ወላጆቻቸው ግንባር ላይ ያሉና በግል ትምህርት ቤት የሚማሩ ልጆች ትምህርታቸውን ያለ ክፍያ እንዲማሩ የድጋፍ ደብዳቤ ተፅፎላቸው ዓመቱን ሲማሩ ቢቆዩም፣ ፈተና ከተፈተኑ በኋላ “ብር ካልከፈላችሁ ውጤት አይሰጣችሁም” መባላቸው ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ወላጆች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ልጆቻቸው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 05 ቀበሌ በሚገኘው አቃቂ ቃለ ሕይወት 1ኛ እና 2ኛ ትምህርት ቤት የሚማሩ ወላጆች፤ ትምህርት ቤቱ የድጋፍ ደብዳቤውን ተቀብሎ እያስተማረ ከቆየ በኋላ ለተማሪዎቹ ውጤት ለመስጠት ከልክሏል ብለዋል።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የተማሪ ወላጅ እናት፣ ብር አልከፈላችሁም ተብለው ልጃቸው ከትምህርት ቤት መባረሯን ለአዲስ ማለዳ አሳውቀዋል። ኹለት ልጆቻቸውን በትምህርት ቤቱ እንደሚያስተምሩ የጠቀሱት ቅሬታ አቅራቢዋ፤ ባለቤታቸው ግንባር ላይ መሆናቸውን ተከትሎ ባቀረቡት የድጋፍ ደብዳቤ አንድ ልጃቸውን በነጻ እንደሚያስተምሩ ቃል ቢገባላቸውም፣ መጨረሻ ላይ ግን ውጤት ተከልክለዋል።
‹‹ባለቤቴ በሕልውና ዘመቻው ግንባር ላይ ስለሆነ ኹለት ልጆቼን በክፍያ ማስተማር አልቻልኩም›› ያሉት ቅሬታ አቅራቢዋ እናት፤ ‹ኬጂ ኹለት› የደረሰች ታዳጊ ልጃቸው በመጀመሪያ ካልከፈልሽ ፈተና አትፈተኚም ተብላ እንደነበር አስታውሰዋል። ነገር ግን፣ ጉዳዩን ለክፍለ ከተማ አሳውቀው፣ ለአንድ ልጃቸው እንዲከፍሉና ለኹለተኛዋ ልጃቸው ግን እንደማይከፍሉ ስምምነት ላይ ተደርሶ ልጆቻቸው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።
አባታቸው በግንባር ላይ ለሚገኘው ለኹለቱም ልጆች የትምህርት ክፍያ የምከፍል ከሆነ፤ በዓመት 24 ሺሕ 400 ብር ያስፈልገኛል ያሉት እናትየዋ፤ አስተያየት ካልተደረገላቸው ልጆቻቸውን ለማስተማር አቅም እንደማያገኙ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ቅሬታ አቅራቢዋ፣ የድጋፍ ቃሉን አስተባብሎ ሕጻናትን ከሌሎች ተማሪዎች በመለየት ውጤት አትቀበይም ማለት ተማሪን ለማብቃት ዓላማ ይዞ ከተነሳ ትምህርት ቤት አይጠበቅም ሲሉ ወቅሰዋል። ተማሪዋ ልጃቸው በመጀመሪያ በነጻ እንድትማር ነበር ድብዳቤ የተጻፈላት። ነገር ግን ትምህርት ቤቱ ቃሉን በማጠፉ የታዳጊዋ እናት የቻሉትን ከፍለው ብር ስለጎደላቸው ነው ውጤት የተከለከለችው። ውጤት አይሰጥሽም የተባለችው ተማሪ ያልተከፈለላት የሦስት ወር ክፍያ ሲሆን፤ ይኸውም ሦስት ሺሕ 60 ብር ነበር።
ቢሆንም ትምህርት ቤቱ ይህን እንኳ አስተያየት በማድረግ ፈንታ የታዳጊዋን ሥነ ልቦና በሚነካ መልኩ ውጤት ሳይሰጥ፣ ከእናቷ ጋር ከግቢው እንዲወጡ አድርጓል ነው የተባለው። ታዳጊዋ እንደ ጓደኞቿ ውጤት ሳይሰጣት ሲቀር መጥፎ ስሜት ስለተሰማት በመጨረሻም ሌሎች ቤተሰቦቿ ክፍያውን ከፍለውላት ውጤት እንደተሰጣት የተማሪዋ እናት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በግንባር የሚገኙት የተማሪዋ አባት በበኩላቸው በግንባር እንደሚገኙ አሳውቀው፤ ‹‹ትምህርት ቤቱ ከመከላከያ ድጋፍ ተቀብሎ ልጄን ሲያስተምር ቆይቷል። መጀመሪያ ከመከላከያ የመጣውን ደብዳቤ አልቀበልም ማለት ሲችሉ፤ አሁን ከተፈተኑ በኋላ ውጤት አልሰጥም ማለት ያሳፍራል። የዓመት ክፍያ ከየት አምጥቼ ነው የምከፍለው። እኔ በምሽግ ውስጥ ከጠላት ጋር ተፋጥጬ እገኛለሁ። ሕጻን ማሸማቀቅም ተገቢ አይደለም›› ብለዋል።
የተማሪዋ ወላጅ አባት በውትድርና ያለ ሰው የሚከፈለው ገንዘብ አናሳ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ልጃቸው አሁን በዘመድ እርዳታ የትምህርት ክፍያ ተሟልቶላት ውጤት ቢሰጣትም ለቀጣዩ ሊታሰብበት ይገባል ነው ያሉት።
ጉዳዩን በማስመልከት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአቃቂ ቃለሕይወት 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ዘውዴ አበራ፣ ደብዳቤውን ቢቀበሉም ክፍያውን ካልከፈሉ የተማሪ ውጤት እንደማይሰጡ ተናግረዋል።
አባቶቻቸው ግንባር ላይ ያሉ ተማሪዎችም ቢሆኑ የሚከፍሉበትን የጊዜ ገደብ ይሰጣሉ እንጂ፣ ክፍያውን ተማሪዎቹ ካልከፈሉ ውጤት እንደማይሰጡ ነው የተገለጸው። ርዕሰ መምህሩ የተማሪ ወላጆች ያቀረቡትን የድጋፍ ደብዳቤ መቀበላቸውን ቢያምኑም፣ ብር ሳይከፈል ውጤት መስጠት ግን “አግባብነት የለውም” ብለዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014


