ተፈናቃዮች ወደ ወለጋ እንድንመለስ ተገደናል አሉ

0
2007
Negassa Deslagen/DW

ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ዞን ቶሌ ቀበሌ ለደኅንነታቸው የሰጉ 64 ተፈናቃዮች ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ሆለታ ላይ በአካባቢው በሚገኙ በመንግሥት የፀጥታ አካላት ወደነበሩበት ለመመለስ መገደዳቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ የተናገሩ ዜጎች፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ዞን ቶሌ ቀበሌ አሁንም ቢሆን የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ነው ማለት እንደማይቻል እና ብዙ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው መጠለያ ጣቢያ እንዲሁም ወደተለያዩ ቦታዎች እየተሰደዱ ይገኛሉ ብለዋል።

አክለውም፣ ለደኅንነታቸው የሰጉ 64 የሚሆኑ ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ ሰኔ 29 ቀን 2014፣ 7 መቶ ብር የትራንስፖርት ክፍያ በመፈፀም ወደ አዲስ አበባ ከተማ እየመጡ ሳለ ሆለታ ከተማ ሲደርሱ፣ በአካባቢው ባለ የፖሊስ እና በፀጥታ አስከባሪ አካላት ወደ መጡበት አካባቢ ለመመለስ እንደተገደዱ ገልጸዋል።

ዜጎችን አሳፍሮ የመጣውን ተሽከርካሪ ወደ መጣበት ሰዎችን ይዞ እንዲመለስ ከማዘዝ በስተቀር የፀጥታ ኃይሎች ምንም ዓይነት ምክንያት አላስቀመጡምም ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ዞን ቶሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ካሳለም ወንድምነው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ቤተሰባቸውን እና ሀብት ንብረታቸውን በኦነግ ሸኔ ቡድን አጥተዋል። በአካባቢው ያለው ሁኔታም ለደኅንነታቸው እንደማያስተማምን ጠቁመዋል።

የራሳቸውን እና የልጃቸውን ሕይወትም ለመታደግ ከሚኖሩበት አካባቢ 700 ብር ለትራንስፖርት ክፍያ ፈፅመው ወደ አዲስ አበባ እየመጡ ሳለ፤ ሆለታ ከተማ ላይ በፀጥታ አካላት እንዲመለሱ ተገደው ሰኔ 29/2014 በአምቦ ፖሊስ ጣቢያ በተሽከርካሪ ውስጥ እንዲያድሩ መሆኑንም ነው ያወሱት።

‹‹ከአንድ ቀን አዳር በኋላ ወደ አካባቢያችን በመጣንበት ትራንስፖርት መልሰውን እንድንሄድ ተደርገናል›› ያሉ ሲሆን፣ አሁንም ቢሆን ከስጋት ነፃ እንዳልሆኑ አመልክተዋል።

ካሳለም አክለው፣ መንግሥት እሮሯቸውን አድምጦ በአካባቢያቸው ያለው የፀጥታ ችግር በዘላቂነት እንዲቀረፍ ወይም ሰላማዊ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የሚሰፍሩበትን እንዲሁም የሚሄዱበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።

ዝናቤ ምስጋነው የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ዞን ቶሌ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፣ አዲስ ማለዳ መረጃውን እስካጠናቀረችበት ጊዜ ድረስ በአካባቢው በሚገኙ እና ባደፈጡ የሸኔ ቡድን የሚገደሉ ሰዎች አሉ ብለዋል።

ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ 70 ሰዎች በቡድኑ ተገድለው መቅበራቸውን ያነሱት ዝናቤ፣ እርሳቸውም ለደኅንነታቸው በመስጋት ካሉበት አካባቢ ከነቤተሰቦቻቸው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ጉዞ ላይ በነበሩበት ወቅት ሆለታ ከተማ ላይ ሲደርሱ በከተማዋ ያሉ የፀጥታ አካላት ወደ መጡበት አካባቢ እንዲመለሱ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

በዚያው በመጡበት ቀን ማለትም ሰኔ 29/2014 አመሻሹን ተሳፍረው በመጡበት ተሽከርካሪ አምቦ ከተማ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ተሽከርካሪ ውስጥ እንዲያድሩ የተደረጉ ሲሆን፣ ‹‹ሰኔ 30/2014 በፀጥታ ኃይል ታጅበን እና ተገደን ወደ መጣንበት አካባቢ ለማቅናት ተገደናል።›› ነው ያሉት።

አዲስ ማለዳ ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ እና ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ስለ ጉዳዩ ለመጠየቅ ያደረገችው ሙከራ ያልተሳካ ሲሆን፣ ተቋማቱ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ በሆኑ ጊዜ የምናስተናግድ ይሆናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here