መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበየሦስት ዓመቱ የሚደረግ የአጎበር ስርጭት በአማራ ክልል መቋረጡ ተገለጸ

በየሦስት ዓመቱ የሚደረግ የአጎበር ስርጭት በአማራ ክልል መቋረጡ ተገለጸ

በኢትዮጵያ በሚገኙ ክልሎች በየሦስት ዓመቱ የሚደረግ የአጎበር ስርጭት እንዲሁም የወባ መድኃኒት ርጭት አገልግሎት በ2014 የክረምት ወቅት በክልሉ መቋረጡን የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ በሽታ ማስወገድ ፕሮግራም ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

የአጎበር ስርጭቱ በየሦስት ዓመቱ መከናወን እንዳለበት ቢታመንም፣ በተያዘው የክረምት ወቅት ግን በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች መቋረጡን የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ በሽታ ማስወገድ ፕሮግራም አስተባባሪ ዳምጤ ላልክር ገልጸዋል።

በዘንድሮው የክረምት ወቅት ያለውን የወባ በሽታ ለመከላከል ለማኅበረሰቡ ኹለት ሚሊዮን አጎበር ለማሰራጨት ታቅዶ ነበር ያሉት ዳምጤ፤ ከጤና ሚኒስቴር ግን ምንም ዓይነት አጎበር አልደረሰንም ብለዋል።

በእቅዱ መሠረት ርጭትና የአጎበር ስርጭት ያላገኙ ስፍራዎች አሉ የተባለ ሲሆን፤ በእርዳታ እና በግዥ የሚገኘው አለመድረሱ እና የርጭት ኬሚካሉ አናሳ መሆን ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ዳምጤ ተናግረዋል።

በመሆኑም፣ አጎበርን መተኪያው ጊዜ በመድረሱ ይተካላቸዋል ተብለው በእቅድ ተመዝግበው የነበሩ በርካታ ቀበሌዎች የስርጭት ጊዜው ተላልፏቸዋል ነው ያሉት። ቢሆንም አሁንም ቢሆን ጥያቄውን ለጤና ሚኒስቴር ባቀረቡት መሠረት አጎበሩ ሲሰጣቸው ለማኅበረሰቡ እንደሚያከፋፍሉ አመላክተዋል።

ርጭትን በተመለከተም በ2014 የክረምት ወቅት በ74 ወረዳዎች የወባ በሽታ መከላከያ ርጭት ለማድረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ በእጃቸው የነበረው መድኃኒት ግን ለ13 ወረዳዎች ብቻ የሚሆን መሆኑን ነው ዳምጤ የተናገሩት።

በእቅዱ መሠረት 400 በላይ ቀበሌዎች የርጭት አገልግሎት ማግኘት የነበረባቸው ሲሆን፤ ተደራሽ የተደረጉት ግን 40 ቀበሌዎች ብቻ መሆናቸውንም አልደበቁም።

በርጭት መስፈርቱ መሠረት በተያዘው ክረምት አጣዳፊ የወባ በሽታ መከላከያ ርጭት ያስፈልጋቸው የነበሩ ሥፍራዎች ባህር ዳር አካባቢ፤ ጎንደር ዙሪያ የሚገኙ አምስት ቀበሌዎች፤ በምሥራቅና ምዕራብ ደንቢያ በለሳ አራት ቀበሌዎች፤ በአዊ ዞን አየሁ ጓጉሳ የሚገኙ ኹለት ቀበሌዎች ሲሆኑ፤ የመርጫ ጊዜው እንደተላለፋቸውም ተጠቅሷል።

ርጭት መደረግ የነበረበትም ከሰኔ ወር ጀምሮ እንደነበር ዳምጤ ተናግረዋል። አጎበር የሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ግን በወረዳ መለየት እንደማይቻልና በቀበሌ ደረጃ ግን በርካታ እንደሆኑ አንስተዋል።

በአማራ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ የጤና ቢሮዎች ለአዲስ ማለዳ በገለጹት መሠረት፣ የአጎበር እና ርጭት አገልግሎት በመቋረጡ በሽታው እንደተስፋፋ ነው። በመሆኑም በጎንደር፤ ባህርዳር እንዲሁም በሌሎች ስፍራዎች የሚገኙ የጤና ተቋማት የአጎበር እና ርጭት አገልግሎት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ዳምጤ በበኩላቸው፣ በማዕከላዊ ጎንደር፤ ጎጃም፤ ደንቢያ፤ ምዕራብና ምሥራቅ በለሳ፤ በራያ ቆቦና በሌሎች ሥፍራዎች የበሽታው ኹኔታ በሰኔ ወር ጭማሪ አሳይቶ ነበር ብለዋል። ይሁን እንጂ አሁን ክረምቱም ወደ መጠናቀቁ ስለሆነ እየቀነሰ መሆኑን አመላክተዋል።

በጤና ሚኒስቴር የወባ በሽታ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ጉዲሳ አሰፋ፣ በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የርጭት መድኃኒት እንደተሰራጨ ጠቅሰው በአማራ ክልል የተነሳውን ጥያቄ በተመለከተም ክፍተቱን በይበልጥ የሚያውቀው ክልሉ ነው ብለዋል።

በርጭት ሂደቱም ተደራሽ ያልተደረጉ ቦታዎች ስለመኖራቸው መስክረው ቁጥራቸውን መናገር ጠቃሚ አይደለም ነው ያሉት። አጎበርን በተመለከተም 300 ሚሊዮን የሚሆን እንደተሰራጨና በግዢ ሂደት እየተጠበቀ ያለ አጎበር ስለመኖሩም የጠቆሙ ሲሆን፤ በእጃቸው ሲገባ እንደሚሰራጭም ጠቅሰዋል።

አጎበር ላይ ያለ መከላከያ ኬሚካል አገልግሎቱ የሚያበቃበት ውስን ጊዜ ስላለው በሦስት ዓመት አንድ ጊዜ ነው የሚሰራጨው። ርጭትም ቢሆን አገልግሎት ላይ ለመዋል የራሱ መስፈርትና የጊዜ ገደብ እንዳለው ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች