የተማሪዎች መማሪያ ደብተር እስከ 80 ብር እየተሸጠ ነው

0
2608

የ2015 የትምህርት ዘመን ሊጀመር ጥቂት ጊዜያት በቀሩበት በዚህ ወቅት የተማሪዎች መማሪያ ደብተር እስከ 80 ብር እየተሸጠ ይገኛል።

አዲስ ማለዳ እንዳረጋገጠችው በተለይ በአዲስ አበባ ራዲካል ተብሎ የሚጠራው ባለሃምሳ ገፅ አንድ ደብተር እስከ 80 ብር የሚሸጥ ሲሆን፣ በክፍለ አገር ከተሞች መጠነኛ ቅናሽ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል።

ሌሎች ‹ዝቅተኛ› የወረቀት ጥራት ያላቸው የመማሪያ ደብተሮችም ከወትሮው በተለየ በጭማሪ ዋጋ እየተሸጡ ነው። በዚህም ባለሃምሳ ገፅ ደብተር ከ50 ብር ጀምሮ ይሸጣል።

32 ገፅ ያላቸው መማሪያ ደብተሮችም እንደጥራት ደረጃቸው ከ30 እስከ 60 ብር መሸጫ ዋጋቸው ነው። የተማሪ ቤተሰቦችም በተማሪዎች መማሪያ ቁሳቁስ አላግባብ የዋጋ መወደድ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ለሦስት ወንድሞቹ መማሪያ ደብተር ለመግዛት ከ2 ሺሕ ብር በላይ አወጣሁ ያለ አንድ ወጣት፤ ‹‹እኔ ገንዘብ ስላለኝ ገዝቻለሁ። ሆኖም በርካታ ተማሪዎች በዚህ የተነሳ ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ መንግሥት ልዩ ድጋፍ ማድረግ አለበት›› ብሏል።

በጉሊት ሥራ የሚተዳደሩ አንድ የተማሪ ወላጅ እንዲሁ በሰጡት አስተያየት፤ ‹‹የተማሪዎች ደብተር ትምህርት ሳይጀመር እንዲህ ዋጋው የተሰቀለ፣ ከተጀመረ በኋላ በጣም እንደሚጨምር ግልጽ ነው። በበኩሌ በአዲሱ የትምህርት ዓመት አምስተኛ ክፍል የምትማረው ልጄ አንዱን ደብተር ለኹለት የትምህርት ዓይነት እንድትጠቀም ነው የማደርገው። ቅድሚያ በልተን ማደር ስላለብን፤ እሱንም ከቻልኩ ነው።›› ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት የትምህርት ዘመን መጀመሪያ እስከ 40 ብር ይሸጥ የነበረ ደብተር ነው በዚህ ዓመት ከእጥፍ በላይ የጨመረው ተብሏል።

ከወራት በኋላም ዋጋው ከዚህ በላይ ሊንር ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው የተማሪ ወላጆች፣ መንግሥት እንደ ሌሎች አስፈላጊ ፍጆታዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ ከማድረግ ጀምሮ ድጎማ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሦስትና አራት፤ ከዚያም በላይ ልጆችን ለሚያስተምሩ እና ገቢያቸው ዝቅተኛ ለሆነ ወላጆች የተማሪዎች መማሪያ ቁሳቁስ በዚህ ልክ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱም በልጆች ትምህርት ላይ የከፋ ጫና ያስከትላል ነው የተባለው።

በተለይ በገጠሩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙ ተማሪዎች ችግሩ የጎላ ሊሆን እንደሚችል ነው የተገለጸው።

ይህ የተጋነነ መሸጫ ዋጋ ለደብተር ብቻ ሳይሆን የእስክሪብቶ እና እርሳስ ዋጋም በዚያው ልክ ውድ የሚባል ነው።

እንዲሁም ከመማሪያ ቁሳቁሶች በተጨማሪ ወረቀትን ጨምሮ ሌሎች የጽሕፈት መሣሪያዎች ዋጋ ጭማሪ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ከቀናት በፊት ማንኛውም የግል ትምህርት ቤት ፈቃድ የተሰጠው ለማስተማር ብቻ በመሆኑ መጽሐፍም ሆነ ደብተር መሸጥ እንደማይችል እና ይህን ሲያደርግ የተገኘ እርምጃ እንደሚወሰድበት ማሳሰቢያ መስጠቱ የሚታወስ ነው።

አዲስ ማለዳ ተማሪዎች በመማሪያ ቁሳቁሶች ዋጋ መጨመር ትምህርታቸው ላይ ጫና እንዳይፈጠር ለማድረግ ምን እየተሠራ እንደሆነ እንዲሁም ከቀረጥ ነጻ ማስገባት ስለመቻሉ ማብራሪያ ለማግኘት የትምህርት ሚኒስቴር የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ጋር ደውላ የጠየቀች ሲሆን፣ ኃላፊዋ ቀጠሮ ሰጥተው በቀጠሮው ሰዓት በተደጋጋሚ ስልክ ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 199 ነሐሴ 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here