በመዲናዋ በሚገኙ 86 መድኃኒት ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተነገረ

0
1254

ለሽያጭ እንዳይቀርቡ የተከለከሉና ምንጫቸው የማይታወቁ መድኃኒቶችን የሸጡ 86 መድኃኒት ቤቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ምግብ መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ምግብ መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ኃይለኢየሱስ አድነው ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት፣ ከሐምሌ 1/2013 እስከ ሰኔ 30/2014 ባሉት ጊዜያት ባለሥልጣኑ ባደረጋቸው ድንገተኛ ፍተሻዎች ለሽያጭ መቅረብ የሌለባቸውን ያቀረቡ፣ ምንጫቸው የማይታወቁ መድኃኒቶችን በኮንትሮባንድ አስገብተው የተገኙ፣ ካለደረሰኝ መድኃኒቶችን የሸጡ የግል መድኃኒት ቤቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል።

ምክትል ዳይሬክተሩ አክለውም፣ 62 መድኃኒት ቤቶች ላይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 11 መድኃኒት ቤቶች ከሦስት እስከ አራት ወራት የሚደርስ የማሸግ እርምጃ እንዲሁም አንድ መድኃኒት ቤት ላይ ደግሞ የብቃት ማረጋገጫውን በመሰረዝ ከዘርፉ እንዲወጣ እንደተደረገ እና ሌሎች ተያያዥ እርምጃዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 86 የሚሆኑ የግል የመድኃኒት ቤቶች ላይ እርምጃ እንደተወሰደ ጠቁመዋል።

ከሐምሌ 1/2013 እስከ ሰኔ 30/2014 ባሉት አስራ ኹለት ወራት ውስጥ ባለሥልጣኑ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ 1 ሺሕ 220 መድኃኒት ቤቶች እና የመድኃኒት መደብሮች ውስጥ 1 ሺሕ 169 የመድኃኒት ቤቶች ላይ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ ሕግን ያልተከተሉትን በመለየት እርምጃ እንደተወሰደ ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል።

ምክትል ኃላፊው አክለውም፣ እርምጃው የተወሰደው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ በኹሉም ክፍለ ከተማ በሚገኙ የግል መድኃኒት መሸጫዎች ላይ መሆኑን ያነሱ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ በቀጣይም ድንገተኛ ፍተሻዎችን በማድረግ እና የቁጥጥር ሂደቱን በማጎልበት ይሠራል ብለዋል።

ማኅበረሰቡም ምንጫቸው የማይታወቁ፣ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ካሉ፣ ደረሰኝ እና ሌሎች ተያያዥ ሕጎችን በመጣስ ሽያጭ የሚፈፅሙ የመንግሥትም ሆነ የግል መድኃኒት ቤቶች እና የመድኃኒት መደብሮች ካጋጠሙት ለባለሥልጣኑ ጥቆማ በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ መልዕክት ተላልፏል።

በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ ከ1 ሺሕ 400 በላይ የመንግሥት እና የግል ጤና ተቋማት ያሉ ሲሆን፣ ማኅበረሰቡ መድኃኒቶችን ከመግዛቱ በፊት በተቋማት ምርመራ እንዲያደርጉ ምክትል ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ምክትል ዳይሬክተሩ አክለውም፣ የመድኃኒት ቤቶች ባለቤቶች ትርፍን እና ማኅበረሰቡን ባመጣጠነ መንገድ አገልግሎት በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ምግብ መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ከባለፈው ዓመት ጋር የማነፃፀር ሥራ ያላከናወነ ቢሆንም፣ በየዓመቱ እና በየወቅቱ በተቋሙ ተነሳሽነት እና ከኅብረተሰቡ በሚደርሰው ጥቆማ ግን የቁጥጥር ሥራ እንደሚሠራ ነው ምክትል ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

በ2013 በጀት ዓመት በተመሳሳይ በአንድ ወቅት በተደረገ ቁጥጥር ባለሥልጣኑ ድንገተኛ ቁጥጥር በማድረግ ከ10 በላይ መድኃኒት ቤቶች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዱም ተወስቷል።

በመድኃኒት ቤቶቹ በአገር ውስጥ ያልተመዘገቡ፣ ከባለሥልጣኑ ፍቃድ ያላገኙ፣ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የተከለከሉ፣ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ ያልተሰጣቸው፣ ጥራታቸውን ያልጠበቁ፣ ደኅንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ መድኃኒቶችን ሲሸጡ የተገኙ የግል መድኃኒት ቤቶች ላይ ነው እርምጃው የተወሰደው።


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here