17 ሰዎች በወባ በሽታ መሞታቸው ተሰማ

0
1260

በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉደቱ አርጆ ወረዳ ሶልኬ ተንከራ ቀበሌ መንደር 42 ስር በወባ በሽታ ሰዎች እየሞቱ መሆኑን በቦታው የሚገኙ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት ባለፉት ኹለት ሳምንታት ውስጥ 17 ሰዎች በበሽታው ምክንያት መሞታቸውን ነው። በተከሰተው የወባ በሽታ ሕይወታቸው ካለፈው 17 ሰዎች መካከልም ሦስቱ ጨቅላ ሕጻናት ናቸው ተብሏል።

ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ሰዎች የበሽታው ሰለባ መሆናቸውን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ ወደ ጤና ጣቢያ ሂዶ ለመታከም የኦነግ ሸኔ ታጣቂ እገዳ እንዳደረገባቸው ነው የገለጹት።

ከዚህ ቀደም ጤና ሚኒስቴር የወባ በሽታ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ከዚህ በፊት መግለጫ መስጠቱ የሚታወስ ነው።

አዲስ ማለዳ በአርጆ ወረዳ በሰዎች ላይ ሞት እያስከተለ ነው የተባለውን የወባ በሽታ መነሻ በማድረግ፣ በሽታው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ምላሽ ለማግኘት ብትሞክርም ጤና ሚኒስቴር ምላሽ አልሰጠም።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኝነቱን የከለከለው በሰጠው ትእዛዝ፣ መረጃን ለማግኘት በሚጠይቀው ደብዳቤ መሠረት ደብዳቤው ከደረሰው በኋላ ኃላፊዎቹ ስብሰባ ላይ ናቸው በሚል ሰበብ ነው።

በአንጻሩ በወለጋ የተለያዩ ስፍራዎች የተከሰተው የወባ በሽታ በባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጠውም ነዋሪዎቹ አሳስበዋል። ሰሞኑን በወባ በሽታ እየተጠቃን ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ ታጣቂ ቡድኑ በተለይም ዘረፋ መፈጸሙን እንደቀጠለበትም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ሰዎች በየጊዜው እንደሚገደሉ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ዝርፊያን በተመለከተ ደግሞ ሰሞኑን ከ180 በላይ ከብቶች በታጣቂ ቡድኑ ተወስደዋልም ነው የተባለው።

በጊንቢ ወረዳ የደረሰውን ጭፍጨፋ ያነሱት ነዋሪዎቹ፤ ከወባ በሽታው ባሻገር በኦነግ እና በቤኒ ታጣቂዎች ከበባ ውስጥ መሆናቸውን አንስተዋል። አያይዘውም በሌሎች ሥፍራዎች የደረሰው የጭፍጨፋ እጣ ፋንታ ሳይደርስባቸው መንግሥት እንዲደርስላቸው አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ወደ ጤና ጣቢያ አቅንተው አገልግሎት እንዳያገኙ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የተከለከሉ በቄለም ወለጋ የሚገኙ ነፍሰ ጡር እናቶች በወሊድ ምክንያት ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአዲስ ማለዳ ታማኝ ምንጮች ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ በተናገሩት መሠረት፣ በቄለም ወለጋ የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ወደ ወደ ጤና ጣቢያ አቅንተው ለመታከም እገዳ የተጣለባቸው ሲሆን፤ በዚህም ኹለት እናቶች በወሊድ ምክንያት መሞታቸውን ነው የጠቆሙት።

በሌላ በኩል ከዚህ በፊት በጊንቢ ወረዳ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 1 ሺሕ 600 የሚሆኑ ንጹሐን ሰዎች መጨፍጨፋቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ሰኔ 27/2014 ደግሞ 380 የሚሆኑ ንጹሐን ዜጎች መጨፍጨፋቸውን በቦታው ያሉ ታማኝ ምንጮች ጠቁመዋል።

የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ፤ ጊንቢ ወረዳ ለምለም ቀበሌ 328 ሰዎች በታጣታቂዎች ተገድለው እንደተገኙና በአጠቃላይ ግን የሟቾቹ ቁጥር 380 ይደርሳል።

መንግሥት በበኩሉ ኦነግ ሸኔ ዳግም በፈጸመው ጥቃት ከ330 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የገለጸ ሲሆን፤ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ግን ሟቾቹ 380 መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከተጨፈጨፉት መካከል “80 የሚሆኑት ሰዎች በአንድ አካባቢ ሞተው ተገኝተዋል” ያሉት ነዋሪዎቹ፣ አስከሬናቸውን ለመቅበር ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

በሌላ በኩል 97 ወጣቶች ሰሞኑን በታጣቂዎች ታግተው ወደ ቴሌ ጫካ እንደተወሰዱና እስከ አሁን ያሉበት ሁኔታ እንደማይታወቅ ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here