132 የእሳት አደጋዎች በዚህ ዓመት ተከስተው ንብረት አውድመዋል
የባህር ዳር ከተማ አሁን ያላት የእሳት አደጋ መከላከያ በአደረጃጀት እና በአቅም ከከተማዋ ዕድገት ጋር የማይመጣጠን መሆኑ ተገለጸ። የባህር ዳር ከተማ እሳት አደጋ መከላከልና ዘላቂ ማረፊያ ቡድን የሥልጠና ክፍል አስተባባሪ ሁሴን እንድሪስ፣ ከከተማዋ እድገት ጋር የሚመጣጠን የእሳት አደጋ መከላከያ ተቋም እንደሌለ እና አሁን ያለውም ብዙ ችግሮች እንዳሉበት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በዚህም በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው ዓመት 132 የእሳት አደጋዎች መድረሳቸውን ተናግረው፣ አደጋዎቹ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ በንብረት ላይ የደረሱ ውድመቶች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። ሆኖም ተቋሙ ባለበት የሰው ኃይል እጥረት ሳቢያ የንብረት ግምት ለመሥራት ሙያተኛ የሚያስፈልግ በመሆኑ በእሳት አደጋው የደረሰውን ጉዳት የንብረት ግምት ለማስቀመጥ እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።
አሁን እየተሠራ ያለው በአራት ሹፌርና በዘጠኝ ተከላካይ ብቻ ነው ያሉት አስተባባሪው፣ በዚህም የተሟላ የሰው ኃይል የለንም ሲሉ ተናግረዋል። ያለንበት ቦታም ብዙ ጊዜ የትራፊክ መጨናነቅ የሚበዛበት በመሆኑ አደጋ በደረሰ ጊዜ ፈጥኖ ለመውጣትና ቦታው ቶሎ ለመድረስ የማይመች ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
የበጀት እጥረት በመኖሩ ምክንያት አስፈላጊ የቢሮ እቃዎች የሉንም ካሉ በኋላ፣ የበጀት ችግሩ ከጦርነቱ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው፣ ሆኖም የበጀት እጥረቱ ሊስተካከል እንደሚገባው አስገንዝበዋል። እንዲሁም ከከተማ ውጭ እንደ መሸንቲ፣ መራዊና ሀሙሲቲ ከተሞች ለአገልግሎት እንደሚወጡ ገልፀው፣ ከከተማዋ ዕድገትና መስፋት ጋር ተያይዞ ተቋሙ አሁን ካለበት ቡድን ወደ ጽሕፈት ቤት ሊያድግና በደንብ ሊደራጅ ይገባል ነው ያሉት።
አሁን ያለው የእሳት አደጋ መከላከል አደረጃጀት በአንድ ጽሕፈት ቤት ውስጥ አንድ የሥራ ሂደት (ቡድን) መሆኑ፣ ቀርቶ ጽሕፈት ቤት ቢሆን ብዙ ችግሮች ሊቃለሉ እንደሚችሉም አመላክተዋል። እንዲያውም በየክፍለ ከተሞች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሊኖሩት የሚገባ እንደነበር ነው የገለጹት። አሁን ያለው ያልተደራጀ መሆኑና አራት የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎች ቢኖሩም የሰው ኃይል የለንም ብለዋል።
ይህም አገልግሎት መስጠት የሚችሉ አራት ተሽከርካሪዎች ቢኖሩም፣ የእሳት አደጋ በሚፈጠርበት ወቅት ለኹሉም መኪኖች ሙያተኞች ስለሌሏቸው አደጋውን ለመከላከል ጥቅም ላይ እንደማይውሉ ነው የተመለከተው። በእሳት አደጋው ወቅት የሠራተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችሉ የተሟሉ ቁሳቁሶች አለመኖራቸውም ተጠቁሟል።
እንዲሁም አስተባባሪው አክለው፣ የእሳት አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ውሃ ለመቅዳት የሚያገለግሉ የውሃ ማጠራቀሚያዎች (ሀይድራንት) የሉም ማለት ይቻላል ነው ያሉት። አደጋው ሲከሰት ቶሎ ቶሎ ውሃ ለመቅዳት አስፈላጊ በመሆናቸው በተወሰነ ርቀት በየቦታው ሊኖሩ ይገባ ነበር፣ ያም ባይሆን ቢያንስ በየክፍለ ከተሞች መኖር ነበረባቸው። ለከተማዋ አሁን ያሉት ግን ኹለት ብቻ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።
የውሃ መቅጃዎችን በየቦታው ለመትከል ከማስተር ፕላን ጋር የተያያዙ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል። የውሃ መቅጃዎች በ200 ሜትር ገደማ ርቀት መኖር የሚገባቸው ቢሆንም፣ በከተማዋ ያሉት ኹለት ብቻ በመሆናቸው፣ አደጋ በሚፈጠርበት ወቅት በኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዞ ውሃ ተቀድቶ ሲመጣ የእሳት አደጋው ከፍተኛ ውደመት ያደርሳል ነው የተባለው።
እስከ አሁን የሚጠይቅ አካል ባለመኖሩና የከተማ አስተዳደሩም ያን ያህል ትኩረት ሳይሰጠው በመቆየቱ አደረጃጀቱ እና አቅሙ ሳይስተካከል መኖሩን አመላክተውም፣ የእሳት አደጋ የሚያስከትለውን ጉዳት በመረዳት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አስተባባሪው አሳስበዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014



