆነ በሽታ የሌለባቸው ናቸው።
በጥናቱ የተካተቱ ሰዎችን የአበላል ታሪክ የእያንዳንዳቸውን በማጣራት መረጃቸው ከተመዘገበ በኋላ፣ የደም ናሙናቸውን በመውሰድ በውስጡ ያሉ ንጥረ ነገሮችን በማነፃፀር ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ የታወቀበት ዘዴ ነው ተብሏል።
በጥናቱ መሠረት ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን ያለውን እንቁላልን የመሳሰለ ምግብ በየቀኑ ሳያበዙ የሚመገቡ በደማቸው ውስጥ ኮሌስትሮል እንዳይበዛ የሚያደርግ ንጥረ ነገራቸው ከፍተኛ ስለሚሆን፣ ከልብ ጋር የተገናኘ በሽታ የመጠቃታቸው አዝማሚያ ምንም ከማይመገቡት አልያም አልፎ አልፎ ከሚበሉት የተሻለ ነው ተብሏል።
ጥናቱ ውጤቱን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነው ማስባል አይችልም ያሉት ዋና ተመራማሪው፣ ለወደፊት ተጨማሪ ጥናቶች እንዲደረጉ በር የሚከፍት ነው ብለዋል። እስከዛሬ ስለእንቁላልና ልብ ሕመም የነበረ እውቀትን የሚያዳብር ጠቋሚ ፍንጭ የሚሰጥ ምርምር በመሆኑ በዋዛ መታየት እንደሌለበትም ጠቁመዋል።
አቮካዶና የልብ ሕመም
ልክ እንደእንቁላል ሁሉ አቮካዶ መመገብም በልብ በሽታ እንዳንጋለጥ እንደሚያደርግ ሌላ ጥናት ጠቁሟል። ቢያንስ በሳምንት ኹለት ጊዜ አቮካዶን የሚመገቡ ሰዎች ናቸው በልብ ሕመም እንዳይጋለጡ የሚያደርጋቸው ያሉት ተመራማሪዎች፣ ምን ያህል በበሽታው የመጠቃታቸው እድል እንደሚቀንስም በአሃዝ አስቀምጠዋል።
በሳምንት በአማካይ ግማሽ አቮካዶን ኹለት ጊዜ የሚበሉ ካርዲዮ ቫስኩላር ዲዚዝ በሚባለው በሽታ የመጠቃት እድላቸው በ16 በመቶ የሚቀንስ ሲሆን፣ ኮሮናሪ ኸርት ዲዚዝ በሚባለው የልብ በሽታ የመጠቃት እድልን ደግሞ በ21 በመቶ ይቀንሳል ተብሏል።
በአሜሪካኑ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዶ ይፋ የተደረገው ይህ የረጅም ጊዜ ጥናት በብዙ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች መናኘቱ የሚታወቀው አቮካዶ ለልብ ጤንነት ቀጥተኛ የሆነ ጥቅም እንዳለው ነው ያሳየው። ለልብ ሕመም ሊዳርጉ የሚችሉ ቅቤንና አይብን እንዲሁም ስጋን ከማዘውተር ይልቅ ሰዎች አመጋገባቸውን ወደ አቮካዶ እንዲቀይሩና ጤናቸውን እንዲጠብቁ ተመክሯል።
እድሜያቸው ከ30 እስከ 70 ዓመት የሚሆናቸው የ110 ሺሕ ሰዎች ናሙና በተመረመረበት በዚህ ሰፊ ጥናት፣ ከመነሻው ጀምሮ ምንም ዓይነት የልብም ሆነ የካንሰር በሽታ የሌለባቸው ሰዎች በሰፊው የተካተቱበት ነው። ገና ከመነሻው አንስቶ ስለአመጋገባቸው፣ የአወሳሰድ መጠናቸውና ልዩነታቸው በመጠይቅ አማካይነት በምርመራ እየታየ ሲመዘገብ የቆየ ነው።
30 ዓመታትን በፈጀው በዚህ ጥናት ቢያንስ በየአራት ዓመቱ የተሳታፊዎቹ የጤናና የአመጋገብ ልዩነት እየተመዘገበ የተያዘ ሲሆን፣ ረጅም ጊዜን ከፈጀ የንፅፅር ጥናት በኋላ በልዩነት የተመዘገበው የጥናቱ ግኝት ይፋ የተደረገበት ነው። እንደግኝቱ ውጤት ከሆነ አዘውትረው አቮካዶን በየሳምንቱ የሚመገቡት፣ እየቆዩ መደበኛ ባልሆነ መጠን ከሚመገቡት በተሻለ በልብ ሕመም የመጠቃታቸው እድል ዝቅተኛ እንደሆነ ነው።
ከላይ የተጠቀሱት ኹለቱም ጥናቶች በቻይናና አሜሪካ የተደረጉ እንደመሆናቸው የዓለምን ሕዝብ እንደማይወክሉም ተጠቅሷል። ነጭ ሀብታሞች በበዙበት የናሙና አወሳሰድ የተገኘው መረጃ ጠቋሚ ሊሆን ይችላል እንጂ፣ እንደ አፍሪካ አህጉር ውስጥ እንዳሉ በድህነት ለፍተው ለሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚኖረው ፋይዳ እምብዛም እንደሆነ ተጠቁሟል።
የልብ በሽታ በድሃ አገራትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ መሆኑ ቢታወቅም፣ አቮካዶንም ሆነ እንቁላልን በመደበኛነት ለመመገብ የሚችለው የድሃ አገር ሕዝብ ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው። የኑሮ ውድነት እንዲህ ዓይነት ምግቦች የቅንጦት መገለጫ እንዲሆኑ ከማድረጉ ባሻገር፣ አቮካዶ በብዛት ወደ ውጪ መላክ መጀመሩ እንዲሁም የዶሮ በሽታ መጣ ተብሎ እንቁላል ከገበያ መውጣቱ ምግቦቹን የማግኘት ችግሩን እንደሚያባብሰው ግልፅ ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 190 ሰኔ 18 2014



