አሐዱ ባንክ ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ ሥራ እንደሚገባ አስታወቀ

0
1307

ታኅሳስ 30 ቀን 2012 አንድ ብሎ ጀምሮ፣ 10 ሺሕ የሚደርሱ ባለአክስዮኖችን ያሰባሰበውና በ564 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል የተመሠረተው አሐዱ ባንክ፣ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ሐምሌ 9 ቀን 2014 ወደ ሥራ እንደሚገባ አስታውቋል።

ባንኩ ዛሬ ሰኔ 30 ቀን 2014 በሰጠው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት የተደራሽነት ውስንነት፣ እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥና ቴክኖሎጂ ክፍተት መኖሩንም ባንኩ ጠቁሟል። ከዚህ አንፃርም የተሻለ የባንክ አደረጃጀት ይዞ ወደ ገበያ የሚገባ መሆኑን አስታውቋል።

በባንኮች ካለው አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ 50 በመቶ እንዲሁም ለተበዳሪዎች ከተሰራጨ የብድር ክምችት 3/4ኛ የሚሆነው በአዲስ አበባ እና አካባቢው ካለ አስቀማጭና ደንበኛ የሚገኝ እንደሆነ ባንኩ በመግለጫው አንስቷል። አሐዱ ባንክ ይህንን ክፍተት ለመሙላትና በገጠር ላለው ማኅበረሰብም አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚሠራ እንደሆነ ተገልጿል።

ባንኩ በተጨማሪም የብድር አቅርቦት፣ የወኪል ባንክ አገልግሎት፣ የገጠር ባንክ አገልግሎት ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ ከማድረስ ጎን ለጎን፣ ወረቀት አልባ አሠራርን ከማጠናከር አንፃር አዲስና የተሻሉ አካሄዶችን እንደሚያስተዋውቅ በመግለጫው ጠቅሷል።

‹አንድ ቅርንጫፍ ለአንድ ልጅ› የሚል መርህም እንዳለው በመግለጫው ተነስቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አንተነህ ሰብስቤ እንደገለፁት፤ ባንኩ ከተለያዩ የሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅቶች ጋር እንደሚሠራ ጠቅሰዋል። በዚህም መሠረት አንድ ቅርንጫፍ በተከፈተ ቁጥር ለአንድ ወላጅ አልባ ልጅ ኹሉንም ወጪ በመሸፈን እንደሚያሳድግ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ባንኩ ወደ ሥራ ከሚገባበት ዕለት ዋዜማ ባሉት ቀናት የተለያዩ መሰናዶዎች እንዳሉት አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

ከዚህም መካከል የደም ልገሳ አንደኛ ሲሆን፤ ለተስፋ የካንሰር ሕሙማን መርጃ፣ ለጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን መርጃ፣ እንዲሁም ለስለእናት የበጎ አድራጎት ድርጅት የተለያዩ ስጦታና ድጋፎችን እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ለቅዱስ ላሊበላ ገዳም እድሳት ሥራም ድጋፍ እንደሚደረግ ተጠቅሷል።

ባንኩ የንግድ ምልክት ወይም ብራንዱ በአዲስ መልክ የተሠራ ሲሆን፣ ምልክቱንም ይፋ አድርጓል። አሐዱ ባንክ ከምርቃቱ ዕለት ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ድረስ በተከታታይ ቅርጫፎቹን 50 ለማድረስ ማቀዱም ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here