መነሻ ገጽዜናወቅታዊንባብ ለሕይወት

ንባብ ለሕይወት

ዘመኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ የላቀበት ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በዚህ ወቅት ተስፋፍቷል። ማኅበራዊ ሕይወት፣ የሥራ ሰዓት፣ እንቅልፍና ሌሎች ብዙ ነገሮችም ጊዜ ይጠይቃሉ።

ስለሆነም በዚህ ሁኔታ ለሰው ልጅ ሕይወት እጅግ ጠቃሚ የሆነውን የንባብ ሕይወት ለማዳበር ለብዙዎች ከባድ ሆኖ ይታያል። ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ስለንባብ ያላቸው ግንዛቤ እንዲሁም የንባብ ልምዳቸውም እጅግ የወረደ ነው።

የተወሰኑ ወጣቶች ስለንባብ ያላቸውን ዕይታ ልምዳቸውን ጠይቀናል። ‹‹በወር 15 ቀን እረፍት አለኝ። በወር የተጣራ ገቢዬ ከ15 ሺሕ ብር በላይ ነው።›› የሚሉ ሥማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ የጤና ባለሙያ፣ ‹‹አዲስ አበባ መኖር ከጀመርኩኝ ኹለት ዓመቴ ነው። እስካሁን ያነበብኩት ግን አንድ መጽሐፍ ብቻ ነው። በእድሜዬ የገዛኹት መጽሐፍም የለም።›› ይላሉ።

‹‹የዩንቨርሲቲ ተማሪ እያለሁም ማንበብ አልወድም ነበር። አሁንም በእረፍት ቀኔ የት ልሂድ እያልኩኝ ላብድ ነው የምደርሰው። ማንበብን ግን አስቤውም አላውቅም።›› ነው ያሉት።

ከትምህርት ነክ መጽሐፍት በስተቀር ሌሎች መጽሐፍትን አንብቤ አላውቅም ከሚሉ ሰዎች ጀምሮ፣ ካነበብን ከኹለት ዓመት በላይ ሆኖናል የሚሉ ሰዎች ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም።

ሆኖም ለንባብ ጥሩ ግንዛቤ ያላቸውና የተሻለ የንባብ ልምድ ባለቤት የሆኑ ሰዎች ስለመኖራቸውም የሚካድ አይደለም።

ሥሟ እንዲጠቀስ ያልወደደች ወጣት ሴት ደግሞ ማንበብ እንደምትወድ፣ ከትምህርት መጽሐፍት ጀምሮ በሳምንት አንድ መጽሐፍ ለመጨረስ ጥረት እንደምታደርግ ትገልጽና፣ ማኅበራዊ ሚዲያን የምትጠቀመውም ለማንበብ እንደሆነ ትናገራለች።

ሻበዲን ጀማል የሚባሉ አባወራ እንዲሁ ስለዚሁ ስለንባብ ጉዳይ አንስተው፣ በስንፍናዬ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሜ፣ ለእንጀራ በምሠራው ሥራ እንዲሁም ቤት ስገባ ከልጆቼ ጋር ስለምጫወት በምፈልገው ልክ አላነብም። ከዚህ ኹሉ በተረፈው ጊዜ ነው ለማንበብ ጥረት የማደርገው ሲሉ ይገልጻሉ።

ሰው በአካል እንደሚያድገው ኹሉ በአዕምሮውም ማደግ ስላለበት፣ በንባብ ማለፍ እንዳለበትና የማያቋርጥ የንባብ ሕይወት ሊኖረውን እንደሚገባ የሥነጽሑፍ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የህትመት ዋጋ መናር ባለው የኑሮ ጫና ላይ ሰዎች መጽሐፍ እንዳይገዙና እንዳያነቡ ያደረገ ትልቅ ችግር መሆኑን ደራሲዎቹም ሆነ አንባቢያን ይገልጻሉ።

በመጪው አዲስ ዓመት መጽሔት ለማሳተምና ለአንባቢያን ለማድረስ ዕቅድ የያዙ እና ሥማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ግለሰብ እንደሚሉት፣ የገጽ ብዛቱ 24 የሆነ 500 ፍሬ መጽሔት ለማሳተም (የውጭ ሽፋኑ ብቻ ባለቀለም የሆነ)፣ ከ50 እስከ 75 ሺሕ ብር ይጠይቃል። ይህም አንዱ መጽሔት ውድ በሚባለው ዋጋ በ30 ብር ቢሸጥ፣ ከ35 ሺሕ እስከ 60 ሺሕ የሚደርስ ኪሳራ አለው። ኪሳራው የሚሞላው በማስታወቂያ ገቢ ሊሆን ነው። በተለይ ለጀማሪ መጽሔት ደግሞ ማስታወቂያ ማግኘት በጣም ፈታኝ ነው ይላሉ።

የህትመት ዋጋ በእጥፍ የጨመረ እንደሆነና አንድን መጽሐፍ አምስት ሺሕ ገደማ ኮፒ ለማሳተምም እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚደርስ ዋጋ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ ያለው የወረቀት ዋጋ በእጅጉ ማሻቀብና የነጋዴዎች ያልተገባ ትርፍ ፍለጋ ይህን ትልቅ የሥነ ጽሑፍ መስክ አክስሮታል ነው የሚሉት።

ስለሆነም፣ የዚህን ዘርፍ ችግር ለመቅረፍ በአገር ደረጃ ትኩረት ያልተሰጠው በመሆኑ፣ በትውልድና አገር ላይ እያደረሰ ያለው ኪሳራ የከፋ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

የመረጃ መጥለቅለቅ፣ ቤተ መጻሕፍት በበቂ ሁኔታ አለመኖርና ያሉትም በትምህርት ተኮር መጻሕፍት ብቻ የተሞሉ መሆን እንዲሁም የህትመት ዋጋ መናር የማኅበረሰቡን የንባብ ሕይወት ፈተና ውስጥ የከተቱ ስለመሆናቸው ይነሳል።

እንደ አገር ኢትዮጵያም በበርካታ ችግሮች የመተብተቧ ምክንያት የማኅበረሰቡ በተለይም የወጣቱ ማኅበረስብ ክፍል የእውቀት ማነስና የአመለካከት ውድቀት መሆኑ ተደጋግሞ ይነሳል። ለዚህም ማኅበረሰቡ ያለው ያነሰ የንባብ ልምድ ነው ተብሎ ይወሰዳል።

የማኅበረሰቡን የንባብ ባህል ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎችን የሚጠይቅ ሲሆን፣ መንግሥትና የተለያዩ ተቋማትም ይህ ይመለከታቸዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ምንም እንኳን ለንባብ የተሰጠው ትኩረት እስካሁን እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ይህ እንዲሻሻልና አንባቢ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የሚሠሩ አካላትም አሉ።

ከዚህ መካከል አራት ዓመታትን የተሻገረው ‹‹ንባብ ለህይወት›› ዓውደ ርዕይ አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል። ይህን የንባብ ሽርሽር የተሰናዳው በመዲናዋ አዲስ አበባ ሲሆን፣ ከሐምሌ 28 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 2/2014 በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ዝግጅቱም በአዲስ አበባ ኤግዚቪሽን ማዕከል የሚካሄድ ሆኖ፣ አዳዲስ መጻሕፍት በቅናሽ የሚሸጡበት፣ ከ50 በላይ መጻሕፍት የሚመረቁበት እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኤሌክትሮኒክስ መጽሐፍት (e-books) በነጻ የሚገኙበት ስለመሆኑ ታውቋል።

ባለፈው ዓመት ከሐምሌ 21 እስከ 25 መካሄዱ ይታወሳል። በመጽሐፍት ዓውደ ርዕዩ አድራሻቸው የጠፉ መጽሐፍት ይገኛሉ፣ ያሉትም በቅናሽ ይቀርባሉ።

ደራሲያንና ጸሐፊዎች ከአንባቢዎች ጋር የሚገኛኙበት መድረክ ስለመሆኑም ተመላክቷል።

በርከት ያሉ አሳታሚዎች እና ሌሎች ተቋማትም በዝግጅቱ ተገኝተው ራሳቸውን ለመግለጽና ለማስተዋወቅ እድል እንደሚያገኙ ነው የተገለጸው። ለአብነትም ብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተመጽሐፍት የኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ቅርሶችን እንዲሁም የሥነጽሑፍ ሀብቶችን በኤግዚቪሽኑ ለዕይታ የሚያቀርብ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

እንዲህ ዓይነቱ የመጽሐፍት ዓውደ ርዕይ መርሃ ግብር ለታዳጊዎችም መልካም ገጽታ እንደሚፈጥር እና በለጋ እድሜያቸው የሚጽፉና የሚያሳትሙ ሕጻናትን አንባቢው የሚተዋወቅበት እድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።

የንባብ ለሕይወት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኤሚ እንግዳ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም አዲስ አበባ ያሉ አብዛኛው የመጽሐፍ ሻጭ መደብሮች፣ አሳታሚዎቸ፣ አከፋፋዮች እንዲሁም ምርምር ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች እና ሌሎች ይሳተፋሉ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ይህ ዓውደ ርዕይ ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው ዝግጅት ሰው ዘንድ በስፋት ተደራሽ የነበረ በመሆኑም፣ በአምስተኛው መርሃ ግብር ከዚያ በላይ ሰው ተደራሽ ይሆናል ብለን እናምናለን ያሉት ዳይሬክተሯ፣ የልጆች ማንበቢያ እንዲሁም ለታዋቂ ደራሲዎች የተዘጋጀ ቦታ መኖሩንም ጠቅሰዋል። ደራሲዎችም ለወጣቶችና ለልጆች ንግግር የሚያደርጉ መሆኑን ነው የገለጹት።

ደራሲዎችን መጠየቅ የሚፈልጉ ሰዎችም በዚህ ዝግጅት እድሉን እንደሚያገኙ አንስተው፣ ከበፊቱ በበለጠ በርካታ ኤሌክትሮኒክስ መጽሐፍት መዘጋጀታቸውን አመላክተዋል። እነዚህን መጽሐፍት ማንም በሞባይሉም ሆነ በፈለገው ነገር መውሰድ ይችላል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከተባሉ የሕፃናት ደራሲያን ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሕፃናትን መጽሐፍ ለማስተዋወቅና ለመሸጥ በዚህ ዓውደ ርዕይ ይገኛሉ። የሌሎች የመጻሕፍት ምርቃትም ይካሄዳል ብለዋል ዳይሬክተሯ።

በዝግጅቱ ሽልማት የመርሃ ግብሩ አንድ አካል ሲሆን፣ ጎተ (የጀርመን ባህል ማዕል) የሥነጽሑፍ ማዕከል ተሸላሚ የሥነፅሁፍ ባለሙያዎችን ዕጩ ማድረጉን ገልጸዋል። የመዝጊያ ስነስርዓቱ ላይም ንባብ ለሕይወት በራሱ አሠራር ዓመቱን ሙሉ ተመልክቶ ለሥነጽሑፍ የላቀ አበርክቶ ላደረጉ ባለሙያዎች የወርቅ ብዕር ሽልማት የሚሰጥ በመሆኑ፣ በዚህ ዓመት ከባለፉት በተለየ ለኹለት ተሸላሚዎች የወርቅ ብዕር እንደሚበረከት ነው የተናገሩት።

በዘንድሮው የንባብ ለሕይወት የመጻሕፍት ኤግዚቢሽን የምርምር ተቋማት በርከት ብለው የሚገኙ ሲሆን፣ ወደ አውደ ርዕዩ የሚመጡ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር አረፍ ብለው እየተዝናኑ ለማሳለፍ ምግብ አዘጋጆችም የሚገቡ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ የመጽሐፍ ዓውደ ርዕይ ንባብን ባህል ከማድረግ አኳያ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑም፣ ወደ ክልሎች ለማስፋት በሐሳብ ደረጃ መያዙን ዳይሬክተሯ አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ከህትመት ዋጋ መናር ባለፈ ለቦታ ኪራይ የሚከፈለውም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመሆኑ፣ እንዲሁም ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቅ የመንግሥት፣ የባለሀብቶች እንዲሁም የንባብ ለሕይወት ደጋፊዎች እገዛ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

- ይከተሉን -Social Media

ቀጣይነቱን አስመልክቶም በሰጡት ሐሳብ፣ ‹‹ዝግጅቱ ከባድ ውጣ ውረድ አለው፣ ቢሆንም ከዚህ በላይ እንዲያድግ እንሠራለን›› ብለዋል።

‹‹ያነበበ ትወልድ የተሻለ ያስባል፣ በዚህም የተሻለ እውቀት ሲኖረው የተሻለ አማራጮችን ማየት ይችላል። የሚያነብ ማኅበረሰብ ማዳመጥም ይችላል። ስለዚህም ማንበብን ባህል ማድረግ ጥቅሙ ይህ ነው ተብሎ ተዘርዝሮ አያልቅም።›› ባይ ናቸው።

ከዚህ አኳያ ልጆች ላይ ነው ይበልጥ እየሠራን ያለነው ሲሉ ገልጸው፣ ይሁን እንጂ ልጆችን አንብቡ ለማለት መጀመሪያ ወላጆች ማንበብ አለባቸው ብለዋል። ልጆችንን ወደ ንባብ ማምጣት ቀላል ነው፣ ባዩት ነገር ይሄዳሉ። የበቁ ወላጆችን ወደ ንባብ ማምጣት ግን ቀላል አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።

በውጪው ዓለም ልጆች ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ሲተኙ ኹሉ የሚመጥናቸው መጽሐፍ ይነበብላቸዋል። እያደጉ ሲሄዱም ከመጻሕፍት ጋር ያላቸው ግንኙነት ከፍተኛ ነው። እኛም አገር ይህን ለማምጣት መሥራት አለብን ሲሉ አስረድተዋል።

ለአምስት ቀን በሚቆየው የመጻሕፍት ዓውደ ርዕይ፣ አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ሰዎች መጻሕፍትን ገዝተው እንዲያነቡ የተሻለ አማራጭ ነው የተባለ ሲሆን፣ በመጻሕፍት ሽያጭ ከ15 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግም ተመላክቷል።

በግለሰቦች ተነሳሽነት የተጀመረው ዝግጅት ተቋማዊ አሠራር ይዞ እንዲቀጥል ጥረቶች እንደሚደረጉም ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች