ለስኳር ፋብሪካዎች የአገዳ ማሳ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት አለመኖሩ ተገለጸ

0
1726

ለስኳር ፋብሪካዎች የአገዳ ማሳ የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት አለመኖሩን አዲስ ማለዳ በፋብሪካዎች ከሚሠሩ ባለሙያዎች ለማወቅ ችላለች። በዚህ ዓመት የአፈር ማዳበሪያ ችግር እንደ አገር የተከሰተ መሆኑን ተከትሎ፣ ቅድሚያ ለገበሬዎች ነው በሚል የሸንኮራ አገዳ ማሳዎች ያለማዳበሪያ እየተተከሉ ነው ተብሏል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በወንጂ ስኳር ፋብሪካ የሸንኮራ አገዳ ማሳ ውስጥ የእርሻ ሠራተኛ ሆነው የሚሠሩ ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የሸንኮራ አገዳ ማሳው በሄክታር እስከ አራት ኩንታል የሚደርስ የአፈር ማዳበሪያ የሚጠቀም ቢሆንም፣ በዚህ ዓመት ግን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ባለመኖሩ እየተተከለ ያለው በባዶ ነው ብለዋል።

የሸንኮራ አገዳ ማሳው ካለ አፈር ማዳበሪያ በሚተከልበት ጊዜ ሰፊ የሆነ የምርት መቀነስ ያስከትላል ሲሉ ገልጸው፣ መጀመሪያ ከሚተከለውም ባለፈ አገዳው እየተቆረጠ ለኹለተኛና ሦስተኛ ጊዜ የሚበቅለውም ምርታማነቱ እየቀነሰ ስለሚሄድ የአፈር ማዳበሪያ ያስፈልገው ነበር ብለዋል።

ለስኳር ፋብሪካዎች የሸንኮራ አገዳ ማሳ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት የሌለው በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ ብቻ ሳይሆን በኹሉም ፋብሪካዎች ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ችግሩን ለማቃለል እንደ ተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያነት የሚያገለግሉ የፋብሪካውን ተረፈ ምርቶች ለመጠቀም ሙከራ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ስምንት ሺሕ ገደማ በሚሆን ሄክታር የሸንኮራ አገዳ እያለማ ቢሆንም፣ አሁንም ለማሳ የሚሆን የመሬት እጥረት አለ ነው ያሉት። ፋብሪካው የመፍጨት አቅሙን በማሳደጉም የጥገና ጊዜውን ጨርሶ ወደ ምርት ሲገባ የአገዳ እጥረት እንደሚኖር ገልጸዋል።

በተጨማሪም፣ በውኃ እጥረት ምክንያት ሳይጠጣ የሚቀር የሸንኮራ አገዳ ምርት መኖሩን በማንሳት፣ የሸንኮራ አገዳ ምርታማነቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሆኑን አስገንዝበዋል። አክለውም የአገዳ ቆረጣ የሚካሄደው በእጅ መሆኑም ከስር እንዳይቆረጥ ስለሚያደርግ የምርት ብክነት ይፈጠራል ብለዋል።

በ13 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሸንኮራ አገዳ ማሳ አለው የተባለው ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካም እንዲሁ ካለው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት አለመኖር በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በሙሉ አቅሙ እያመረተ ባለመሆኑ፣ የሸንኮራ አገዳ ምርቱ ቀድሞ ደርሶ እየደረቀ ነው ተብሏል። በሌላም በኩል በአንዳንድ ስኳር ፋብሪካዎች ለአብነትም በወንጂ እና ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ከሸንኮራ አገዳ ማሳው የተወሰነው ስንዴ እየተዘራበት በመሆኑ በቀጣይ ዓመት የስኳር እጥረት ሊኖር ይችላል የሚሉ ስጋቶች ይቀርባሉ።

ይሁን እንጂ ባለሙያዎች ይህ የሆነው ማሳውን ለማሳረፍ እንዲሁም ፋብሪካዎች በክረምት ጥገና ላይ ስለሚሆኑና አገዳው በዚህ ወቅት ከተዘራ የሚደርሰው በዓመቱ ሰኔ ስለሆነ የመሬት ብክነቱን ለመቀነስ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አዲስ ማለዳ በስኳር ፋብሪካዎች የሸንኮራ አገዳ እጥረት ማጋጠሙን ከዚህ በፊት መዘገቧ ይታወሳል።

ለአብነትም በመተኻራ ስኳር ፋብሪካ የበልግ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡና በአካባቢው ያለው የድርቅ መጠን ከሌላው ዓመት የተለየ በመሆኑ የአገዳ ምርት እጥረት መኖሩን፣ እንዲሁም በአፋር ክልል የሚገኘው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በድርቅ ምክንያት ማሳው መውደሙን የስኳር ኮርፖሬሽን ቀደም ብሎ አሳውቋል። አዲስ ማለዳ በስኳር ፋብሪካዎች የሸንኮራ አገዳ ማሳ አሁን ስላለው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ማብራሪያ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም ሳይሳካ ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here