ሰነድ ባጭበረበሩና የውል ግዴታቸውን ባልተወጡ ከ58 በላይ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ ገላን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በ2014 በተለያዩ ጊዜያት ለመንግሥት ተቋማት የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁሶች ለማቅረብ ጨረታ አሸንፈው ውላቸውን ተግባራዊ ያላደረጉ እና በሌሎች ሕገ ወጥ ወንጀሎች ላይ ተሳታፊ ሆነው የተገኙ ከ58 በላይ የግል ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
ገዳማይቱ ኮንስትራክሽን አስመጪና ጅምላ ንግድ፣ ሩቢስከ ጽሕፈት መሣሪያ፣ ሙላት አምበል ንግድ፣ ሴኔት ጅምላ ንግድ፣ ክንደ ብርቱ አጠቃላይ የፅዳት አገልግሎትን ጨምሮ ከ58 በላይ የንግድ ድርጅቶች ለመንግሥት ተቋማት የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ጨረታ ቢያሸንፉም፣ ውላቸውን ያልተገበሩ ናቸው ተብሏል።
እነዚህ ተቋማት ከአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ እሳትና አደጋ አመራር ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ እና ሌሎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ከሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ጋር የገቡትን ውል ያልተወጡ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ከዚህ መካከል የውል ግዴታን ለመወጣት ወይም ውል ለመፈጸም ፍቃደኛ ያልሆኑ 47 የንግድ ድርጅቶች፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ሰነድ ያጭበረበሩ፣ የዋጋ ማቅረቢያ አሸናፊ የሆኑበትን ያላቀረቡ፣ በመመሳጠርና በማጭበርበር የተጭበረበረ ወይም ሐሰተኛ ሰነድ ይዘው የተገኙ ናቸውም ተብሏል።
ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ከላይ የተጠቀሱት ተቋማት ከስድስት ወር እስከ ኹለት ዓመት ከስድስት ወር ለሚሆን ጊዜ ማንኛውም የመንግሥት ተቋማት በሚያወጣው የንግድ ጨረታ ላይ እንዳይሳተፉ የሚያግድ ሕጋዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተናግረዋል።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የጣለባቸው ሕጋዊ የመጫረት እግድ ጊዜ እስኪጠናቀቅ ድረስ ማንኛውም የመንግሥት ተቋማት በሚያወጡት የግዥ ጨረታ ላይ ማቅረብ የማይችሉ ሲሆን፣ የግል ድርጅቶች በሚያወጡት የግዥ ጨረታ ላይ ግን መሳተፍ ይችላሉ ተብሏል።
ባለሥልጣኑ የጣለባቸውን የቅጣት ጊዜ ካጠናቀቁ በኋላ የተጠቀሱት የንግድ ድርጅቶቹ ከስህተታቸው የሚታረሙ ከሆነ ወደ ግዥ ጨረታ ሂደቱ የሚመለሱበት ሁኔታ እንደሚኖር ተወስቷል።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት፣ ማስጃዎችን መሠረት አድርገው ባደረሱት መረጃ መሠረት ይህን ውሳኔ ለመወሰን የተገደደ ሲሆን፣ በቀጣይ በክልል የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ተያያዥ ጥቆማዎችን በሚያቀርቡበት ወቅት እርምጃው እንደሚቀጥልም ተጠቅሷል።
ዳይሬክተሩ አክለውም፣ የመንግሥት ተቋማት ብዙ ቁሳቁሶችን ከንግድ ድርጅቶች እንደሚገዙ ሁሉ የንግድ ድርጅቶችም ቢሆን፣ ከመንግሥት ተቋማት ጋር ያላቸውን የግዥ ሂደት ማጣት እንደማይፈልጉ ያስረዳሉ።
ከዚህ አንፃር የንግድ ድርጅቶች ከሕገ ወጥ የንግድ አሠራር፣ ከማጭበርበር፣ በውላቸው መሠረት ግዴታቸውን ካለመወጣት እና ከሌሎች ሕግን ከጣሱ አሠራሮች እንዲቆጠቡ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
የግል ድርጅቶችም ቢሆኑ ሕገ ወጥ ማስረጃ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የንግድ ድርጅቶች ሲያጋጥሟቸው ጥቆማ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ጥቆማዎችን ተቀብሎ እና አጣርቶ የሚወስደውን እርምጃ አጎልብቶ እንደሚቀጥልም ተነግሯል።
ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014



