በኢትዮጵያ በርከት ያሉ ሐይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ በዓላት ዓመት ጠብቀው በአደባባይ በድምቀት የሚከበሩ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ በዓለም የሰው ልጅ የማይዳሰስ ቅርስነት እስከመመዝገብ የደረሱ ናቸው።
ለአብነትም ጥምቀት፣ ደመራ፣ ኢሬቻ እና ፊቼ ጨምበላላን የመሳሳሉ ደማ በዓላትን መጥቀስ ይቻላል።
በተጨማሪም በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይና በአማራ ክልል በሰፊው የሚከበረው የልጃገረዶች በዓል ሳይጠቀስ አይታለፍም።
ይህ በዓል ከቅድመ ልደተ ክርስቶስ ጀምሮ የክረምቱን ወይም የጨለማና ብርዱን መውጣት፣ የወንዞችን መጥራት፣ የአበቦችን መፍካት፣ የአዝዕርቱን ማሸትና የአዲሱን ዓመት መግባት ምክንያት በማድረግ ቅድመ እንቁጣጣሽ፤ ዘመን መለወጫ ኹለት ሳምንት ሲቀረው ጀምሮ አዲሱን ዘመን በደስታና በሀሴት ለመቀበል ልጃገረዶች በብሩህ ተስፋ ውስጥ ሆነው የሚያከብሩት ውብ ባህል ስለመሆኑ ይነገራል።
አሸንዳ/ሻደይ/አሸንድዬ/ሶለል
በክረምት ወቅት ከሚበቅለው ለምለም ተክል ሥሙን እንደወረሰ የሚነገርለት የልጃገረዶች በዓል፣ በትግራይ አሸንዳ በመባል ይታወቃል። በሰቆጣ አካበቢ ሻደይ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ በላልይበላ ደግሞ አሸንድዬ፣ እንዲሁም በቆቦ አካባቢ ሶለል በመባል እንደሚታወቅም ይነገራል።
የአሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ ወይም ሶለል በዓል የሚከበረውም በክረምቱ ወቅት ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 21 ድረስ ነው። በዚህ ጊዜም ልጃገረዶች አምረውና ተውበው በነጻነት ይጫወታሉ። ከሕጻን እስከ አዋቂም የበዓሉ መገለጫ በሆኑ አልባሳትና መዋቢያዎች አጊጠው የሚታዩበት ሰሞን ነው።
የአሸንዳ/ሻደይ/አሸንድዬ ወይም ሶለል ዓመታዊ ክብረ በዓል ከዋዜማው እስከ ማግስት ልጃገረዶች የአሸንዳ ቅጠልን አሸርጠው አደባባይ በመውጣትና በየቤቱ በመዞር ይጨፍራሉ፣ ያዜማሉ።
የፀጉር አሠራራቸው ከአልባሶ እስከ ግልብጭ፣ ጋሜ፣ ቁንጮ፣ ሳዱላና ቅርድድ ተሠርተው አደባባይ የሚውሉበት ነው።
ጌጣ ጌጣቸውም ልዩ ልዩ ዓይነት ሲሆኑ፣ ሕንቆ፣ አልቦ፣ ድሪ፣ ድኮት፣ ጉትቻ፣ ማርዳ፣ መስቀል ሲሆን፣ አለባበሳቸውም ጥልፍ ቀሚስ ፣ ሹፎን፣ ጀርሲ ታጅቦ ይታያል።
ይኸው በዓል ከአንድ አካባቢ ሌላ አካባቢ በሥያሜ ከመለያየቱም ባለፈ የአከባበር ስርዓቱም እንደሚለያይ ይነገራል።
ለአብነትም በላስታ፣ በዋግ፣ በራያ፣ በተወሰኑ የየጁ አካባቢዎች እንዲሁም በተምቤንና እንደርታ በደመቀ ሁኔታ የሚከበር ሲሆን፣ ሥያሜውም ዋግ ሻደይ ሲባል፣ በላስታ እና በተወሰኑ የራያ አካባቢዎች አሸንድዬና አሸንዳ፣ በየጁ እና በተወሰኑ የራያ አካባቢዎች ደግሞ ሶለል ተብሎ እንደሚጠራ ይነገራል።
አከባባሩ ግን የበዓሉን ልማድ የሚያጠፋ ከመሆኑም በላይ ለዛ እና ውበት የሌለው ነው የሚሉ አካላት አሉ።
አሸንድዬ ልጃገረዶች በየሰፈራቸው በቡድን በቡድን ተከፋፍለው ቤት ለቤት እየዞሩ በጭፈራ፣ በዘፈን፣ በውዳሴ ሰውን እያወደሱ ለተወሰኑ ቀናት ገንዘብ ከሰበሰቡ በኋላ ድግስ ደግሰው በድልቂያ በዘፈን ድግሳቸውን የሚበሉበት የሚቦርቁበት ባህል ነው።
ነሐሴ ሲገባ ጀምረው ልጃገረዶች እርስ በእርስ እየተገናኙ ከየእድሜ እኩዮቻቸው ጋር ቡድን መሥርተው የአሸንድዬ ቀን ነሐሴ 16 እስኪደርስ ድረስ በጉጉት እንደሚጠብቁ ይታመናል።
ልጃገረዶቹ ለአሸንድዬው ቀን በወገባቸው የሚያስሩት የተጎነጎነ ቅጠል ‹‹የአሸንዳ ቅጠል›› የሚባል ሲሆን፣ ቅጠሉ በበጋ ወራት የማይገኝና የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ የሚበቅል የበዓሉም ትልቅ ድምቀት ነው።
ልጃገረዶች በበዓሉ ዋዜማ ዕለት ቅጠሉ ካለበት ቦታ ቆርጠው ካመጡ በኋላ በወገባቸው ልክ በማሰሪያ ይጎነጉኑትና ለጠዋት እንዳይጠወልግ ጤዛ ሳር ላይ ያሳድሩታል።
በማግስቱም ልጃገረዶች ከቻሉ አዲስ አልያም ነባር ልብሶቻቸውን አጥበው ለብሰው፣ ጠጉራቸውን በሚችሉት መልኩ አበጃጅተው፣ እስከቻሉት ድረስ በሚገባ አምረው እና ተቆነጃጅተው ‹‹አሸንድዬ፣ ወፌ ይላላ›› እያሉ ሲጨፍሩ፣ ሲዘሉ ይውላሉ።
ልጃገረዶች ቀን ቀን የተጎነጎነውን አሸንድዬ ወገባቸው ላይ አስረው በየመንደሩ እየዞሩ የሚጨፍሩ ሲሆን፤ ማታ ማታ ደግሞ የተጎነጎነውን አሸንድዬ ከወገባቸው በመፍታት በሚቀጥለው ቀን ላለው ጭፈራ እንዳይጠወልግ ጤዛ ውስጥ ያሳድሩታል።
አሸንድዬ ባይ ልጃገረዶች ወደሚያወድሱት ቤት ሲገቡ አውጫዋ ልጅ ‹‹እሜቴ አሉ ደኅና ወይ›› ስትል ተቀባዮቹ ‹‹አሉ እንጂ ግቡ ይላሉ እንጂ›› ብለው በኅብረት ያዜማሉ።
ከዚያም ‹‹አሸንዳዬ፣ ወፌ ይላላ›› እያሉ በመዝፈን ስጦታውን እስኪቀበሉ ድረስ የተለያዩ የውዳሴ ስንኞች እየቋጠሩ ይቀጥላሉ።
ክብረ በዓሉ በልጃገረዶች ደማቅ ጭፈራ እና ግጥም የተሞላ ነው። ለአብነትም፦
ሳምራየ ………….. ሳምራ
ሳምራየ…………..ሳምራ
ስሽሽ…………..ሳምራ
ሳምራየ…………..ሳምራ
ሳምራ እንኩት…………..ሳምራ
እንኩትኩት…………..ሳምራ
ስወጣ…………..ሳምራ
በፎጣ…………..ሳምራ
ሳምራየ…………..ሳምራ
ስገባ …………..ሳምራ
ባጀባ…………..ሳምራ
ሰበር…………..ሳምራ
በብር…………..ሳምራ
ሳምራየ…………..ሳምራ
የመሳሰሉ ግጥሞች እየደረደሩ እስክስታ ይወርዳሉ። ጨዋታው ከደራ በኋላም ስጦታ ሲያገኙ ምስጋናቸውን በግጥም ያቀርባሉ።
ከዚህ በተጨማሪ የአሸንድዬ ጨዋታ፣ የክረምቱ ዝናብ እየቀለለ መሄዱ፣ ወቅቱ የሚፈጥረው ልምላሜ እንዲሁም የወንዞቹ ጥራት፣ ከቡሄና ሌሎች የአዲስ ዓመት መግቢያ ጨዋታዎች ጋር ተዳምሮ ወቅቱን የሚናፈቅ ያደርገዋል።
የራያ ቆቦ ወረዳ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጥላሁን አሌ፣ በዓሉ በየቦታው የተለያየ ሥያሜ እንደሚሰጠው እንዲሁም ሐይማኖታዊ ይዘት እንዳለው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ሐይማኖታዊ ይዘቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ራማ ዞብል አካባቢ ይኖር የነበረው ዮፍታሄ የሚባል ንጉሥ ለዘመቻ በሄደበት ወቅት በድል ከተመለሰ ቅድሚያ በር ላይ ያገኘውን እሰዋለሁ ብሎ ቃል ገብቶ ነበር። ይሁን እንጂ በድል ሲመለስ በሩ ላይ ያገኘው የሚሳሳላት ሴት ልጁን እንጂ በግ አልነበረም።
ቃሌን አልሽርም በማለት ልጁን ሊሰዋ ባለበት ጊዜም ልጁ ትንሽ ቀን ከጓደኞቼ ጋር እንድጫዎት ፍቀድልኝ ብላ ትጠይቀዋለች። ስለፈቀደላትም ወደ ተራራ ወጥታ አሸንድዬ ቅጠል እየቆረጠች ከልጃገረዶች ጋር እንደቦረቀችና እንደተደሰተች የሚነገር ሐይማኖታዊ ትውፊት አለ ነው ያሉት።
እንዲሁም፣ ልጃገረዶች የአሸንድዬ ቅጠሉን በወገባቸው አስረው ሶለል እያሉ ሲያሾሩት የክንፍ ቅርጽ ስለሚሠራ መላዕክት ድንግል ማርያም በክንፋቸው እያሸበሸቡ ከሸኙበትና ነሐሴ 16 ከሚከበረው በዓል ጋር ይገናኛል ብለዋል። ሶለል የሚለው ቃልም በግዕዝ ቋንቋ እልል አለ ወይም አመሰገን የሚል ትርጓሜ እንዳለው ሳይጠቅሱ አላለፉም።
በ2012 በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲሁም ባለፈው ዓመት በጦርነት ምክንያት ሳይከበር መቅረቱን ያነሱት ኃላፊው፣ ዘንድሮ ራያ አካባቢ ከጦርነቱ ነጻ የወጣ በመሆኑና ኅብረተሰቡም ታፍኖ የቆየ ስሜቱን ለመግለጽ በተለየ ድምቀት ለማክበር ታስቧል ሲሉ ተደምጠዋል።
በዚህም በበጀት ታግዞ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንዳሉና የተለያዩ እንግዶችም እንደተጋበዙ ነው የተናገሩት።
በዓሉ በቱሪዝም መስክ ለገቢ ማስገኛነት የሚያገለግል በመሆኑም፣ በ2011 የውጪ አገር ቱሪስቶች ታድመውበት ነበር። በዚህ ዓመት ግን ባለው ሁኔታ የአገር ውጪ ቱሪስት ይታደማል ብለን አናስብም ብለዋል።
ልጃገረዶች ተውበው ከሚወጡበት ጌጥ አንዱ የአሸንድዬ ቅጠል መሆኑን በማውሳትም፣ በዓሉ የልጃገረዶች የነጻነት በዓል እንደመሆኑ በዚህ ቀን ወላጆች ልጆቻቸውን እንደማያዝዙና ራሳቸው ደርበው እንደሚሠሩ ጠቅሰዋል።
በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል እሴቶችና ኢንዱስትሪ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርሃን ፀጋዬ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በዓሉን እንደወትሮው ኹሉ በድምቀት ለማክበር ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው።
እንዲሁም ከዚህ በፊት ማጠቃለያ በሚል እና የተወሰነ ልዩነት ቢኖረውም፤ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች የሚከበረውን እርስ በእርስ ለማስተሳሰር ባህር ዳር ላይ ይከበር ነበር። በዚህ ዓመት ግን ይህን ከማድረግ ይልቅ በዚያው አካባቢ በድምቀት እንዲከበር ታስቧል ነው ያሉት።
በኹሉም አካባቢዎች በማክበር ክልል ዐቀፍ እንዲሆን ከማድረግ ይልቅም ባለበት አካባቢ እሴቱን ሳይለቅ በተሻለ ሁኔታ እንዲከበር ነው የሚፈለገው ሲሉ ገልጸዋል።
በዓሉን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመውም፣ ክልሉ አስፈላጊ መረጃዎችን አሟልቶ ለሚመለከተው የፌዴራል ተቋም መላኩን አመላክተዋል።
ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ይህን በዓል በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በኩል ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ጠቁሟል።
የበዓሉ ስጋቶች
በዓሉ በጊዜ ሂደት ብዙ ጉዳት ማስተናገዱ የሚነገር ሲሆን፣ ባህላዊ አልባሳቶችና መሣሪያዎች እንደተዘረፉ ብሎም የበዓሉ መነሻው እንዳይታወቅ የሚሠሩ አካለት እንደነበሩም ይነሳል። በዓሉን በጋራ ከማክበርና በስፋት ለማስተዋወቅ ከመሥራት ይልቅ ባለቤትነትን ለመንጠቅ በተለያዩ አካባቢዎች ሽኩቻዎች ኹሉ እንደነበሩም ነው የሚደመጠው።
የጽሕፈት ቤት ኃላፊው በዓሉ በድሮው ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች በድምቀት ሲከበር የኖረ ቢሆንም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን እየደበዘዘ መምጣቱንም ያነሳሉ። ይህም የሆነው በባህል መወራረስ፣ በመበረዝና የእኔ ነው የእኔ ነው በሚል ፉክክር የተነሳ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተሰጠው ትኩረት ሕዝባዊ እየሆነና በድምቀትም እየተከበረ የመጣበት ሁኔታ እንዳለ አንስተዋል።
ዳይሬክተሯ ብርሃን ፀጋዬ ኅብረተሰቡ በዓሉ እሴቱን ሳይለቅ እንዲቀጥልና በዘመኑ ሉዓላዊነት እንዲሁም የቴክኖሎጅ ተፅዕኖ ስር እንዳይወድቅ የድርሻውን ከተወጣ ያን ያህል ስጋት አለ ማለት አይቻልም ብለዋል።
ይህ የልጃገረዶች ውብና ትውፊታዊ ጨዋታ በቦታ መራራቅ፣ በጊዜ ርዝማኔ፣ በሁኔታዎች መቀያየርና በሌሎች ምክንያቶች ከቦታ ቦታ እየተለያየ የመምጣትና በዓሉ የመጥፋት አደጋ ሁሉ ተጋርጦበት እንደነበር ይነሳል።
በዓሉ የነፃነት፣ የእኩልነትና የአንድነት ማሳያ ተደርጎ የሚታይ ሲሆን፣ በውስጡም ብዙ ያልተፃፉና ያልተነገሩ ባህሎች እሴት እንዳሉትና ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ዛሬ ላይ የደረሰ ጥንታዊና ትውፊታዊ በዓል እንደሆነም ነው የሚነገረው።
እንዲሁም በጎጃም አካባቢ ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊና ሐይማኖታዊ እሴቶች ያሉት ‹‹የእንግጫ ነቀላ›› በሚል ሥያሜ የሚታወቅ፣ ልጃገረዶች ከተፈጥሮ ጋር የሚገናኙበትና በዜማ የሚጫወቱበት ሌላኛው የልጃገረዶች በዓል በዚሁ በነሐሴ ወር ይከበራል።
ቡሄ
በየዓመቱ ነሐሴ 13 በድምቀት የሚከበረው የቡሄ በዓልም በዚህ ወቅት ሳይወሳ የሚታለፍ አይደልም።
የቡሄ በዓል መሠረቱ የክርስትና እምነት ሲሆን፣ ትርጉሙም ተገለጠ ማለት ነው።
በዓሉ በመላው ኢትዮጵያ በተለይ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በስፋት የሚከበር እንደመሆኑ፣ በገጠርም ሆነ በየከተማው ልጆች ጅራፋቸውን ገምደው ሲያጮሁ (ሲያኖጉ) ይሰነብታሉ። እናቶችም ለበዓሉ ዝግጅት ስንዴ ሲለቅሙ፣ ሲፈትጉ፣ ሲፈጩ ይሰነብታሉ።
የበዓሉን ታሪካዊ አመጣጥ የሚያውቁ ሰዎች እንደሚናገሩት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ተራራ መለኮቱን በገለጠበት እለት ጊዜው ምሽት ነበር። እረኞችም ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር። ልጆቻቸው የዘገዩባቸው ወላጆችም ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጡ።
ስለዚህም ያንን ማስታወሻ ቡሄ ለሚሉ ልጆች፣ ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ በማብራት በዓሉ የሚከበረውም ከዚህ በመነሣት እንደሆነ አዋቂዎቹ ይናገራሉ።



