በ2015 በጀት ዓመት በ250 ሚሊዮን ብር በጀት 16 የወንዝ ዳርቻ ኘሮጀክቶችን ለመሥራት እቅድ መያዙን የአዲስ አበባ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እንዳሻው ከተማው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በመዲናዋ በ2015 በጀት ዓመት 250 ሚሊዮን ብር በጀት የሚፈጁ 16 አፋጣኝ የወንዝ ዳርቻ ኘሮጀክቶችን ለመሥራት እቅድ ተይዞ ወደ ሥራ እየተገባ ነው።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለውም፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ በሚገኘው በርደሜ ወንዝ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፈረጃ ወንዝ፣ በአቃቂ ክፍለ ከተማ አካባቢ በሚገኘው ሸዋልድባ ወንዝ፣ በአፍሪካ ኅብረት ጀርባ አካባቢ በሚገኙ ወንዞች፣ በልደታ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ፍሬሕይወት ድልድይ፣ መካኒሳ አካባቢ በሚገኘው ጀርመን ድልድይ እና በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ በጥቅሉ 16 የሚጠጉ አፋጣኝ ሥራ በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች የወንዝ ዳርቻ ማልማት ሥራ ይሠራሉ ብለዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች በቅድሚያ የድጋፍ ግንቦችን በመሥራት በአረንጓዴ ልማት የማስዋብ እና በአረንጓዴ የመሸፈን ሂደት እንደሚከናወን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል።
በእነዚህ ወንዞች ላይ አፋጣኝ ሥራ ለመሥራት የታሰበው በመዲናዋ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችንና ማኅበረሰቦችን ከመታደግ ባሻገር ወንዞችን ከፅዳትና ውበት አንፃር ከሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ለመታደግ በማሰብ ነው ተብሏል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለውም፣ በ2015 በጀት ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማን ለማስዋብ 100 ሺሕ ካሬ የሚሸፍን የአረንጋዴ ልማት ይከናወናል ብለዋል።
ይህም በመዲናዋ በኹሉም ክፍለ ከተማ በሚገኙ አረንጓዴ ፓርኮች፣ በተለያዩ የመንገድ አደባባዮች እና መሻገሪያዎች፣ በመንገድ ዳርቻ ቦታዎች ላይ ከዚህ በፊት የተሠሩ ልማቶችን በመንከባከብ እና በአዲስ መልክ የማልማት ክንውን ይካሄዳል ነው የተባለው።
ለዚህም ሥራ የሚሆን አሁን ላይ 40 ሚሊዮን ብር በጀት የተለቀቀ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ተጨማሪ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚመደብም ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል።
በእነዚህ ቦታዎች ላይ ለሥነ ምህዳሩ ተስማሚ ወይም ምቹ የሆኑ የተለያዩ ውበት የሚፈጥሩ ተክሎች፣ አበቦች፣ ፅዶች እና የሳር ተከላ እንዲሁም ሌሎች የችግኝ ተከላ ሥራዎችም እንደሚከናወኑ ተጠቅሷል።
በአዲስ አበባ ከተማ በ2014 በጀት ዓመት እንዲሁ ለአደባባዮችና ለመስመር ዳር አረንጓዴ ማስዋብ ሥራ 50 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ መሠራቱ ይታወሳል።
ይህ ሥራ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበት እና አረንጓዴ ማልማት ቢሮ በተጨማሪ ሌሎች የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች እንዲሁም ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል የራሱን አሻራ ያሳረፈበት ነበር ተብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አዲስ አበባ ከተማን ውብና ጽዱ ለማድረግ በ11 አደባባዮች እና የመንገድ ዳርቻዎች ላይ ነበር የአረንጓዴ ማልማት ሥራ የተከናወነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014


