ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአገራችን የመጀመሪያው የግል የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት እንደሆነ የተነገረለት ካቻ ዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎት አ.ማ እና በፋይናንስ ተቋማት አክስዮን የተመሰረተው ኢት ስዊች በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ካቻ ዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎት አ.ማ ከኢት ስዊች አ.ማ ድርሻ ገዝቶ መቀላቀሉ ነው የተገለጸው፡፡
የካቻ ዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎት አ.ማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም ጥላሁን የፋይናንስ ዘርፉን ለማቀላጠፍ ወቅቱ ያፈራቸውን ቴክኖሎጅዎች በመጠቀም እንዲሁም፤ በመላ አገሪቱ ወኪሎችን በማስቀመጥ ለአገራችን የባንክ እድገት የበኩላችንን እየተወጣን ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ኢት ስዊችን በመቀላቀላችን ደስታ ተሰምቶናል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህም የኹሉም ባንክ ደንበኞች የካቻን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አንድ የካቻ ደንበኛ ወደ ኹሉም ባንኮች የገንዘብ አገልግሎት ለማግኘት የኢት ስዊት አባል መሆን አለበት ካሉ በኋላም፣ አገልግሎቱን ሥራ ለማስጀመር የሚረዱ ቴክኒካል ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
አገልግሎቱን በመጠቀም የሞባይል ሂሳብ መክፈት፣ ገንዘብ ገቢ እና ወጪ ማድረግ፣ አነስተኛ ቁጠባ፣ ዋስትና የማይጠየቅባቸው አነስተኛ ብድሮች፣ አነስተኛ የኢንሹራንስ አገልግሎቶች፣ የቀጥታ ክፍያዎች፣ ዓለም አቀፍ ሃዋላ፣ ገንዘብ ማስተላለፍ፣ የሞባይል አየር ሰዓት፣ የኤቲ ኤም ገንዘብ-አልባ ግብይቶችን መከወንና ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚቻልም ተገልጿል።
ኢት ስዊች አ.ማ በኹሉም ባንኮች፣ በማክሮ ፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም ክፍያ እያሳለጡ ባሉ የፋይናንስ ተቋማት የተመሰረተ ሆኖ፣ ከአስር ዓመታት በላይ የተናበበ የፋይናንስ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑም ተመላክቷል፡፡



