የአስከሬኑ ጥላ እና የሞት ፉክክር ከአሜሪካ ጋር

0
2172

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ16ኛ መደበኛ ጉባዔውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ባለፈው ሀሙስ ሰኔ 30/2014 አካሂዷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባላት በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያን በመሩበት ጊዜ የንጹሐን ዜጎች ሞትና የኢትዮጵያ ችግር መባባስ በስፋት ተነስቷል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ከምክር ቤት አባላት በቀረቡላቸው ጥያቄዎች ላይ በሰጡት ማብራሪያ ያነሷቸው ሀሳቦችን በብዙዎች ዘንድ “የጤና ሀሳብ አይደለም” የሚል ትችት እየቀረበባቸው ነው።

አነጋጋሪ ከሆኑ ንግግራቸው መካከል “ሰው እየሞተ የሞተበት ቦታ ችግኝ እንተክላለን ቢያንስ አስከሬኑ ጥላ እንዲኖረው” የሚለውን ብዙዎችን አስተያየት እየሰጡበት ነው። ብዙዎች ሀሳቡን የኮነኑት ችግኝ መትከልን በግፍ ከተገደሉ ዜጎች አስከሬን ጋር ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ማገናኘታቸው ነው።

ሰው እየሞተ ችግኝ አትትከሉ የሚለን ጠላት ነው የሚል ሀሳብ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ችግር ስላለ ችግኝ አትትከሉ ማለት ጠላትነት መሆኑን ከዚህ በፊት ገልጸው ነበር። ይሁን አንጂ ቅሬታ የፈጠረው ጉዳይ ችግኝ መትከሉ ሳይሆን፣ ብዙዎች የዜጎችን ሞት ከችግኝ ተከላ ጋር በማገናኘት “አስከሬን ጥላ እንዲኖረው” የሚለው ቃል በዜጎች ሞት እንደመሳለቅ ወስደውት በማኅበራዊ ሚደያ መነጋገሪያ አድርገውታል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር በየዓመቱ የሚያካሂደው የችግኝ ተከላ በመንግሥት በኩል ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ቢሆንም፣ የዜጎች ግድያ ተባብሶ እየቀጠለ ስለ ችግኝ ተከላ ማውራት ትርጉም የለውም የሚል ሀሳብ የሚሰጡ ሰዎች አሉ። ለዚህም ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባገኙት አጋጣሚ ስለ ችግኝ ተከላ የሚያወሩት። ይሁን እንጂ፣ በተለይ የዚህ ዓመት የችግኝ ተከላ ወቅት በርካታ ዜጎች ከተገደሉበት ወቅት ጋር መገጣጠሙ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ሀሳብ ብዙ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያን መምራት ከጀመሩ ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች በንጹሐን ዜጎች ላይ በየጊዜው የሚፈጸሙ ግድያዎች መባባሳቸውና መንግሥታቸው ለምን ማስቆም አልቻለም የሚል ጥያቄ ከምክር ቤት አባላት ቀርቦላቸዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት በዜጎች ላይ በተለይም በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ያለው “የዘር ፍጅት የዘር ፍጅቱንስ መንግስትዎ መቼና እንዴት ለማስቆም እያሰበ ነው?” በሚል ከምክር ቤቱ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በኢትዮጵያ በየአካባቢው የሚፈፀመውን ግድያ በአሜሪካ ከተፈጸሙ ግድያዎች ጋር ለማነጻጸር መሞከራቸው ብዙዎችን እያጋገረ ነው።

የንጹሐን ዜጎችን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፣ ግድያ ባደጉትና ከፍተኛ ደህንነት ባላቸው እንደ አሜሪካ ባሉ አገራትም ይፈጸማል አይነት መልስ መሥጠታቸው ብዙዎችን አስገርሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ማብራሪያ መንግሥታቸው የዜጎችን ሞት ማስቆም አልቻለም ተብሎ መወቀስ እንደለሌበት ለማስረዳት ያቀረቡት ንጽጽር በአሜሪካ በስድስት ወራት የተፈፀሙ ግድያዎችን ነው። በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ግድያዎችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካ ጋር ለማነጻጸር በቁጥራዊ መረጃ አስደግፈው ላነሱት ሀሳብ ፖለቲከኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ ሞትን ለማሳነስ ማነጻጸር ተገቢ አይደለም የሚል ትችት አሰንዝሯል።

አስተያየት ከሰጡ የማኅበረሰብ አንቂዎች መካከል በአባይ ጉዳይና በፖለቲካ ጉዳዮች ሀሳብ በመስጠት በውጭ ሚዲያዎች ለኢትዮጵያ በመታገል የሚታወቀው ሴሌማን አብደላ አንዱ ነው። ወጣቱ የማኅበረሰብ አንቂ “አሜሪካ ያለው አሸባሪ ሞት ያበዛሁ እኛ የግድ ከአሜሪካ ሞት ጋር እኩል መሞት የለብንም። ዋናው ጥያቄ የሞትን ብዛት በቀመር አስልቶ ማቅረብ አይደለም። ታንክም ባንክም በራሪ አየርም ኢንተለጀንስም የተቆጣጠረ የአንድ የአገር መሪ፣ በፍጹም አገሪቱ ላይ የሞቱትን ሰዎች ከነ ሱማሌያና ከነ አሜሪካ ጋር አባዝቶ ወንጀሉን ማሳነስ አይችልም። ነውርም ነው።

የመረጠውን ህዝብ ሲቪል ገበሬን እያስበላ ድክመትን አምኖ ከመቀበል ይልቅ ወደ ሌሎች አገሮች ሞት ብዛት ወስዶ ቀመር መስጠት የመሪነትን ማንነት የሚያሳጣ ነው።” ሲል የጠቅላይ ሚንስትሩን ንጽጽር አጣጥሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው ዜጎችን ሰላም የማረጋገጥ ግዴታውን መወጣት አልቻለም ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ “መንግሥት ሰላምን የማስከበር ቀዳሚ ተግባሩ ነው። ነገር ግን ህዝብም የመረጠውን መንግስት የማድመጥ እና የማገዝ ቀዳሚ ተግባሩ ነው።” ሲሉ ተደምጠዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን የፓርላማ ውሎና ማብራሪያ ብዙዎች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች አንጻር ንጽጽሮችን በማቅረብ ጥቄዎችን ለማጣጣል እንጂ ተገቢ ምላሽ ለተገቢ ጥያቄ የሰጡባቸው አለመሆናቸው በስፋት አንስተዋል።

በመንግሥታቸው በየቀኑ በርካታ የጥቃት እቅዶች እንደሚከሽፉ ለምክር ቤቱ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች በመንግሥት ቸልተኝነት የተፈጸሙ ናቸው ማለት ተገቢ እንዳልሆነ አንስተዋል። ይሁን እንጂ በተለይ በወለጋ በተገደጋጋሚ የሚፈፀሙ ግድያዎች መንግሥት ከዜጎች መረጃ እየደረሰው ጭምር ተገቢውን ጥበቃና ክትትል ባለማድረጉ የተፈጸመ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ(ኢሰመጉ) እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ኹለቱ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋሞች በንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎችን በማስመልከት ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ባወጧቸው ሪፖርቶችና መግለጫዎች፣ መንግሥት ዜጎችን የመጠበቅ ኃላፊወነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ዜጎች ያለ አግባብ በታጣቂዎች መገደላቸውን በተደጋጋሚ ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው የታጣቂዎችን ጥቃት ለመከላከል የመከላከያ እና የደህንነት ተቋማት ካለፈው 20 እና ከዛ በላይ ዓመታት በተሻለ ቁመና እንዲደራጅ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። ለደህንንት ተቋማት ቅድሚየ መስጠታቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የደህንነት ተቋማት መጠናከር ቅድሚያ የተሰጠው የሽብር ቡድኖች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያላቸውን መሻት እና ፍላጎት ስለምናውቅ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ የደህንነት ተቋማት መጠናከር የዜጎችን ሞት ማስቀረት አልቻለም በሚል ከተለያዩ አካላት ትችት ይቀርባል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ሀሳብ “የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል ምንም ያክል ለማጠናከር ጥረት ያደረግን ቢሆንም፣ ለእያንዳንዱ ዜጋ ወታደር ልናቆም አንችልም። ስለዚህ የህዝብም ቀዳሚ ተግባር ሁኖ ተሰናስሎ አገርን መታደግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

በሌላ በኩል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከንጹሐን ግድያ ጋር አያይዘው ያነሱት የመረጃ ጦርነት ሲሆን፣ “በወለጋ አንድ ቀበሌ ውስጥ ሞት የሚካሄድ ከሆነ ብዙ አለም ያለ የመረጃ ተዋናዮች ያውቁታል፤ ጫፍ ጫፍ ይላሉ። የአለም ሚድያዎች ይዘግባሉ። እኛ ገና መረጃውን ሰምተን ወታደር ስናሯሩጥ ከኛ በላይ መረጃውን የሚያሰፋ ሃይል አለ። ይህ መረጃ ኃይል በስንዴ ላይ በግሪን ሌጋሲ ላይ ኢትዮጵያ ብትሰራ ስራም አላጣ እዛ አይገኝም” ሲሉ ተደምጠዋል። ኢትዮጵያ ላይ አሁን እየተካሄደ ያለው የግራጫ ጦርነት መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ማንም ኃይል በህዝብ ድምፅ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የመጣውን መንግስት በኃይል፣ በወረቀትና በዘፈን ጋጋታ ሊያፈርሰው አይችልም” ብለዋል።

በተደጋጋሚ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ላይ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ሰላም ማስጠበቅ ላይ ጥያቄ የሚቀርብበት አስተዳደራቸው፣ ችግሮቹን ለመፍታት አራት “የመ” ስትራቴጂ ያላቸውን አቅጫዎች እንደሚከተል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራያ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአራቱ “የመ” ስትራቴጂ ያሏቸው መከላከል (Prevent)፣ መከታተል (Pursue)፣ መጠበቅ (Protect) እና መዘጋጀት (Prepare) ሲሆኑ፣ መንግሥታቸው የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት አራቱን ስትራቴጂዎች ነድፎ እየሰራ ነው ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here