ዓለም አቀፉ የሶላር አላያንስ በኢትዮጵያ 410 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል የፀሐይ ብርሃን መሰብሰቢያ ፓርክ ልማት እየሠራ መሆኑን ገለጸ። የዓለም ዐቀፍ ሶላር ጥምረት አራተኛው የአፍሪካ ዐቀፍ ጉባዔ ከነሐሴ 23 እስከ 25/2014 ተካሂዷል።
ጉባዔው የዓለም ዐቀፍ ሶላር አላያንስ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመተባበር የተሰናዳ ሲሆን፣ ኮሚቴው በአካል ተገናኝቶ ሲመክር የመጀመሪያው ነው ተብሏል። ከጉባኤው መገባደድ በኋላ የዓለም ዐቀፉ ሶላር አላያንስ በሰጠው መግለጫ፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከፀሐይ ኃይል 410 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለማምረት እየሠራ መሆኑንና ለዚህም ከኹለት ሺሕ በላይ የፀሐይ ብርሃን ኃይል መሣሪያዎችን በመግጠም ሥራ መጀመሩን ገልጿል።
በተገጣጠሙት የፀሐይ ብርሃን መሰብሰቢያ መሣሪያዎች አማካኝነትም በአሁኑ ወቅት 1 ሺሕ 400 የውኃ መሳቢያ ፓምፖች የመጠጥ ውኃ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውም ተመላክቷል። አገሪቱ ከፀሐይ የሚገኘውን ኃይል ለመጠቀምና ለማሳደግ መንግሥት ፖሊሲዎቹን እስከ ማረም በመሄድ የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ እያበረታታ መሆኑን በማንሳት፣ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ዘርፉ ላይ ያተኮሩ 12 ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014


