12 ኢትዮጵያዊያን በዛምቢያ ፍርድ ቤት ሕገወጥ ስደተኞች ተብለው ቅጣት ተበየነባቸው

0
810

ሕገ ወጥ ስደተኞች ተብለው በዛምቢያ መንግሥት ቁጥጥር ስር የገቡ 12 ኢትዮጵያዊያን በዛምቢያ ፍርድ ቤት እያንዳንዳቸው 10 ሺሕ የዛምቢያን ክዋቻ እንዲከፍሉ ተበየነባቸው።

ኢትዮጵያዊያኑ አገራትን አቆራርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያስኬደውን መስመር ይዘው ሲጓዙ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት። ከ15 ቀናት በፊት አይሶካ በተባለች በአንዲት የዛምቢያ ግዛት ውስጥ የተያዙት እነዚህ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ አገሪቱ ውስጥ እንደገቡ በቀጥታ ወደ ኢሚግሬሽን ቢሮ ሄደው ባለመመዝገባቸው ነው ወንጀለኛ ተብለው የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው።

የጥፋተኝነት ውሳኔው ባሳለፍነው ሳምንት የተወሰነባቸው እነዚሁ ኢትዮጵያዊያን፣ ለጥፋታቸው ቅጣት እያንዳንዳቸው 10 ሺሕ የአገሪቱን ገንዘብ (ክዋቻ) እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል። በኢትዮጵያ ብር ወደ 32 ሺሕ ብር የሚሆነውን ይህን መጠን መክፈል ካልቻሉ እስከ ዘጠኝ ወር እንዲታሰሩ መወሰኑን ሉሳካ ታይምስ ዘግቧል።

የኢትዮጵያዊያኑ ሥም በዘገባው ያልተገለጸ ሲሆን፣ ብዛታቸውና ይጓዙበት የነበረው አቅጣጫ ተጠቅሷል። በአንድ ዛምቢያዊ ጥቆማ መሠረት የአገሪቱ ፖሊስ ክትትል አድርጎ ያቋርጡታል ብሎ የገመተውን መንገድ ዘግቶ ቢጠብቃቸውም ሊያገኛቸው አልቻለም ነበር። ይህ ቢሆንም ግን መንገድ ቀይረው በሌላ አሳባሪ በኩል ማለፋቸውን የሰማው የአገሪቱ ፖሊስ ሲከታተላቸው ቆይቶ ሊደርስባቸው መቻሉ ተዘግቧል።

ስደተኞቹ ኢትዮጵያዊያን ሊያዙ የቻሉት ይጓጓዙበት የነበረ ሚትሱቡሺ የሕዝብ ማመላላሻ ተሽከርካሪ ድንገት መንገድ ላይ ተበላሽቶ በመቆሙ መሆኑ ተነግሯል። ይህን ተከትሎ የመኪናው አሽከርካሪ የሆነው ዛምቢያዊ ከአካባቢው ተሰውሮ ማምለጡ ታውቋል። ኢትዮጵያዊያኑ ግን አካባቢውን ባለማወቃቸው እዛው ቆይተው በፖሊስ መያዛቸው ታውቋል።

በእግራቸው ለማምለጥ ባለመሞከራቸው እነሱ ተይዘው ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን፣ ተሽከርካሪው ግን ወደ መንግሥት እንዲገባ ተወስኗል። በ90 ቀናት ውስጥ ባለቤቱ መጥቶ ወንጀል ሲሠራበት ለቆየበት በቂ ምክንያት ካላቀረበ መንግሥት ይወርሰዋል መባሉ ተሰምቷል።

በአይሶካ ግዛት ውስጥ የተያዙት ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች በሕገወጥ መንገድ ወደ ዛምቢያ ገብተዋል ተብለው የተወሰነባቸው በግዛቲቱ ፍርድ ቤት ነው። በአገሪቱ ከ12 ዓመት በፊት የተደነገገ የኢምግሬሽንና ዲፖርቴሽን አዋጅን ተላልፈዋል ተብለው ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት ኢትዮጵያዊያኑ፣ የቀረበባቸው ውንጀላን በመከላከል መቃወም ባለመቻላቸው ጥፋተኛ ተብለው ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

የ10 ሺሕ ክዋቻ ወይም የ9 ወር እስራት የተፈረደባቸው ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች፣ ከ24 እስከ 30 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው ተብሏል። እነሱን እያጓጓዘ የነበረው የመኪናው ሹፌር ማንነት እየተጣራ ነው የተባለ ሲሆን፣ እሱንም በቁጥጥር ስር ለማዋል ከመኪናው ጋር በተገናኘ ምርመራ እየተደረገ መሆኑም ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች በአጠቃላይ የተወሰነባቸውን ወደ 380 ሺሕ ብር ቅጣት ከፍለው ለመውጣት ስለመቻል አለመቻላቸው የተባለ ነገር የለም። ይህን ያህል ገንዘብ ይዘው እንደማይሰደዱ ቢታወቅም፣ በድህነት የሚኖሩና ሕይወታቸውን እንቀይርላቸዋለን ብለው የሸኟቸውን ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት ስለመቻላቸውም የታወቀ ነገር የለም።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የዓለም ዐቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር በጉዳዩ ላይ ምንም ያሉት ነገር ባይኖርም፣ አዲስ ማለዳ ለማግኘት ሞክራ አልተሳካላትም። ግለሰቦቹ ቅጣቱን ከፍለው አልያም እስራታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ቢገመትም፣ በምን ኹኔታ እንደሚቆዩ ግን አልታወቀም።

የዛምቢያ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ሦስት ቀናት ብቻ 51 ሕገወጥ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር አውያለሁ ብሎ ሪፖርት ቢያደርግም፣ የዜግነታቸውን ሁኔታ ከመግለፅ ተቆጥቧል። አገሪቱ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ይዛ የቀጣችና ወደ ኢትዮጵያም የመለሰች መሆኑ ይታወሳል። የኢትዮጵያ መንግሥትም በዛምቢያ የሚገኙ ኢትዮጵዊያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ እንቅስቃሴ መጀመሩን ሐምሌ አጋማሽ ላይ ማሳወቁ አይዘነጋም።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here