የመጅሊሱ ነጠቃ እና የመንግሥት ጣልቃ ገብነት

ከ1 ሺሕ 400 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያውያን አማኞች ሲተዳደሩበት የነበረው የእስልምና ሃይማኖት መጅሊስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአመራር መረጣና አስተዳደር ረገድ ፈተና እንደገጠመው ሲሰማ ቆይቷል። ባልተለመደ መልኩ ገለልተኛ ነኝ የሚል የመንግሥት አካል ሆነ መሪ፣ የሃይማኖቱን አባቶች ሰብስቦም ስለማወያየቱ ዘግይቶም ቢሆን ኹሉም ኢትዮጵያዊ እንዲከታተለው የተደረገ ነበር። ስለሕዝበ ሙስሊሙ የውስጥ ጉዳይ የሃይማኖቱ ተከታዮች የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰነዝሩም ቆይተዋል። ጁሃር ሳዲቅ (ጋዜጠኛ) በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ዕይታእንዲህ አስፍረዋል።

የኢትዮጵያ ነባር እስልምና ፈተና ከበዛበት ዐስርት ዓመታትን አሳልፏል። በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ፈተናዎቹም የነባሩ የኢትዮጵያ እስልምና በቁንጮነት የሚመራው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችን ለማወክ እና ለመውረር (Destruct and invade) ያለመ ነበር ማለት ይቻላል ። በዚህ መጣጥፍ ነባሩ የኢትዮጵያ እስልምና ስል ለ1400 ከኢትዮጵያ ባህል አኗኗር ቋንቋ ጋር ተዛምዶ ሀገርና ትዉልድ ያቀናዉ አህሉሱና/ነባር ሙስሊም ማለቴ ነው።

በአንፃሩ ደግሞ ከሠላሳ ዓመት ወዲህ የመጣው ከኢትዮጵያዊ ዕይታ ማንነት ይልቅ፣ የፖን-አረቢዝም አስተሳሰብ ያለዉ የወሓቢ ሰለፊ እና የብራዘርሁድ መጤ አስተሳሰብ በተቃራኒው ለነባሩ የኢትዮጵያ ሙስሊም ፈተና ሆኖ ነባሩን ለማፍረስ በርካታ ድንጋዮች ሲፈነቅል ቆይቷል። ከነባሩ የኢትዮጵያ አህለሱና አስተሳሰብ ውጪ ያሉት መጤዎቹ የወሓቢ ሰለፊ እና የብራዘርሁድ አስተሳሰብ የእምነት መሠረት የሌለው ነገር ግን ኢስላማዊ የሚመስል ፖለቲካን በማራመድ ይታወቃሉ።

ይህንን የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማስፈፀም በቅድሚያ አድማጭ ለማፍራት ኢስላማዊ አስተምህሮ ላይ ቁንፅል እዉቀት ይዘዉ ስሱ (Sensetive) ጉዳዮችን በማንሳት ተከታይ ለማፍራት ይጥራሉ። በዚህም ያለእውቀታቸዉ “ኡስታዝ” ሆነዉ መንጠላጠል ይጀምራሉ። “ኡስታዝ” የሚለው በፓን-አረቢዝም የፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ አክቲቪስቶች መሆናቸውን ያስረግጣሉ። በዚህ አክቲቪዝም ስር በርካታ ፖለቲካዊ ተፋልሶ (paradox) ሳጥኖች በመክፈት የመታገያ ትርክት ይፈጥራሉ።

ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ የቅራኔ አጀንዳዎችን በማስፋት አልያም ድርሰት በመፍጠር ለፖለቲካ ዓላማቸው ለማስፈፀም ይጠቀማሉ። እነዚህ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴን ኢስላማዊ አስመስሎ በማቅረብ አንዱ የሚታወቁበት ማንነታቸው ነው። እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው አካላት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መንበር ለመቆናጠጥ ያላቸው ዓላማ ከፍ እንዲል ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ሀገሪቱ የተከተለችው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ለመሸሸጊያነት ይገለገሉበት ዘንድ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል ማለት ይቻላል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕግ በሀይማኖት የፖለቲካ ዓላማ ማራመድ ስለሚከለክል በተበታተነው የዘር ፖለቲካ ስር መመሸግ ቆንጆ አማራጭ ሆኗል።

ለዚህም ሲባል ‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው› የፖለቲካ ቀመር በመከተል፣ ‹የድምፃችን ምናምን› የተባለ ፀረ እስልምና እንቅስቃሴ ከየትኛው የዘውግ ፖለቲካ ጋር ሲያገናኙት እንደነበርና ሲሠራ እንደነበር ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀዉ ጉዳይ ነው።

የዚህ ሀይማኖት ያዳቀለ የፖለቲካ አጀንዳ አራማጆች ዓላማቸው የራሳቸውን የገፅታ ግንባታ ከገነቡ በኋላ፣ የእነሱን ዓላማ አይደግፉም አልያም መሰናክል ይሆኑብናል የሚሏቸውን በሀይማኖት ዘርፍ እጅግ ልሂቅ የተባሉ ኡላማዎችን ከፍ ዝቅ በማድረግ ሥማቸውን በማጉደፍ ከሕዝብ የመነጠል ሥራ መሥራት ነው። በዚህ ረገድ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ብራዘርሁዶቹ እና ወሓቢ-ሰለፊስት የሆኑት የሠሩት ይህንኑ ነው።

ይሄ የአስተሳሰቡ አራማጆች ሥነምግባር አልባነታቸው በዓለም የሚያሳወቅበት ነው። በኢትዮጵያ ደግሞ ከእነዚህ አስተሳሰቦች አደራጅ ተዋናይ የሆነው አሕመዲን ጀበል እና የድምፃችን ይሰማ ተዋናዮች የመሠረቱትን ኮሚቴ መጥቀስ ይቻላል። በቅርቡ የዚህ ቡድን እኩይ መንገዶች ይፋ በተደረገው ድብቅ ቪዲዮ ታይቷል። የቡድኑ አሳፋሪነትና ጨካኝነት ብሎም ከፋፋይነት አንጥሮ ያሳየ ነበር ማለት ይቻላል።

ለምሳሌ የኛ ሰው ካጠፋ ዝም እንላለን። ከእኛ ውጪ ያለ አካል ከሆነ እናብጠለጥለዋለን። የገፅታ ማበላሸት ዘመቻ እናደርጋለን። የኛ ሰው ከሞተ/ለኛ ፖለቲካ የሚጠቅመውን እናጦዘዋለን። ከእኛ አጀንዳወ ውጪ ከሆነ ነገሩን ማድበስበስ ማስቀየስ ነው፤ በማለት ከሀይማኖት ሰዉ ነኝ ከሚል የማይጠበቅ፣ የከፋ አስተሳሰብ አራማጅ መሆናቸውን ከዚህ በላይ የሚያሳይ የለም። ይሕ የክፋት ቅርሻትና ዘመቻ በዚህ የሚያበቃ አይደለም። ከግለሰቦች እስከ ተቋም፤ ከተቋም እስከ ዘር ተኮር እና ሀይማኖት ጭምር ለይቶ ያስቀመጠ መሆኑ ደግሞ በዚህ እሳቦት ሰይጣን ሳይቀና ሁሉ አይቀርም ባይ ነኝ።

አንድ አማራ ሙስሊም ከክልሉ ውጪ ከሞተ መጀመሪያ ይድበሰበሳል፤ አማራ ስለሆነ። ሙስሊም መሆኑ ለእነሱ የፖለቲካዊ ጥቅም የማያስገኝ ከሆነ ማስቀየሻ ይደረጋል። ለምሳሌ በመተከል ቤንሻንጉል እና በወለጋ በተደጋጋሚ የተከሰቱ ግድያዎችን መመልከት በቂ ነው። በተቃራኒው በአማራ እና ትግራይ በሆነ በእምነትም በሌላም ጉዳይ ከተገደለ ጉዳዩን እናጡዘው ይላሉ። ዋቢ እንዲሆናችሁ የሞጣና የጎንደር ከዚህ ቀደም በትግራይ የነበረውን ሁነት መመልከት በቂ ይመስለኛል።

ሌላዉ በነባሩ ሙስሊም መሻኢሆች የተመሠረተው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችን በመቆጣጠር የፖለቲካ አክቲቪዝማቸውን ሰፊውን ሙስሊም ምዕመን ለመያዝ መሥራት አንዱ አጀንዳ ነበር። መጅሊሱ ታርጌት የተደረገው በሀይማኖት ጉዳይ አይደለም፤ ለፖለቲካ መንበር መሰላል ሆኖ ያገለግላቸው ዘንድ እንጂ።

ወሓቢዝም እና ብራዘርሁድ ሀይማኖት ያለመሆናቸውን የኢትዮጵያ ነባር ሊቃውንትን ጨምሮ የዓለም ሙስሊም የሚያምንበት ጉዳይ ነው። እምነቱን ግን ለፖለቲካ ይጠቀሙበታል። ይህንን ዓላማ በመያዝ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መጅሊስ ከሀይማኖት አባቶች ተነጥቆ የፖለቲካ ፓርቲ ዓይነት ቅርፅ ለማስያዝ ከ80ዎቹ ጀምሮ ላለፉት በርካታ ዓመታት ከፍተኛ ዘመቻ አካሂደውበታል። ባስቀመጡት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ንቅናቄ ለመፍጠርና ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ሥራ የሠሩበት የ2004ቱ እንቅስቃሴ ይገኝበታል።

በዚህ እንቅስቃሴ ወቅት እንደዋና ማታገያ የያዙት የሀይማኖት ተቋም የሆነው መጅሊሱን ነበር። ከላይ በተገለፀው መሠረት እንቅስቃሴው ከእምነት የበለጠ ፖለቲካው ላይ ያመዘነ ነበር፤ ታርጌቱ የፖለቲካ ሥልጣን መቆናጠጥ ስለነበር።

መጅሊሱ ከጅምሩ ገና እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ሲነሱ የዚህ አንጃ ቀንደኛ ጠላት ተደርጎ ተፈርጆ ዘመቻ የተደረገበት መሆኑን ነው። ለዚህም መጅሊስ ላይ ያሉ ሰዎች ከቀንደኛ ተቀናቃኞች መድበዋቸው በተቋሙም በግለሰቦችም ላይ ዘመቻ ሲያደርጉ መክረማቸው ከላይ በጠቀስኩት የምስጢር ቪዲዮ ጭምር አፈትልኮ የወጣ ሀቅ ነው።

እንግዲህ ሀገሪቱ አዲስ አመራር ካመጣች ጀምሮ ለተከታታይ አራት ዓመታት በመጅሊሱ ላይና በፕሬዝዳንቱ፣ የሰላም አባት የሀይማኖት ሊቃውንት የሆኑት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ ላይ ሲደረግ የነበረው ገፅታ የማበላሸት ዘመቻ መሆኑን ልብ ይሏል። የተቀዳሚ ሀጂ ሙፍቲ ዑመር ሥምን ለማጥፋት ከጠምጣሚ ካድሬ እስከ ‹የመጅሊሱ ነፍጠኛ ኦርቶማራ› በማለት ለማሸማቀቅ የዚህ የፓን-አረቢስቱ ፖለቲካ ዋና ተዋናይን ጨምሮ ከየት እንደተማሩ የማይታወቁ የታሪክ ተመራማሪ ነን ባይ ጎረምሶች ዘመቻ፣ ፖለቲካ እንጂ ሀይማኖት እንዳልሆነ በትክክል አማኝ ለሆነ ሙስሊም ግልፅ ነዉ ።

ሀይማኖት ሳይማሩ ለርካሽ ፖለቲካ ሲሉ ትላንት ዘፋኝ የነበሩ አዝማሪዎች ነፍጥ አስነግበው በፎቶሾፕ ሁሉ ተቀዳሚ ሙፍቲን ሲሰድቡ ፖለቲካ እንጂ ሀይማኖት እንዳልሆነ፤ እሳትም ድንጋይም የሚያመልክ ስለማያደርገው ግልፅ ነዉ። ልክ በዚህ መልኩ፤ ከነሱ የፖለቲካ አመለካከት በተቃራኒ ነፃ ሆኖ የሚያስብን ተቋም ለማሳጣት የሄዱበት ርቀት በአንክሮ ለተመለከተ የግለሰቦቹን ፖለቲካ አራማጅነት ይረዳል። ምንም እንኳ ዛሬ ላይ ለፖለቲካ ዓላማ የዘር ፖለቲካ ያጋመደው ጥምረት ብናይም፤ እየዋለ ሲያድር ፖለቲካ ነውና መጋጨታቸው የሚጠበቅ ይሆናል።

የጋራ ጠላት (common enemy) ጉዳይ ሲያበቃ የእርስ በእርሱ ሽኩቻ በሂደት ሀገሪቷን ለመቆጣጠር መንግሥት ላይ ለመነሳት አቅደው እንደሚንቀሳቀሱ ለመዘርዘር፤ ይህ ርዕስ ስለማይበቃ ወደመዝገብ ቤት ዘግቼ መልሼዋለሁ።

የብሔር ፌዴራሊዝም ያዋለደው መጅሊስ ይዘልቃል ብላችሁም ይሁን የጊዜያዊ የፖለቲካ አሊያንሶቹ ጋርም ይዛለቃሉ ብላችሁ አታስቡ። ወሓቢዝም አንድ ቦታ ላይ የማይረግጥ አቋም የሌለው በመሆኑ ፅንፈኝነቱ ስለማይላቀቀው አብረው የመቀጠሉ ነገር የምናየው ይሆናል። አላልንም እንዳይባል ብለናል እና ይሄ ይያዝልን። በዚህ ረገድ ከመጅሊሱ እስከ ሙፍቲና የነባሩ ሙስሊም አራማጆች፤ እንደ አምባሳደር ሸይኽ ሀሰን ታጁን የመሳሰሉ ታላላቅ ምሁራን ጭምር የማክሰም ሥራዎችን ነው ሆነ ብለው ሲፈፅሙ የመጡት።

በዚህ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የነባሩ ሙስሊም ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ ግለሰቦች በመርዝ ከመመረዝ ጀምሮ በኢኮኖሚ ማእቀብ፣ በትዳር ሕይወት፣ በቤተሰብ ሕይወት ጭምር እስከ መግደል ሙከራዎች እንደተደረገባቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀው አይመስለኝም። በአጠቃላይ መጅሊሱ የፖለቲካ አጀንዳው ማእከል (core place) ነበር፤ ነውም ማለት ይቻላል።

ልክ ይሄ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ አካሄዳቸው ከወራት በፊት አንድ የድምፃችን ይሰማ መሪ ይህንኑ መጅሊሱን አስመልክቶ በአወሊያ ሚሲዮን ባደረገው ፅንፈኛ ንግግር በጁመዓ በየመስጂዱ ለወለጋ ሟቾች ሰልፍ እንጠራለን ካሉ በኋላ፣ “የሸኽ ኢብራሂም ቱፋ መጅሊስ ይቆጣጠራል። አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተነጋግረናል። የወለጋ ሙስሊሞች ጉዳይ አስመልክቶ ይሠራል” በማለት በወቅቱ የአድማጭ ጆሮ ለመሰብሰብ ችለው ነበር። ቢሆንም ለእምነቱ ተቆርቁረው እንዳልሆነ ጁመዓ ያሉት ድምፅ ለንፁሃን ማሰማት የወሀ ሽታ ሆኖ ቀረ፤ ለፖለቲካቸው ስለማይጠቅማቸው።

በቅርቡ ይኸዉ የነ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ለሦስት ዓመት ሕገወጥ ሲል መንግሥት ሲያባርረው የነበረ አካል በመንግሥት የፀጥታ አካላት ታጅቦ የነባሩ የኢትዮጵያ ሙስሊም ተቋም መጅሊስ ከተቀዳሚ ሀጂ ሙፍቲ ተነጥቆ ለፖለቲከኛው ቡድን ተሰጥቷል። ይህ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የታየበት የመጅሊስ ጉዳይ ሙስሊሙን አሳዝኖታል፣ እኔንም ጨምሮ።

መንግሥት ከጅምሩ ጣልቃ የገባበት መጅሊስ ነው ማለት ይቻላል። በመሆኑም ለወሓቢ ኢኽዋኑ ክንፍ አሳልፎ በኃይል ሲሰጥ ተቋሙ ከነበረበት ሀይማኖታዊ እና ታሪካዊ ባለቤቱን የካደ ስለሆነ ሕዝበ ሙስሊሙ መጅሊሱ ተነጥቆ እንዲፈርስ ተደርጓል ማለት ይቻላል። ከመጀመሪያው ጀምረን ብናየው የሀይማኖት አባቶች መነጋገር መጅሊሱ ራሱ መፍታት የሚችለው ጉዳይ ዉስጥ መንግሥት ለሀገር ሰላም በሚል የነበረው መጅሊስ ጠቅላላ ጉባኤ በመበተን ሕዝበ ሙስሊሙ ለሦስት ዓመታት ተቋም አልባ እንዲሆን ተደርጓል። በዚህ መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ ወሓቢሰለፊው እና ብራዘርሁዱ ታጭቆ በዓላማቸው መሠረት መጅሊሱን ለመንጠቅ ተኮልኩለው እንዲገቡ ተደርገዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ተቋም ያገኘ ፅንፈኛ ብል፤ አሳነስኩት ባይ ነኝ።

የሰላም አባት የሆኑት ሙፍቲ ዑመር ሁሌ ለሰብዓዊነት፣ ለሰላምና ለአንድነት የሚጨነቁ አባት ናቸው። የሕዝበ ሙስሊሙን አንድነት በሚጠየቁ ሰዓት ያለ ፖለቲካ ስሌት (without political conspiracy) ተቀብለው ሠርተዋል። በኋላም ‹ለሰላም በሚደረግ ሂደት ላይ ብልጣብልጥ ጨዋታ በመታለሌ ባላዝንም፤ ነባሩን እስልምና አራማጅ ሕዝብ ግን ጎድቻችኋለሁ› ሲሉ የሂደቱ ጨፍላቂነት ብዙም ሳይሄድ ነበር ይፋ ያደረጉት።

እንደው ለወደፊቱ ትውልድ እና የኢትዮጵያ ታሪክ አካል ሆኖ እንዲሰነድ ሂደቱ ትንሽ ለመዳሰስ ወደድኩ። የለውጥ ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ለነበሩ የመጅሊስ አባላት ለሰላም ሲባል ሥልጣናቸው እንዲለቁ ጠየቁ። በዚህ መሠረት ከብዙ መጨቃጨቆች በኋላ ፖለቲካዊ ማሳመኛዎች ታክለውበት ሥልጣን አስረከቡ። ወዲያው ከሱፊ ሰለፊ ተወካዮች እና ዘጠኝ ኮሚቴ ተመረጡ።

ከተወሰኑ መነጋገሮች በኋላ የመጀመሪያው ብልጣብልጥነት ከሸራተን ሚያዝያ 23/2011 ስብሰባ ይጀምራል። ተቋሙ በነበረው ስምምነት በሱፊ ነባሩ ሙስሊም እና በወሓቢሰለፊ ተዋቅሮ ስብሰባ ለማድረግ በታሰበው ፕሮግራም እስከ 300 ሰው እንዲወያዩ ማድረግ የነበረ ቢሆንም፤ ተሳታፊ ጠሪም፣ ተቆጣጣሪም፣ መድረክ መሪም ወዘተ መፈንጫ ሆነ ውክልናው ለማምከን የቂል ጨዋታ አድርገውት አረፉ። ስብሰባ የተባለው ሰነድ ማጽደቅ ሆኖ እውነታውን በአንድነት ሥም የሚሸቅጥ የፖለቲካ ስብስብ መሆኑ ለሙስሊሙ ፍንትው ብሎ ታየ።

ሂደቱ ቀጠለ፤ መጅሊሱ በጊዜያዊነት እንዲመሩ የተደረጉት ኡለሞች ከስር በመሆን ከሸሪዓ ውጪ የሆኑ ቴክኒካል ሥራዎችን እንዲሠራ የተደረገው አካልም፣ ኡለሞቹን ገሸሽ አድርጎ እኔ ካልዘወርኩ በሚል ኢጎ ከተሰጠው ዓላማ ውጪ ስብሰባዎች መጥራት፣ መጅሊሱ በፋይናንስ እንዲዳከም ማድረግ፣ ሠራተኞች በፈቃዱ በማባረር ውጪ ላለው የፖለቲካ ኃይል ጥርጊያ መንገዱ ካልከፈትኩ ሞቼ እገኛለሁ ሲል እጅ ከፍንጅ ተያዘ። ተይዞም በሙሉ ስምምነት እገዳ ሲጣልበት፣ ውጪ ያለው ክንፍ መንጫጫት ጀመረ። ይሄኔ በመጅሊሱ ሥም የሚያካሂዱት ፖለቲካ ለሙስሊሙ ተገለጸ።

ከመጅሊሱ የተባረረዉ ቦርድ ውጪ የሚንቀሳቀሰው ኃይል በማኩረፉ በውስጥ ሰላም እንዲነሱ በማድረጉ በዚህ መሠረት እስከመታገድ የደረሱ ነበሩ። መጨረሻ ቁልፍ ያስረከበም ነበር። ይህ ብቻም አልነበረም፤ ጠቅላላ ጉባኤ በሚል መሠረታዊ የተባሉ የአንድነት የመግባቢያ ሰነዶች ላይ አንድ ውሳኔ መግባባት ላይ ሳይደረስ ሰነድ ሳይኖር ጠቅላላ ጉባኤ አንዱ አንዱን ጨፍልቆ ለመሄድ ያለመና የሚያመች በመሆኑ፤ የመጅሊሱ ተግባር ይህንን መሠረት መሥራት ስለሆነ፤ ጠቅላላ ጉባኤ ከዛ ቀጣይ የሚመጣ በመሆኑም፣ ጠቅላላ ጉባኤ እያሉ የቀረ ሆቴል ያለ አይመስለኝም።

እነዚህን ስብሰባዎች ሲመሩ፣ በመንግሥት በኩል ነበር ሕገወጥ በመሆናቸው ሲቋረጡ የነበረው። በመጨረሻም የነበረው ጠቅላላ ጉባኤ ሕጋዊ ያለመሆኑ ጭምር የታወቀ ነበር። ይሄ ሁሉ ሲሆን መንግሥት እነዚህ ሰዎች ጉባኤ እንዳያደርጉ ይሁን እንጂ፣ በአዲስ አበባ መጅሊሱ ክንፋቸው በኩል የሚሠራው ሙስሊሙን የማናከስ ሥራ ግን አላቆመም ነበር።

ሙፍቲ የሾሙት ቅርንጫፍ ተቋም አልታዘዝ ብሎ እንደፈለገ የሕግ ጥሰት ሲፈፅም፣ ከ40 በላይ መስጂድ ሲያበጣብጥ ሙስሊሙን ሲያሳስር፤ ሙፍቲ ደብዳቤ ሲፅፉ ተግባራዊ የሚያደርግ አካል አልነበረም። ይህ የሆነበት ምክንያትም ከስር ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወሓቢሰለፊዉ ቡድን ከአረብ በሚጎርፍ ሪያሉ በማጨማለቁ መሆኑ የድፍን ሙስሊሙ መነጋገሪያ ነበር። በዚህ መልኩ የሙፍቲን መጅሊስ ለማፍረስ (sabotage) ሠርተዋል።

ሪዛይን ሲያደርጉ፤ ከላይ መጀመሪያ የፌዴራል መጅሊሱ ሙሉ ሲስተሙ በመቋረጡ፣ በየክልሉ ያሉ መጅሊሶች በወሐቢሰለፊዉ ጎረምሶች እንዲሰበሩ አድርጓል። አህመዲን ጀበል ኦሮሚያ ባህል ማዕከል አካባቢ የሚገኘው የኦሮሚያ መጅሊስን የተቆጣጠረው እንዲሁ በጉልበት ጎረምሶችን ሰብስቦ ነበር። በዚህ መሠረት ነበር የነባሩ ሙስሊም ተቋማትን መንግሥት ያስረከበው።

እንግዲህ ብቻውን በወሓቢያ መጅሊስ ተከቦ የተንጠለጠለው በሙፍቲ ሲመራ የነበረው መጅሊስ፣ በአዲስ አበባ በራሳቸው ደብዳቤ የተሾመው በሱልጣን አማን የሚመራው የአዲስ አበባ ጠቅላይ መጅሊሱ ላይ ያልተገባ ሥም ማጥፋት፣ መፎካከር እንዲሁም ራሱ በጠቅላላ ጉባኤ የወሓቢያ መጅሊስ አዉጆ መገንጠሉን ያወጀው ቡድን አካል በመሆኑ ጠቅላይ መጅሊሱ ቅርንጫፍ መጅሊሱን እውቅና በማንሳት እንዲታሸግ አደረገ።

አንድ የታሸገ ተቋምን ሰብሮ መግባት ከሕግ ጥሰትም በላይ ወንጀል ቢሆንም፣ ሱልጣን አማን ጎረምሳ ሰብስቦ መጅሊሱን ሲሰብር የፀጥታ አካላት ይህንን ወንጀል ለመከላከል ያደረጉት ጥረት አልነበረም። ከዚህም ባስ ብሎ በአዲስ አበባ የነባሩ ሙስሊም የሚወክሉት ሸይኽ አሊን ሌሎች በርካታ ሠራተኞችን አባረረ። በዚህ ኢ-ፍትሐዊነቱ ባፈጠጠ ወገንተኝነት የተናደዱ ወጣቶች የሀይማኖት አባቶች ተቃውሞ ሰልፍ በጠዋት መጅሊሱ ቢሮ ሄዱ። በውስጥ ከተቋሙ ቅጥረኝነት ውጪ መጅሊሱ ቢሮ ሲያድሩ የነበሩ ወጣቶች ከሰልፈኞቹ ጋር አለመግባባት ፈጠሩ። ሁከት ተነሳና እኔ በሀይማኖት ጣልቃ አልገባም ሲል የነበረው የፀጥታ ኃይሉ፣ ተበዳዩ አካል መብቱ ለመጠየቅ ሲሄድ ግን እስከ 120 ሰው በመያዝ ሲያስር ተስተውሏል።

ይሄ በትልቁ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መሆኑ ይሰመርበት። ሌላዉ ቀርቶ በፌዴራል መጅሊሱ ሲያስረብሹ ለፀጥታው አካላት ሲነገር እኛ ውስጥ አንገባም የሚል የሕግ ማስከበር አሳዛኝም ትልቅ በደል በነባሩ ሙስሊም ላይ ለመፈፀሙ ከዚህ በላይ ማሳያ የለም። ከአረፋ በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የመሰባሰቡ ገፊ ምክንያት ይኸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወያይታችሁ ወስኑ አልያም ወደ ሕዝቡ እንመራዋለን ቢሉም፣ በተሠራዉ ሿሿ ለሦስት ዓመታት ሕገወጥ የነበረ አካል ሕጋዊ ተደርጎ በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ታጅቦ መጅሊሱ ተሰብሮ በመግባት መደበኛ ያልሆነ ሽግግር (informal transition) ተደርጓል። ይህ ሕገመንግሥታዊ ስርዓት አለበት በሚባል ሀገር ላይ እንዲህ ዓይነት ሕገወጥነት ማየት በእውነቱ ያሳዝናል።

የመጅሊሱ ሕገወጥ ነጠቃና ፍንቀላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካሉት አንፃር የተቃረነ ነው። ይህ ነገር በእኔ ዕይታ በኹለት መልኩ ይቀርባል። አንደኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩን የማይሰሙ ባለረዥም እጅ ባለሥልጠናት ተፈጥረውባቸዋል፣ ተዳክመዋል የሚለው ሲሆን፣ ኹለተኛዉ ደግሞ ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዚህ የመጅሊሱ ሿሿ አንዱ አካል ሆነው እየተወኑ ነበር የሚባለውን ለማመን እገደዳለሁ። ከዚህ ውጪ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም በመጅሊሱ ላይ የተደረገው መፈንቅል ፍፁም ሕጉን የተፃረረ ሕገወጥ ነው። የዚህን አደራ ለታሪክ ትቻለሁ። ይህንን ያደረጉም ታሪክ ይወቅሳቸዋል።

የጽሁፉን አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጁሃር ሳዲቅን በ [email protected] ኢሜል አድራሻቸው ማግኘት ትችላላችሁ።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here