የሸገር ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶች ውል ለተጨማሪ ስድስት ወራት መራዘሙን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ አሰታወቀ። ውሉ ከመጋቢት 4/2014 ጀምሮ ለስድስት ወራት እስከ መስከረም 2/2015 ተራዝሟል።
በመዲናዋ ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶች ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ በየቀኑ አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረጉ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ አበርክተዋል ተብሏል። በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት በሸገር የብዙኀን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በኩል ስምሪት እየተሰጣቸው የሚገኙ አውቶቡሶች አገልግሎት መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ ቢሮው ውላቸውን አራዝሟል።
ማኅበራትም በውሉ መሠረት የተቀመጡ የአሰራር ስርዓቶችን ሥራ ላይ በማዋል ከዚህ የተሻለ አገልግሎት እንዲኖር ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ቢሮው አሳስቧል። በሁሉም አውቶቡሶች ጂፒኤስ (GPS) በመግጠም የክትትልና ቁጥጥር ሥራው የተጠናከረ እና አገልግሎት አሰጣጡም የተሻሻለ እንዲሆን በትኩረት እንደሚከወንም ቢሮው ጨምሮ አስታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ከጥቅምት 9/2013 ጀምሮ ሀገር አቋራጭ አውቶቡሶች በኪራይ መልክ በመዲናዋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ የሚታወስ ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014


