በድሬዳዋ ከ600 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ተመረቀ

0
1395

ፋብሪካው በዓመት እስከ 12 ሺሕ የሚደርስ መኪና የመገጣጠም አቅም እንዳለው ተገልጿል

ቅዳሜ ነሐሴ 14 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ከስድስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጪ የተደረገበት ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግና ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግል ማህበር የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና ውስጥ ተመርቋል።

ፋብሪካውን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጅሃር፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰንዱቃን ደበበ፣ ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግና ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ በቀለ አበበ የኤልነት ቢዝነስ ግሩፕ መስራች እና ፕሬዝዳንት ኢ/ር ቶኪቻ አለማየሁ በጋራ በመሆን መርቀውታል።

ከንቲባ ከድር ጅሃር በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ እንዲስፋፋ እና መሰል በሆኑ ሥራዋች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የከተማ አስተዳደሩ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

አክለውም ድሬዳዋ ቀደምት የቴክኖሎጂ መዳረሻ  መሆኗን በመግለጽ፤ ዛሬ ድሬዳዋ ላይ የተመረቀው ፋብሪካ ድሬዳዋን አስበው ሥራ መጀመራቸው ለባለቤቶቹ በራሳቸው እና በአስተዳደሩ ሥም አመስግነዋል።

ፋብሪካው 4 ዓይነት የመኪና ሞዴሎችን የሚገጣጥም ሲሆን፤ ባለ አራት ወንበር እና ባለ ሰባት ወንበር መቀመጫ የሆኑ መኪኖችን በዓመት እስከ 12 ሺ የሚደርስ መኪና የመገጣጠ አቅም እንዳለው ተገልጿል።

ፋብሪካው አሁን ላይ ለሰማኒያ ሰራተኞች የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን፤ በቀጣይ ጊዜያቶች እስከ ሶስት መቶ ለሚደርሱ  ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጠር የኤልነት ቢዝነስ ግሩፕ መስራች እና ፕሬዝዳንት ኢ/ር ቶኪቻ  አለማየሁ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።  ፋብሪካው በሚገጣጥማቸው መኪናዎች ላይ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በአገር ውስጥ አምርቶ ሜዲን ኢትዮጵያ መኪና ለመገጣጠም  እቅድ መኖሩን ኢ/ር ቶኪቻ ተናግረዋል።

ኢ/ር ቶኪቻ አክለውም፤ ፋብሪካው በሦስት ፈረቃ በቀን 35 መኪናዋችን መገጣጠም እንደሚቻል ተናግረዋል።

ከጥቂት ዓመት በኋላም ሙሉ በሙሉ መኪናውን በአገር ውስጥ የማምረት እቅድ እንዳለም መመላከቱን ከከተማው ኮምዩኒካሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ አመላቷል።

ኤልአውቶ ኢንጂነሪንግ እና ትሬዲንግ ኃ.የተ.የግል ማህበር የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በጎረቤት አገር ኬኒያ ቅርንጫፍ ከፍቶ የሞተር መገጣጠሚያ እየሰራ መሆኑም በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here