ተሰረቅን ወይስ ተወረስን?

0
975

ግመል ሰርቆ አጎንብሶ እንዲሉ፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም 12 ቦቴዎች ተሰረቁብኝ ማለቱ ብዙዎችን አነጋግሯል። የተሰረቀ ይሰወራል፤ የእነሱ ግን በግላጭ መወሰዳቸውን የሚናገሩ፣ ተሽከርካሪዎቹ እንዴት ጂፒኤስ አልተገጠመላቸው ሲሉ ሞግተዋል።

ከዚህ ቀደም በሺሕ የሚቆጠሩ የእርዳታ መኪኖች ከትግራይ አልተመለሱም ተብሎ ከነነዳጃቸው ለጦርነት ሲውሉ እየታየ፤ አሁን ከ570 ሺሕ ሊትር በላይ የጫኑ ቦቴዎች እንዲገቡና እንዲሰወሩ ሲደረግ አስቀድሞ አልታወቀም ማለት እንደማይቻል ብዙዎች ተናግረዋል።

ምዕራባውያንና የቅርብ ጠላቶች ቢቻላቸው ምርኮኛ እያቀያየሩና የጦር መሣሪያ እኩል እያካፈሉ ይዋጣላችሁ እያሉ ቢያጫርሱን እንደሚመርጡ የተገነዘቡ ትንሽ ናቸው የሚል አስተያየታቸውን ያሳወቁም ታይተዋል፡፡ በአንፃሩ ምዕራባውያኑ ዓለም ዐቀፍ ተቋሞቻቸውን ለእኩይ ዓላማ ይጠቀማሉ ብለው የሚናገሩን ለማመን የሚከብዳቸው ብዙ መሆናቸውን የሚናገሩ በርካቶች ናቸው።

የነዳጁ ተሰረቀ መባል ጦርነቱ በጀመረ በአንድ ቀን ውስጥ መሆኑና የተቋማቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወዲያው አውቀውት መነጋገሪያ እንዲሆን ያደረጉት ከተጠያቂነት ለማምለጥ ነው የሚሉ አሉ። የዛኑ ያህል አስቀድመው ተዘጋጅተውበት ውሰዱልን እንደማለት ያስተላለፉበት መሆኑን የሚናገሩ አሉ።

በሌላ በኩል፣ ይህን ያህል መጠን ይዘው ገብተው ተሰረቀ ማለት እንደማይችሉ ያመላከቱ አካባቢውን በሚያስተዳድረው አካል ተወረሰባቸው ማለት እንደሚቀል የተናገሩ አሉ። አብዛኞች ሴራ ነው እንጂ እስካሁን ምግብ ሳያሰራጩበት መቀመጥ አልነበረበትም። ምግቡንስ ለምን ስረቁ አይሏቸውም ብለው የተቹ አሉ። በአንፃሩ ከትግራይ ሕዝብ ለማጣላት አስበው ሕዝብ በረሃብ የሚጎዳበትን ምክንያት ያገኙ መስሏቸው አሻጥር የዘረጉ ሊጠቀሙበት ነው ወሬውን ያናፈሱ የሚሉ አሉ።

አንዳንዶች ትግራይ ውስጥ ያሉ 40 ገደማ ከተሞችን እርስ በርስ የሚያገናኙ ኹሉም መንገዶችን ስንቴ ለመመላለስ ነው ይህን ያህል ሊትር ነዳጅ የተፈቀደላቸው በሚል፣ ከመጀመሪያውም ጦርነቱ በድጋሚ እንዲካሄድ አስቀድመው የተዘጋጁ መሆናቸውን የጠቆሙ አሉ። ይህን ያህል ቦቴ ነዳጅ ለጦርነቱ ሊውል ተሰረቀ ከማለት፣ ለእኩይ ዓላማ ልናውለውና ባለበት ሊወድም ስለሚችል ሕዝቡ ከነዳጅ አቅራቢያ እንዲርቅ ቢመከርም ያሉ ተሰምተዋል።

የጦር መሣሪያ ጭና ወደ ትግራይ ልትገባ ነበር የተባለች አውሮፕላን ተመታች ተብሎ የተመታችበተ ቦታና ዓይነቷ ባለሥልጣናቱንና የውጭ ሰዎችን ጭምር ማወዛገቡ ሳይቆም፤ የነዳጁ ጉዳይ መደገም ጠርጥር ያስብላል ሲሉ የሴራ ትንታኔያቸውን ያቀረቡም ነበሩ።

አጀንዳ እየሰጡ ትኩረት ለመሳብ ነው በሚል፣ ዋናው ጦርነት ያስከተለውን ችግር ከመዘገብ ይልቅ አውሮፕላንና ነዳጅ ላይ አተኩሮ ዜና አስመስሎ ፕሮፓጋንዳ ለማሰራጨት የተሄደበት ርቀት ነው በሚል የተቹም ነበሩ። ከሰሜኑ ጦርነት እኩል ኦነግ ሸኔ በአፋር ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ያን ያህል ትኩረት አለመሰጠቱ አግባብ እንዳልሆነ የሚናገሩ፣ የነዳጁ ስርቆት የተባለው ማዘናጊያ ነው ይላሉ። ያም ተባለ ይህ እርዳታው ሊደርሰው የሚገባው የትግራይም ሆነ የሌሎች ክልሎች ተረጂ በጦርነቱ ሰበብ ትኩረት እንዳይነፈገው ያስገነዘቡም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here