ለ5ኛ ጊዜ የተራዘመው 4ኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ

0
2876

በ2014 የግንቦት መጨረሻ ወር ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሳይካሄድ ቀርቷል። የሕዝብና ቤት ቆጠራ በተያዘለት እቅድ የመከናወን እድሉም በተደጋጋሚ እየተነጠቀ ይገኛል።

ቆጠራውን በበላይነት የሚመራውና ተጠሪነቱን ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ያደረገ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር የሚመራ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን መቋቋሙ የሚታወስ ነው። ሆኖም የሕዝብና ቤት ቆጠራው ከ2010 እስከ 2013 ባሉት ዓመታት አራት ጊዜ የተራዘመ ሲሆን፤ በ2014 መሰል እድል ገጥሞት ነው ለአምስተኛ ጊዜ ሳይካሄድ የቀረው።

በመሆኑም ቆጠራው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ሰንሰለቱን ጠብቆ አለመከናወኑ፤ መሠረታቸው የሕዝብ ቁጥር የሆነ እንደ በጀት ምደባ፤ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም ሌሎች የፖሊሲ ዝግጅቶች ትግበራ ላይ ፈተና መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው።

ሕዝብና ቤት ቆጠራ መቼ ተጀመረ?
የማእከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው፤ የሕዝብ ቆጠራ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገው በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር በ1976 ነው። ኹለተኛው 1987 እንዲሁም ሦስተኛው ደግሞ በ1999 ተጀምሮ በ2000 የተጠናቀቀ ነው። በመሆኑም፣ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ እስከ አሁን የሕዝብና ቤት ቆጠራ የተከናወነው ለሦስት ጊዜ ሲሆን፤ ቆጠራው አሁን ብቻ ሳይሆን ተካሄደበት በተባለው ወቅት የመራዘም መሰናክል ይገጥመው እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ።

ለአብነትም ሦስተኛው የሕዝብ ቤት ቆጠራ በመርሃ ግብሩ መሠረት ይካሄዳል ተብሎ የነበረው በ1997 ሲሆን፤ ኹለት ዓመት በመጨመር ወደ 1999 እንዲሸጋገር ተደርጓል። በዛም መጠናቀቅ ሳይችል ቀርቶ እስከ 2000 ኅዳር ወር ድረስ ዘልቆ ነበር።

እስከ አሁን በኢትዮጵያ በተደረጉት ሦስት የሕዝብና ቤት ቆጠራዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በ1976 ኤርትራን ጨምሮ በተካሄደው የሕዝብ ቆጠራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 46 ሚሊዮን እንደሆነ ተመዝግቧል። ለኹለተኛ ጊዜ በ1987 በተካሄደው ቆጠራ ደግሞ የሕዝብ ብዛት 53 ሚሊዮን እንዲሁም በ1999/2000 ለሦስተኛ ጊዜ በተካሄደው የሕዝብ ቆጠራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 75 ሚሊዮን ሆኖ ተመዝግቦ ነበር።

በኢትዮጵያ ለሦስት ጊዜያት የተከናወኑት እነዚህ የሕዝብና ቤት ቆጠራዎች ብዙ እንከን እንዳለባቸው ቅሬታ ይነሳባቸው ነበር። አሁን ላይ ግን ከዛም ብሎ፣ የሚራዘምበት ጊዜም እየጨመረ፤ የሚከናወንበት ጊዜም ከዛሬ ነገ ሲባል እንደ ሰማይ እየራቀ መጥቷል። ታዲያ በርካቶች ምነው ቆጠራው ግን መራዘም በዛበት የሚል ጥያቄያቸውን በግርምት እያነሱ ይገኛሉ።

ቆጠራው ለምን ተራዘመ?
የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየ10 ዓመቱ መካሄድ እንዳለበት የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ምዕራፍ 11 በአንቀጽ 103 በይፋ አስቀምጧል። ሆኖም ግን ሕዝብና ቆጠራው ወቅቱን ጠብቆ እየተካሄደ አይደለም። ቆጠራው በሕጉ በጸደቀው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ለአራተኛ ጊዜ ይካሄዳል ተብሎ እቅድ ከተያዘለት ከ2010 ጀምሮ ተደጋጋሚ መቆራረጥ ገጥሞታል።

በ1997 እንዲካሄድ እቅድ ተይዞለት የነበረው ሕዝብና ቤት ቆጠራ በምርጫ ምክንያት እንዲራዘም ተደርጎ ወደ 1999 ተሸጋግሮ ነበር። ቆጠራው ከኹለት ዓመት ቆይታ በኋላ በ1999 መከናወን ቢጀምርም፣ ሲንዛዛ ቆይቶ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች የተጠናቀቀው 2000 ላይ እንደነበር አይዘነጋም።

በ1997 የነበረው የቆጠራ መርሃ ግብር ለኹለት ዓመት ተራዝሞ ወደ 1999 መሸጋገሩ ሳያንስ 2000ን መዝለቁ ሌላ የጊዜ መዛባትንም ፈጥሯል። ይህም በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በ2009 መካሄድ የነበረበትን አራተኛውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ወደ 2010 እንዲተላለፍ አድርጓል። ይህ በመሆኑም፤ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽኑ አራተኛውን የቆጠራ መርሃ ግብር ኅዳር 10/2010 እንደሚሆን በይፋ አጸድቆ ነበር።

ይሁን እንጂ ያውም በ2010 ይካሄዳል ተብሎ የነበረው አራተኛው የሕዝብ ቆጠራ መጋቢት 29/2011 ይካሄዳል መባሉን የማእከላዊ ስታትሰቲክስ ኤጀንሲ አስታውቆ ነበር። የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽኑ በወቅቱ እንደገለጸው ከሆነ፤ ለቆጠራው መራዘም በኢትዮጵያ አንዳንድ ሥፍራዎች የፖለቲካ አለመረጋጋት መከሰቱን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው፤ የሰላም መደፍረስና የአለመረጋጋት መንገሥ ምክንያት ናቸው ሲል አስታውቋል።

ታዲያ አራተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በ2009 መካሄድ እያለበት ከዓመት ወደ ዓመት ሲሸጋገር ቆይቶ፣ በ2014 የግንቦት መጨረሻ ወር ይካሄዳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ሆኖም ‹እንደተለመደው› መራዘም አልቀረለትም፤ ለአምስተኛ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጓል።

ለሕዝብና ቤት ቆጠራው ከዓመት ወደ ዓመት መሸጋገር ባለድርሻ አካላት የተለያዩ ጉዳዮችን በመንስኤነት ያንሱ እንጂ፣ ሌሎች የፖለቲካ ምሁራን ግን ድርጊቱ ሌላ በግለጽ ያልተጠቀሰ ምክንያት ሳይኖረው እንደማይቀር ማብራሪያ ይሰጣሉ።

በምርጫ ከማሳበብ ጀምሮ በሰላም መደፍርስና መሰል በሚሉ ምክንያቶች ቆጠራው አይካሄድም ማለት በራሱ ፖለቲካዊ ውስጠ ወይራ አለው የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ ሱራፌል አያሌው ናቸው። ሱራፌል ከዚህ ቀደም ቆጠራው በምርጫ ምክንያት እንዲራዘም መደረጉን አስታውሰው፣ በመሠረቱ ከምርጫ ይልቅ መቅደም የነበረበት ሕዝብ ቆጠራ ነው ብለዋል።

ይህ መሆን የነበረበትም ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ በቅድሚያ በየሥፍራው ያለውን የሕዝቡን ቁጠር ማወቅን ስለሚጠይቅ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል። ምርጫን ተከትሎ ቆጠራው እንዳይካሄድ ምክንያት ሆኗል የተባለው የሰላም መደፍረስም፣ ቆጠራው እንዲካሄድ ቢፈለግ ኑሮ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ትከተላለች ከተባለ በሕጉ መሠረት በሕገ ወጦች ላይ ቆንጠጥ ያለ እርምጃ ወስዶ ጦርነቱን መቋጨት ይቻል ነበር ነው ያሉት።

በመሆኑም፤ ለሰላም መደፍረሱ እልባት መስጠት ሲገባ ለሕዝብና ቤት ቆጠራ መሰናክል ሆኗል እያሉ መቀጠል በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲከ ረገድ ለአገርም ለሕዝብም ፋዳ የለውም፤ ብለዋል ሱራፌል ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ።

የቆጠራው ተግባራዊ አለመሆንና ጉዳቱ
በሕዝብና ቤት ቆጠራ ዙሪያ የተጻፉ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በማኅበራዊ፤ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች በኩል የሚያስገኘው ጥቅም የጎላ ነው። በአንጻሩ ቆጠራ አለመካሄዱ በኢኮኖሚያዊ፤ በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ረገድ ጉዳት እንደሚያስለትልም የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።

ይኸው የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ተግባራዊ አለመሆኑ የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል የሚባል አለመሆኑ እሙን ነው። አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝብና ቤት ቆጠራ መራዘሙን ተከትሎ፤ ይህም በተለይም መንግሥት በየክልሉ በሚያከፋፍለው በጀት ከእቅድ ውጭና ተመጣጣኝነት የጎደለው የመሆን እድሉ የሰፋ እንደሚሆን በጉዳዩ ላይ አስያየት የሚሰጡ ምሁራን ይገልጻሉ።

የሕዝብና ቤት ቆጠራ አንደኛውና ዋነኛው ረቡ መንግሥት በአንድ ሥፋራ በሚኖረው የሕዝብ ብዛት ተመርኩዞ አስፈላጊውን በጀት ፍትኃዊ በሆነ ሂደት እንዲያከፋፍልና ማኅበረሰቡ በሚያስፈልገው አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን መሆኑ ይታመናል።

ዜጎች የመሠረተ ልማት አገልግሎት ተደራሽነትን የሚያገኙት፣ መንግሥት ብዛታቸውን መሠረት በማድረግ በሚያከፋፍላቸው በጀት ነው።
ለአብነትም የጤና፣ የትምህርት እና የንግድ ተቋማት፣ የውሃ መሠረተ ልማት፤ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ብሎም ሌሎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህም መንግሥት በሚበጅተው በጀት ተግባራዊ የሚደረጉ ሲሆን፤ ለዚህም የሕዝብ ቁጥር መታወቁ የግድ ይላል። ሆኖም ግን ሕዝብና ቤት ቆጠራው እየተራዘመ በመሆኑ የመንግሥት በጀት ዕቅድ እንዲሁ በዘፈቀደ ሲተገበር ይስተዋላል እየተባለ ነው።

ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጦስ
የሕዝብና ቤት ቆጠራ አለማካሄድ በኢኮኖሚያዊ ረገድ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም የሚሉት የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ ብሩህተስፋ (ዶ/ር) ናቸው።

እቅድ ለማቀድ በጀት ለማከፋፈል፤ ቁጥር ከጨመረ የሕዝብ ተወካይ ለመደልደል የሕዝብ ቁጥር መታወቅ ግድ ቢልም፤ ይህ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑ ትችትን እያስነሳ ይገኛል።

በጀት ለመበጀት የሕዝብ ቁጥር በትክክል መታወቅ አለበት የሚሉት ቆስጠንጢኖስ፤ በተለይም ሕዝቦች እየተፈናቀሉ ባሉበት ሁኔታ ፍትኃዊ የበጀት ክፍፍል መኖሩ አጠራጣሪ እንደሚሆንም ሳይናገሩ አላለፉም።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ የሕዝብ ቆጠራ ሳይካሄድና ቁጥሩ በትክክል ሳይታወቅ በጀት ማከፋፈልም ሆነ በእቅድ መሠረት ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ነው ያብራሩት።

እንደ ገለጻው ከሆነ፤ የኢኮኖሚ ለውጥ ሊመጣ የሚችለውና ፍትኃዊ የበጀት ክፍፍል የሚኖረው፤ የ10 ዓመቱ እቅድና የበጀት ክፍፍሉ በኢትዮጵያ ያሉ ሕዝቦችን ትክክለኛ ሙሉ ቁጥር መሠረት ሲያደርግ ነው። ይህ ደግሞ እንኳን ሕዝብና ቆጠራ ሳይካሄድ ተካሂዶም በሚኖረው መጭበርበር በኢኮኖሚው ላይ ፈታኝ ሁኔታዎች ሊጠፉ አይችሉም ነው ያሉት።

የሕዝብን ቁጥር ማወቅ ዋነኛ ዓላማው የትምህርት፤ የጤና እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን በተመለከተ እቅድ ለማቀድ ነው። ለዚህም ደግሞ በቅድሚያ የሕዝብን ቁጥር ማወቅ ግድ ይላል የሚሉት ሌላኛው የኢኮኖሚ አማካሪ ያሬድ ገብረ መስቀል ናቸው።

የዓመታዊ የኢትዮጵያ ምርትና አገልግሎት ተደምሮ ለጠቅላላ ሕዝብ ሲካፈል ወይም ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት በነፍስ ወከፍ የሚደርሰው መጠን (GDP per Capital) ግምታዊ መሆኑን ያሬድ አንስተዋል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን እና ውሳኔዎችን ያለ ሕዝብ ቁጥር ማስኬድ እንደማይቻል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በአጽንኦት ይናገራሉ። ኢኮኖሚያዊ ሥራዎችን ያለ ትክክለኛ ሕዝብ ቁጥር ከግብ ማድረስ እንደማይቻልም ነው ያሬድ ለአዲስ ማለዳ የጠቀሱት። የሕዝብ ቁጥር በትክክል ሳይታወቅ የሚወጣው ማንኛውም ቁጥራዊ መረጃ (Statistical Data) አስተማማኝ አለመሆኑንም ጠቁመዋል።

‹‹ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሰው ቆጠራ ሳይሆን ብሔር ቆጠራ ስለሆነ፣ ደግሞም በዛው መሠረት ስለተከናወነ፤ እስከ አሁን ያለው ፖለቲካ አዘል የሆነ የይገባኛል ፍላጎት የኢትዮጵያ ሕዝብና ቤት ቆጠራን አስፈሪና አጨቃጫቂም አድርጎታል።›› ነው ያሉት ያሬድ።

ሕዝብና ቤት ቆጠራ በሚካሄድበት ወቅት ቆጠራውን የሚያካሂዱት ገለልተኛ አካላት መሆን እንዳለባቸው ቢታመንም፤ ብሔርተኝነት ስር መስደዱን ተከትሎ በኢትዮጵያ ያለውን ትክክለኛ የሕዝብ ቁጥር ማወቅ ይከብዳል የሚሉ ትችቶችም ይሰነዘራሉ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ለሦስት ጊዜ በተካሄዱት ሕዝብና ቤት ቆጠራዎችን መለስ ብለን ብናስታወስ እንኳ፤ በ1976 የተካሄደው ከሌሎቹ የተሻለ ቢባልም ቀሪዎቹ ግን በብዛት እንከን የተላበሳቸውና ሁሉንም ቦታ ተደራሽ ያላደረጉ መሆናቸው በወቅቱ በስፋት ይወሳ ነበር።

ያሬድ በበኩላቸው፣ ሁሉም ክልል የሕዝብ ቁጥሩን በማጋነን ከበጀት ላይ ትልቁ ድርሻ ይድረሰኝ በሚል ስግብግብነትና የፍላጎቶች መጋጨት (Conflict of Interest) መፈጠሩን ጠቅሰዋል። በዚህም የተነሳ እውነተኛ የሕዝብ ቁጥር በትክክል ይቆጠራል ብሎ በእርግጠኝነት ለመናገር ያዳግታል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹ባደጉ አገራት ሰዎች በየአድራሻቸው የቤተሰብ ብዛታቸውን በፖስታ ይልካሉ እንጂ፣ ዙሮ መቁጠር የሚባል ነገር ስለሌለ ፖለቲካ በሕዝብ ቁጥር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት አይኖርም። በኢትዮጵያ ግን ቆጣሪዎች የሕዝቡን ቁጥር ጨማምረው የሚያወጡበት አጋጣሚ በመኖሩ ፖለቲካው አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።›› ይላሉ ያሬድ።

በተለይም ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ተንቀሳቅሰው የሚኖሩ ሰዎች፣ መጀመሪያ በኖሩበትም በወቅቱ ባሉበት ሥፍራም በድጋሚ የሚቆጠሩበት አጋጣሚ እንዳለም ይነገራል። ከዚህም አልፎ አንዳንድ ቆጣሪዎች ሆን ብለው የሌለውን ሰው ይጨምራሉ ነው የተባለው።

ያሬድ እንደገለጹት ከሆነ፤ ቀጥር መጨማመሩ ለፖለቲካ መሪዎች እንጂ ለሕዝቡ የሚሰጠው ጥቅም የለም። ይህ የሚሆነው በጀቱ በመሪዎች እጅ እንጂ ከሕዝቡ ስለማይደርስ ነው ተብሏል። በመሆኑም፣ ከብሔር ቁጥር የበጀት ትርፍ ለማግኘት የሚጣደፉ ሰዎች ቁጥሩን ከመጨመራቸው ካልተቆጠቡና የብሔር ቆጠራ ካልተወገደ የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁጥር ማወቅ እንደሚከብድም ተጠቅሷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here