ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት ወቅታዊ የፀጥታ ስጋትን አስመልክቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል።
1ኛ. በከተማ አስተዳደሩ በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚኖር ተፈናቃይ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት በኋላ ወደ መጠለያ ጣቢያውም ሆነ ወደ ከተማው መግባት ክልክል ነው።
2ኛ. በከተማው የሚገኙ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ አይችልም ክልክል ነው። ይህን ሲያደርግ የተገኘ ባለባጃጅ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበታል።
3ኛ. በከተማው የሚገኙ መጠጥ ቤቶች ምግብ ቤቶች ምሽት ጭፈራ ቤት እስከ ምሸት 2:00 ሰዓት ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ወስኗል።
4ኛ. በከተማው በሚገኙ የንግድ ቤቶች የምርት የዋጋ ጭማሪ ማድረግ በጥብቅ የተከለከለ ነው።
5ኛ. ከተፈቀደላቸው የፀጥታ ሀይሎች ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ፈፅሞ የተከለከለ ነው።
6ኛ. ከመንግስት ዕውቅና ውጭ የሚደረጉ ማናቸውም አይነት ውይይቶችና ስብሰባ ማድረግ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡
7ኛ. የጠላትን ሀሳብና እንቅስቃሴ በመደገፍ አሉባልታና ወሬን ማሰራጨት በህብረተሰቡ ላይ ሽብር መንዛት በጥብቅ የተከለከለ ነው።
8ኛ. አዳር የሚሰሩ በከተማዋ ያሉ ፋብሪካዎችና ድርጅቶች ድርጅቱ በሚሰጣቸው ህጋዊ መረጃና በፀጥታ መዋቅሩ የተረጋገጠ የይለፍ ማስረጃ ከያዘ ብቻ መንቀሳቀስ ይችላል፡፡
9ኛ. መላው የከተማው ማህበረሰብ በአደረጃጀት አካባቢውን ቀንና ሌሊት ከሰርጎ ገቦች በንቃት መጠበቅ አለበት።
10ኛ. በከተማ አስተዳደሩ ፀጉረ ልውጥ ሲያጋጥም በፍጥነት ለህግ አካል ጥቆማ በመስጠት በህግ ቁጥጥር ሥር እንዲውል ማድረግ ከማህበረሰቡ ይጠበቃል።
11ኛ. የከተማው ባለሆቴሎች እና አልጋ አከራዮች ማንነቱ ያልታወቀ የታጠቀ ግለሰብ በድርጅታችሁ ሲያጋጥማቸው ለህግ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡ ተጠይቋል።
12ኛ. በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የቤት አከራይዎች የምታከራዩትን ግለሰብ ማንነትት መታወቂያ በመጠየቅ ለይተው እንዲያከራዩ፤ የተከራዩንም መረጃ በፎርም በመሙላት ለከተማው ሰላምና ፀጥታ መምሪያ እንዲያሳውቁ መልዕክት አስተላልፏል።
ይህ የውሳኔ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፤ ከላይ በዝርዝር የተቀመጡትን የውሳኔ ሀሳቦች የሚጥስ ማንኛውም አካል ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድበትም የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር
ነሐሴ 24 ቀን 2014



