የነዳጅ እጥረትና የታለመው ድጎማ ፈተና

0
1947

የነዳጅ አቅርቦት እጥረትና ዋጋ መናር ለኢትዮጵያ ፈተና እየሆነ መምጣቱን የሚያሳዩ ምልክቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ጎልተው እየተስተዋሉ ነው። ባለፉት ኹለት ሳምንታት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የነዳጅ አቅርቦት እጥረት መከሰቱን ተከለትሎ፣ የትራንስፖርት መስተጓጎል ተከስቷል። በዚህም የሕዝብ ትራንስፖርት የሚጠቀሙ ዜጎች በትራንስፖርት እጥረት ለእንግልት ተዳርገዋል።

በተለይ ባለፉት ኹለት ሳምንታት የተከሰተውን የነዳጅ አቅርቦት እጥረት የተከተለው የትራንስፖርት መስተጓጎል ዜጎችን ያማረረ መሆኑን አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ታክሲ መጫኛና ማውረጃዎች ተገኝታ ታዝባለች። በአዲስ አበባ ባለፉት ኹለት ሳምንታት የነዳጅ እጥረት መከሰቱን ተከትሎ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ለማግኘት ለሰዓታት ሰልፍ ላይ ለመቆየት መገደዳቸውን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

ነዳጅ ለማግኘት ለሰዓታት በነዳጅ ማደያዎች ሰልፍ የሚጠባበቁ ተሽከርካሪዎች ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሌሎች ከተሞች የታዩ ቢሆንም፣ በአዲስ አበባ የታየው የተሽከርካሪዎች ሰልፍ ለተከታታይ ቀናት ጎልቶ ነበር። አዲስ ማለዳ በአዲሰ አበባ ከተማ ባደረገችው ምልከታ፣ የነዳጅ እጥረት የፈጠረው የትራንስፖርት መስተጓጎል ቀላል የማይባል የጊዜ ብክነትና እንግልት ያስከተለ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ በተለይ ምሽት ላይ ከፍተኛ የአሽከርካሪዎች ሰልፍ ከመኖሩ በላይ፣ ተመጣጣኝ የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖሩን አዲስ ማለዳ በተለይ በአራት ኪሎ ተገኝታ የምሽቱን ትራንስፖርት ሁኔታ ተመልክታለች። ይህንኑ ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው ለመግባት ምሽቱን፣ በእግራቸው ሲጓዙ አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

የትራንስፖርት እጥረቱን ተከትሎ አሽከርካሪዎች ትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን በተለይ ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላ ከመደበኛው ታሪፍ እጥፍና ከዚያ በላይ ሲያስከፍሉ እንደነበር አዲስ ማለዳ ተረድታለች። ምንም እንኳን ምሽት ላይ ከሥራ ሰዓት በኋላ የትራንስፖርት እጥረቱ ሰፊ ቢሆንም፣ ከምሽቱ መጨናነቅ ይልቅ ጠዋት ላይ በአንጻራዊነት ያነሰ የትራንስፖርት አጥረት መኖሩን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

አሽከርካሪዎች ነዳጅ ለማግኘት ለሰዓታት ወረፋ ለመጠበቅ መገደዳቸውን ተከትሎ፣ የተፈጠረው የትራንስፖርት መስተጓጎል ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልል ከተሞች ተከስቷል። ከአዲስ አበባ ውጪ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት የተከሰተው ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሲሆን፣ በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር የነዳጅ እጥረቱን እንዳባባሰው አዲስ ማለዳ ከአሶሳ ነዋሪዎች ሰምታለች።

ወትሮውንም በጸጥታ ችግር ምክንያት የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በነበረባት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው አሶሳ ነዋሪ የሆኑ ምንጮች እንደተናገሩት፣ ችግሩ ቆየት ያለ ቢሆንም አሁን ላይ የተባበሰ መሆኑን ጠቁመዋል። አማራ ክልልም የነዳጅ እጥረት መከሰቱን ተከትሎ የክልሉ መንግሥት ከመጠባበቂያ ነዳጅ ለመጠቀም መገደዱን አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ አሽከርካሪዎች ነዳጅ ለመቅዳት ለሰዓታት ረጅም ሰልፍ ለመጠበቅ ከተገደዱ ቀናት ተቆጥረዋል። መንግሥት ለነዳጅ የማወጣው ገንዘብ ከአቅሜ በላይ እየሆነ ነው ማለቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ነዳጅ መግዣ ዋጋ በሚጨምርበት ጊዜ የሚያስገባውን የነዳጅ መጠን የመቀነስ አዝማሚያዎች እንደሚያጋጥሙ ይጠበቃል።

ከሰሞኑ የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍ ችግሩ ካጋጠመ በኋላ መንግሥት በቀን የማስገባውን የነዳጅ መጠን ጨምሬያለው ቢልም፣ ያንን ሊከተል የሚችለው ለውጥ እስከ አሁን አልታየም።

በኢትዮጵያ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዓለም ዐቀፍ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየትና በጸጥታ ችግሮች የሚስተጓጎል የነዳጅ ማጓጓዝ ሂደት መሆኑ ይነገራል።

ከሰሞኑ ለተከሰተው የነዳጅ እጥረት መባባስ ከጂቡቲ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ነዳጅ መድረስ ካለባቸው ቦታ ውጪ መውሰድና የነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ትራንስፖርት መዘግየት ምክንያት መሆኑን የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለሥልጣን እወቁልን ብሏል።

ከኹለት ሳምንት በፊት በአፋር ክልል ነዳጅ ጭነው ተደብቀው የነበሩ 200 ቦቴዎች እንዳሉና ከዛም ውስጥ የተወሰኑት ትዕዛዝ ባለመቀበላቸው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ማዋላቸውን መንግሥት ይፋ አድርጎ ነበር። አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በበኩሉ 10 ነዳጅ ጫኝ ቦቴዎችን ከሕግ ውጪ ሲንቀሳቀሱ እግኝቻቸዋለሁ በማለት መውረሱን አስታውቋል።

ባለሥልጣኑ እንደሚለው ከሆነ የነዳጅ እጥረት የሚከሰተው፣ በነዳጅ ማመላለሻ መስመሮች አካባቢ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች፣ ተሽከርካሪዎች አቅርቦታቸውን በሚፈለጉበት ቦታ ዘግይተው ማድረስ፣ ነዳጅ መድረስ ካለባቸው ቦታዎች ውጪ ወደ ሌሎች ቦታዎች መሸጋገር እንዲሁም አከፋፋዮች ነዳጅ የመደበቅ ሁኔታ ሲያሳዩ ነው ተብሏል።

የታለመው ድጎማ የፈጠረው ስጋት
የኢትዮጵያ መንግሥት የነዳጅ ምርቶችን የማቅረብ እና የመሸጫ ዋጋ የመተመን ሥልጣን ያለው ሲሆን፣ በዚህም የነዳጅ ምርቶችን የመሸጫ ዋጋ በየወሩ ይከልሳል። የነዳጅ ዋጋ በየወሩ እንደየሁኔታው የሚከለስ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ወራት ከአውሮፕላን ነዳጅ ውጭ ያሉት የነዳጅ ምርቶች ባሉበት ዋጋ እረግተው እንዲቆዩ ሲደረግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

ይሁን እንጂ መንግሥት ለነዳጅ ድጎማ በየዓመቱ የማወጣው ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከአቅሜ በላይ እየሆነ ነው በሚል፣ የታለመ የነዳጅ ድጎማ ከሰኔ 29/2014 ጀምሮ ተግባራዊ አድርጓል። ተግባራዊ የተደረገው የነዳጅ ድጎማ ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች የሚሰጥ ሲሆን፣ 160 ሺሕ ገደማ ተሽከርካሪዎች በድጎማው ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።

በታለመ የነዳጅ ድጎማው መሠረት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ዕለታዊ የነዳጅ ፍጆታ ተመድቦላቸዋል። በዚህም ለባለ ሦስት እግር (ባጃጅ) በቀን ሰባት ሊትር፣ ለባለ ኮድ አንድ እና ሦስት የከተማ ሚኒባስ ታክሲዎች በቀን 25 ሊትር፣ ለአነስተኛ አገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በቀን 65 ሊትር፣ ለመለስተኛ አገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በቀን 94 ሊትር፣ ለከተማ ሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ በቀን 102 ሊትር፣ ለፐብሊክ አውቶብስ 25 ሊትርና ለአገር አቋራጭ አውቶብስ 65 ሊትር ዕለታዊ ፍጆታ ተመድቦላቸዋል።

የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ዓመታዊ የነዳጅ ፍጆታ ተቀራራቢ የሊትር መጠን ግምት በጥናት መለየቱና እያንዳንዱ ተሽከርካሪ የሚጠቀመውን የነዳጅ መጠን ያገናዘበ ስሌት በመቀመጡ፣ ተሽከርካሪዎቹ ያለ ብክነት የታለመ የነዳጅ ድጎማን ጥቅም ላይ እንዲያውሉ የሚያግዝ ነው ተብሏል።

በታለመው የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ተብለው የተመደቡ ብቻ በተቀመጠላቸው ዕለታዊ የነዳጅ ፍጆታ ዝርዝር መሠረት ዕለታዊ የነዳጅ መጠን ማግኘት እንደሚችሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

የታለመ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለዩ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ለመሆን አስፈላጊ መረጃዎችን በመስጠት በኢትዮ ቴሌኮም የሽያጭ ማእከላት በኩል ተመዝግበው አገልግሎት እያገኙ ነው ተብሏል። የነዳጅ ድጎማን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል፣ በቴሌ ብር አገልግሎቱን ለማግኘት የተመዘገቡ ከ160 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች ከሰኔ 29/2014 ጀምሮ መተግበሪያውን በመጠቀም ይስተናገዳሉ።

በታለመ የነዳጅ ድጎማው መሠረት የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ ተደርጓል። በተደረገው ጭማሪ መሠረት፣ ቤንዚን በሊትር 47 ብር ከ83 ሳንቲም፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር 49 ብር ከ02 ሳንቲም፣ ኬሮሲን በሊትር 49 ብር ከ02 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ በሊትር 53 ብር ከ10 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ በሊትር 52 ብር ከ37 ሳንቲም፣ የአውሮፕላን ነዳጅ በሊትር 98 ብር ከ83 ሳንቲም ነው።

ከላይ የተገለጸው የቤንዚን፣ የኬሮሲን እና የነጭ ጋዝ ዋጋ ላይ ለሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ወይም የታለመ ድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች 15 በመቶ በመንግሥት እንዲደጎሙና ቀሪውን 10 በመቶ እንዲከፍሉ በማድረግ የድጎማ መጠኑን በቴሌ ብር ተመላሽ እንዲሆንላቸው ይደረጋል ተብሏል።

መንግሥት ይፋ ባደረገው የታለመ የነዳጅ ድጎማ ያልተካተቱ ተሽከርካሪዎች፣ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ነዳጅ ይገዛሉ ተብሏል።

የነዳጅ እጥረት ችግር እየሆነ በመጣበት ሁኔታ፣ ተደርቦ የመጣው መንግሥት ይፋ ያደረገው የታለመ የነዳጅ ድጎማን መንግሥት በበጎ ሁኔታ ቢያየውም፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የኑሮ ውድነት አባባሽ ምክንያት እንዳይሆን ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሌሎች ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ በመጣው የዋጋ ግሽበት ላይ ሌላ አቀጣጣይ ምክንያት እንደሚሆን በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ክፍሉ ደገፉ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።

“የነዳጅ ዋጋ መጨመር ዋነኛ የዋጋ ግሽበት አቀጣጣይ ነው” የሚሉት ክፍሉ፣ መንግሥት የዋጋ ጭማሪውን ካለው ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር ያለበትን ጫና ለመቀነስ ያደረገው ቢሆንም፣ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል አለመሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ገበያ የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየወሩ የሚያወጣው ሪፖርት ያመላክታል። በኢትዮጵያ የሚታየው የዋጋ ግሽበት በአንድ ምርት ላይ የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ ሲደረግ የሌሎች ምርቶች መሸጫ ዋጋ አብሮ ማደጉ የተለመደ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ በኢትዮጵያ የሚታየው የዋጋ ግሽበት በአንድ ምርት የዋጋ መጨመር ላይ ሰበብ አድርጎ የሚከስት መሆኑን ብዙ ጊዜ ሲገልጹ ይደመጣል። የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚነካቸው ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ አስገዳጅ እንደሚሆንም ስጋታቸውን አስቀድመው ሲገልጹ ነበር።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ መሠረታዊ የሆነውን የነዳጅ ድጎማን ማንሳት ባለው የኑሮ ውድነት ላይ “እየነደደ ባለ እሳት ላይ ነዳጅ ማርከፍከፍ” እንዳይሆን ስጋት አላቸው።

የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተብለው ድጎማ ውስጥ ከተካተቱት ተሽከርካሪዎች ውጪ የሚገኙት፣ በተለይ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት የሚሰጡት የአገልግሎት ክፍያ ከጨመረ በሚያጓጉዙት ምርት ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት አስገዳጅ መሆኑን ባለሙያዎች ያነሳሉ።

ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች የትራንስፖርት ዋጋ ሲጨምር በትራንስፖርት ተጓጉዘው ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች እንደመሆናቸው፣ መሸጫ ዋጋቸው መጨመሩ የማይቀር መሆኑን አስቀድመው ባለሙያዎች ሲገልጹ ነበር።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here