ከሠሞኑ ይፋ የተደረገ የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ሪፖርት እንደጠቆመው፣ ድርቅ በተከሰተባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሕጻናት ጋብቻ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን ነው። በተለይ ድርቁ በበረታባቸው የሱማሌ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች 12 ዓመት የሚሆናቸው ሕጻናት ጭምር በቤተሰቦቻቸው አማካኝነት ለትዳር እየተሰጡ መሆኑ ታውቋል።
ዓለም ዐቀፉ ተቋም በቁጥር የተደገፈ ማስረጃ አግኝቻለሁ ብሎ በያዝነው ሳምንት ይፋ እንዳደረገው፣ ካለፈው 30 ዓመት ወዲህ እየቀነሰ የነበረው ያለእድሜ ጋብቻ ካለፉት 4 ወራት ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ እንደሆነ ነው። ለዚህ ምክንያት የተባለው ላለፉት 4 ዓመታት ያህል ወቅቱን ጠብቆ መዝነብ የነበረበት ዝናብ ባለመምጣቱ ምክንያት የተከሰተው ድርቅ ነው።
ለብዙዎች ሞትና መፈናቀል እንዲሁም ለከብቶቻቸው ማለቅ ምክንያት የሆነው ይህ ድርቅ እየቀነሰ የነበረውን የሕጻናት ጋብቻ እንደ አዲስ እንዲያገረሽ ማድረጉ ተነግሯል። ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያበሉት ሲያጡ አማራጭ አድርገው የወሰዱት ሕጻናት ሴት ልጆቻቸውን በጋብቻ መልክ አቅም ላላቸው ባለሀብቶች መስጠትን ነው ተብሏል።
ይህም ምግብ የሚፈልግ የቤተሰባቸውን ቁጥር መቀነስ እንዲያስችላቸው ከማድረጉ ባሻገር፣ ያለእድሜያቸው የሚዳሩት ሕጻናት ወላጆች ልጆቻቸውን ሲሰጡ በጥሎሽ መልክ ገቢ እንዲያገኙ ስለሚያስችላቸው ነው ድርጊቱ በከፍተኛ ቁጥር የጨመረው ሲል የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት አሳውቋል።
በ40 ዓመት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ ድርቅ ምሥራቅ አፍሪካን ማጥቃቱን ተከትሎ የሕጻናት ጋብቻን በተመለከተ እየታየ የነበረው መሻሻል ተቀልብሷል። የሕጻናት ጋብቻ በአራቱ ወራት ብቻ በአማካይ ሦስት እጥፍ አድጓልም ነው የተባለው። በአንዳንድ ወረዳዎች በኹለት እጥፍ ማደጉ የተመዘገበ ሲሆን፣ አጠቃላይ ሁኔታው ሲታይ በጣም አሳሳቢ መሆኑ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በተለይ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር እጅጉን የሕጻናቱ ጋብቻ ጨምሯል። ዩኒሴፍ እንዳለው መረጃው የተገኘው ከየአካባቢዎቹ የወጡ መረጃዎችን በመመርኮዝ ሲሆን፣ በልጅነታቸው እንዲያገቡ የሚደረጉት ሕጻናት እስከ አምስት እጥፍ በእድሜ የሚበልጧቸውን ሰዎች እንዲያገቡ እየተገደዱ ነውም ተብሏል።
የተቋሙ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ተጠሪ የሆኑት አንዲ ብሩክስ ስለተግባሩ አሳሳቢነት ሲናገሩ፣ ወላጆች ይህን የሚያደርጉት የተግባራቸውን አስከፊነት ሳይረዱት ቀርተው ሳይሆን አማራጭ አጥተው እንደሆነ ያስረዳሉ። የ12 ዓመት ሕጻንን ሳይቀር የሚድሩ ወላጆች ልጆቻቸው በረሃብ ከሚያልቁባቸው ቢዳሩ ይሻላል ብለው እንደሆነም ጠቁመዋል።
ችግሩ ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ሕጻናቱ ያለእድሜያቸው ትልልቆችን እንዲያገቡ መገደዳቸው ሌላ ችግር ያስከትልባቸዋል። በባህላቸው መሠረትም የሴት ልጅ ግርዛት የነበረ ቢሆንም እየቀነሰ ከነበረበት ተመልሶ እንዲጨምር ድርቁ ማድረጉም ተመላክቷል።
ለጋብቻ እንደቅድመ ሁኔታ የሚወሰደው ይህ የሴቶች ግርዛት በሕጻንነታቸው የሚፈፀም እንደመሆኑ፣ ቤተሰቦች ልጃቸውን ለመዳር በማይግደረደሩበትና ይብሱኑ በሚፈልጉበት ወቅት፣ ልጆቻቸው ተፈላጊነታቸው እንዲጨምር ሲሉ ይህን እየቀረ የነበረ ክፉ ልማድ እንደሚያስፈፅሙባቸው ተጠቅሷል።
የሕጻናቱ ጋብቻ ባለፉት አራት ወራት እጅግ ከመጨመሩ በፊትም ያለእድሜ ጋብቻ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደነበር ጥናቶች ያመላክታሉ። ለምሳሌ አሁን ድርቁ በተከሰተባቸው የሱማሌ ግዛቶች ባለፈው ዓመት ያለእድሜያቸው ለትዳር የተሰጡ ሕጻናት ቁጥር ከፍተኛ ነበር።
ከዓመት በፊት በተለያዩ የሱማሌ አካባቢዎች ከተፈፀሙ ጋብቻዎች 40 በመቶ የሚሆኑት ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትና ታዳጊዎች ያለእድሜ ጋብቻ የፈጸሙበት ነበር። የባለፉት አራት ወራት አሐዝ እንደሚያሳየው ግን አሁን የሚፈፀሙ ያለእድሜ ጋብቻ ከአምናው በሦስትና ኹለት እጥፍ እንደጨመረ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት ጋብቻን ለማስቀረት እንደ አጀንዳ ይዞ መንቀሳቀስ ከጀመረ የቆየ ቢሆንም፣ ላለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ ጥሩ ሥራ ሠርቶ እንደነበር ይናገራል። ከሦስት ዐስርት ዓመታት በፊት 18 ዓመት ባልሞላቸው ልጆች ይፈፀም የነበረው 70 በመቶ ጋብቻ መሻሻል አሳይቶ ወደ 40 በመቶ ወርዶ ነበር መባሉን ተቋሙ በሪፖርቱ አመላክቷል።
ላለፉት ዓመታት በተከታታይ የተከሰተው ድርቅ የዘመናት ሥራን ወደኋላ መልሷል ያለው ተቋሙ፣ የሰው ሕይወትን ማትረፍ ቀዳሚው ተግባር ቢሆንም ማኅበረሰቡ በዘላቂነት ሕይወቱን ሊመራበት የሚያስችለው ነገር በአፋጣኝ ካልተመቻቸለት የባሰ ነገርም ሊከሰት እንደሚችል ጠቁሟል።
ሕጻናቱ ያለእድሜ ሲዳሩ የሚከሰተው የጤናና የሥነልቦና ችግር እንዳለ ሆኖ፣ በማኅበራዊ ሕይወታቸው ረገድም የሚያስከትልባቸው ተጽዕኖ ቀላል አይሆንም። በዚህም ሳቢያ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ማድረጉም መገለልን የመሳሰለ በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችል ማኅበረሰባዊ ችግር ሊያስከትል ይችላል።
ወደቀደመው ዘመን የሚመልሰው ይህ ድርቅ እስከ አሁን በርካታ ያላገቡ ሴቶችንም ከትምህርት አፈናቅሏል ተብሏል። በድርቁ ሳቢያ ወደ ትምህርት ቤት የማይሄዱ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ቢታወቅም፣ ተፈናቅለውም ሆነ ቸግሯቸው የማይማሩት ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ተገምቷል። ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ የቀሩባቸው የትምህርት ተቋማትም በራቸውን ዘግተው የመማር ማስተማሩን ሂደት እንዳቋረጡት ተመላክቷል።
በዚህም ሳቢያ ተምረው ሕይወታቸውን ለመቀየር ያስቡ የነበሩ ታዳጊዎች ባላቀዱበት መንገድ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ድርቁ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩ ተነግሯል። ይህም ሲሆን በግዛቱም ሆነ በአገር ደረጃ ተፈላጊው የተማረ የሰው ኃይል እንዳይኖር ስለሚያደርግ የእድገት ጉዞን ይቀለብሳል ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት የተረዱት ሲናገሩ ይደመጣሉ።
ስለሕጻናቱ ያለእድሜ ጋብቻ የወጣውን ሪፖርት አል-አረቢያን እና ብሉምበርግን የመሳሰሉ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ዘግበዉታል። ክስተቱም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በጎረቤቶቻችን ሱማሊያና ኬንያም እንደተስተዋለ ተነግሯል።
ኢትዮጵያ ከ2020 እስከ አሁን ድረስ ባሉት ኹለት ዓመታት ሕጻናትን በመዳር ወይም ያለእድሜ ጋብቻ የሚፈጸምባት በመሆን ከዓለም አገራት አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፣ 2.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕጻናት ያለእድሜ ለትዳር የተሰጡባት አገር ናት ተብሏል። ሦስተኛ የሆነችው ናይጄሪያ 3.7 ሚሊዮን ሕጻናትን በመዳር ከአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም፣ የኢትዮጵያ አካሄድ በዚሁ ከቀጠለ ናይጄሪያን ለመቅደም ጊዜ እንደማይወስድባት ተጠቅሷል። ሕጻናትን ያለ እድሜያቸው በመዳር ቀዳሚዎቹ ሕንድ በ12 ሚሊዮን፣ ባንግላዴሽ በ4 ሚሊዮን ተከታትለው የተቀመጡ ሲሆን፣ ድህነትና የኑሮ ውድነት ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ይነሳሉ።
ለሕጻናቱ ጋብቻ መባባስ ሌላው ምክንያት የነበረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ነበር። ክስተቱ በርካቶችን ቤት ባዋለበት ሰሞን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው ቤት ለመዋል ተገደው ስለነበር የሕጻናቱ ጋብቻ ቁጥሩ ጨምሮ ነበር። በወቅቱ ችግሩን የተመለከቱ አካላት ለማስቆም ሞክረዋል። ከኹለት ዓመት በፊት በዚህ መንገድ ሊዳሩ ብለው ጋብቻቸው የተቋረጠ 500 የሚሆኑ ሕጻናትን በኹለት ወር ውስጥ ብቻ ከሰሜን የኢትዮጵያ ግዛቶች መታደግ መቻሉን ሬውተርስ ጭምር አስነብቦ ነበር።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንደዘመናዊ ባርነት የሚያዩትን የሕጻናት ጋብቻን ለማስቀረት ሲደክሙ ይስተዋላሉ። የልፋታቸውን ውጤት እየተመለከቱ ሳለ ግን፣ የተፈጥሮ አደጋም ሆነ ጦርነትን የመሳሰሉ ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ልፋታቸውን መና እንደሚያስቀርባቸው ይናገራሉ።
ዩኒሴፍን የመሳሰሉ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት መሻሻል ዐሳይቶ የነበረው የሕጻናቱ ጋብቻ በተለያዩ ምክንያቶች እየጨመረ እንደሆነ እየተናገሩ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ 15 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕጻናት ያለእድሜያው ተድረው ባለትዳሮች ሆነው አሉባት ብሎ የሚያምነው ይህ ተቋም፣ በፈረንጆቹ 2030 ተጨማሪ 13 ሚሊዮን ሕጻናት ያለእድሜያቸው እንዲያገቡ ሊደረግ ይችላል ሲል ስጋቱን አስቀምጦ ነበር። ለጭማሪው በዋናነት ምክንያት ያደረገውም ድህነትን ነው።
የሕጻናት ያለእድሜ ጋብቻ አስከፊነቱን በብዙ መልኩ መግለጽ እንደሚቻል ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። ትምህርታቸውን አቋርጠው የተለያዩ እድሎች እንዲያመልጧቸው ከማድረጉ ባሻገር፣ በጤናቸው ላይ ችግር ሊያስከትልባቸውም ይችላል። ለጉልበት ብዝበዛም ከማጋለጡ በላይ፣ ለፆታዊ ጥቃት እንዲዳረጉም ምክንያት ነው። የስቃይ ኑሮን ሊገፉ ከመቻላቸው በላይ በወሊድ ወቅትም ሊሞቱ የሚችሉበት እድል ከፍተኛ በመሆኑ፣ የነበረው መሻሻል እንዲቀጥልና ወደ ነበረበት መሻሻል እንዲመለስ ርብርብ ያስፈልጋል ተብሏል።
ችግሩን ለመቅረፍ አስገዳጅ ሕግ አውጥቶ የተላለፉትን ለፍርድ ማቅረቡ እንዳለ ሆኖ፣ ማስተማርና ለድርጊቱ የሚገፋፋቸውን ችግራቸውን መቀነስ ሂደቱን ቀስ በቀስ ለመቀነስ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ያለመሰልቸት መሠራት እንዳለበት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሂደቱ የሚያስቀጣ ሆኖ ወላጆች ቅጣትን እንዲፈሩ ማድረጉ መቅረት የሌለበት ሂደት ቢሆንም፣ ከሞትና ድህነት ቅጣቱ ይሻላል ብለው እንዳይገቡበትና የሕጻናቱን ሕይወት እንዳያበላሹት በከፍተኛ ፍጥነትና ትኩረት ስለጉዳዩ መጮኽ እንደሚገባም ባለሙያዎቹም ይስማማሉ።
የአገር ሽማግሌዎችም ሆኑ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ሰዎችን በመያዝ የችግሩን አሳሳቢነት እንዲረዱ በማድረግ ድርጊቱ ውስጥ የሚሳተፉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንዲያስተምሩ ማድረጉም ጠቃሚ እንደሆነ ይታመናል።
ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014



