በተላላፊ በሽታ የተያዙ 700 የጊምቢ ወረዳ ተፈናቃዮች ሕክምና ማግኘት አልቻልንም አሉ

0
1405

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ እና አጎራባች አካባቢ በጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ ከ700 በላይ ሰዎች በተላላፊ በሽታ ቢያዙም ሕክምና እያገኙ አለመሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ እና አጎራባች ቦታዎች ከኹለት ሳምንት በፊት ጀምሮ የኦነግ ሸኔ ቡድን ያደረሰውን ግድያ እና ጥቃት በመሸሽ በአካባቢው በሚገኙ የመጠለያ ጣቢያዎች የተጠለሉ ዜጎች ቁጥር ከሰባት ሺሕ በላይ መድረሱ ተሰምቷል፡፡

ከእነዚህ መካከል ከ700 ያላነሱ ሰዎች በአካባቢው ባለው የአየር ፀባይ እና የክረምት ወቅቱን ተከትሎ በውኃ ብክለት እና በተለያዩ ምክንያቶች በሕክምና ተረጋግጦ ባልታወቀ ተላላፊ በሽታ የተያዙ ቢሆንም፣ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

አክለውም፣ በመጠለያ ጣቢያው የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች አለመኖራቸውን እና በአካባቢው የኦነግ ሸኔ ቡድን መኖሩን ተከትሎ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በነፃነት መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ሌሎች ቦታዎች ወደሚገኙ የጤና ተቋማት አቅንተው ሕክምና ማግኘት እንዳልቻሉም ተናግረዋል።

ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጥያቄ እያቀረቡ ሲሆን፣ የሕክምና አገልግሎቱን እንዲያገኙ እየተሠራ መሆኑ ቢነገራቸውም፣ አዲስ ማለዳ መረጃውን እስካጠናቀረችበት ጊዜ ድረስ ምላሽ እንዳላገኙ አመልክተዋል።

በወቅቱ ምላሽ ወይንም የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ካልቻሉ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል፡፡ አያይዘውም፣ የሰብዓዊ ድጋፍ የቀረበ ቢሆንም፣ የተፈናቃይ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ድጋፉ በቂ እንዳልሆነ እና ሁሉንም ሰው ተደራሽ አለማድረጉን ተፈናቃዮች ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ የሕክምና አገልግሎት አላገኘንም የሚለውን የአካባቢው ነዋሪዎችን ቅሬታ አድምጣ ለኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ እና ለጤና ሚኒስቴር ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረገች ሲሆን ምላሽ አላገኘችም።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደበበ ዘዉዴ በበኩላቸው፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ለተፈናቀሉ አምስት ሺሕ ለሚጠጉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ ድጋፉ በቂ መሆኑን እና አለመሆኑን ግን የተፈናቃዩ ቁጥር የሚወስነው ይሆናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ በኹለት ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ በአካባቢው ለሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎች ልኳል ብለዋል። በመጀመሪያው ዙር ከኹለት ሳምንት በፊት 375 ኩንታል ሩዝ፣ 375 ኩንታል የስንዴ ዱቄት እንዲሁም ከተፈናቃዮቹ ውስጥ ለሕጻናት፣ ለነፍሰጡር እና አጥቢ እናቶች እና ደካሞችንም ታሳቢ በማድረግ 37 ኩንታል አልሚ ምግብ፣ 500 ካርቶን ብስኩት፣100 ሺሕ ቴስቲ ሶያ መላኩን ኃላፊው ጠቁመዋል።

አክለውም 2,400 ብርድ ልብስ፣ 400 ፍራሽ፣ 2,400 ብረት ድስት፣ 1,200 ጀሪካን፣ 4,800 ኩባያ፣ 4,800 ጆግ፣ 4,800 ሰሃን፣1,200 ጭልፋ ተልኳልም ብለዋል።

በተጨማሪ በኹለተኛው ዙር ማለትም ባሳለፍነው ሳምንት 4,800 ኪሎ ቴምር እና በኹለት ተሽከርካሪ ሙሉ አልባሳት ተጭኖ መላኩን ያነሱት ኃላፊው፣ በቀጣይም ከክልሉ ጋር በመነጋገር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here