“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
አገራችን የተፈጥሮና የታሪክ ሀብታም ናት። በታሪካችን ሴት መሪዎችን ከማየት ባለፈ “ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ አንዲት እንስት አለች” የሚል ብሂልም አለን። ታዲያ የዚህ ታሪክና ብሂል ባለቤቶች እንዴት እስከዛሬ ድረስ ስለ ፆታ እኩልነት እናወራለን?
በመሠረቱ እኩልነትን የምንለካበት መስፈርት እስከሌለን ድረስ በደፈናው እኩል ስለመሆን ማውራት አንችልም። “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር” ብሎ በአንድ ማህጸን ውስጥ ያደሩ ልጆችን ልዩነት የተረዳ ማኅበረሰብ፤ ስለምን ሰዎችን ለኹለት የሚከፍልን የጾታ ልዩነት መረዳት ያቅተዋል? ለነገሩ ጉዳዩ ከአገርም አልፎ ዓለም ዐቀፋዊ ነው።
ወደራሴ ሐሳብ ስመጣ፣ እኩልነትን ርዕስ አድርገን ከምንከራከር ይልቅ፣ ልዩነቱን ማጣጣም ላይ ብናተኩር ይሻላል። አብዛኛው ያገሬ ሰው የመኖሩን ምክንያት ከወለዳቸው ወይም እወልዳለሁ ብሎ ካሰባቸው ልጆቹ አንፃር ያገናኘዋል። ታዲያ ይህ የልዩነት በረከት አይደለምን?
ወንዶች ዓለምን ያለ ሴት፤ ሴቶች ደግሞ ዓለምን ያለ ወንድ መመልከት ብንችል ምናልባትም የሕይወት መሠረት ይገባን ነበር። የአንዱን ሚና አንዱ በማይወስድበት መንገድ እኩልነት ትርጉም ሊኖረው አይችልም። ታዲያ መበላለጥ አልያም እኩልነት የሚባል ሕግ የለም። በእርግጥ ሕግም ቢኖር ስለማንስማማበት መዳኛ አይሆነንም።
ሴት ልጆች አባታቸውን፤ ወንድ ልጆች ደግሞ እናታቸውን ይበልጥ ይቀርባሉ ሲባል በተደጋጋሚ ሰምተናል፣ አይተናልም። ጥናት ተጠንቶ ከግምት ያለፈ ምክንያት ባልሰማም፤ እውነት አይደለም ሲባልም አልሰማሁም።
እናቱን ተንገብግቦ እየወደደ፤ ሴትን የሚያሳንስ ወንድ ካለ ችግሩ እሱነቱ ላይ እንጂ ወንድነቱ ላይ እንዳልሆነ አምናለሁ። አባቷን ነፍሷ እስኪወጣ እየወደደች፤ ወንድ ልጅን የምታሳንስ ሴትም ካለች ችግሩ እሷነቷ ላይ ነው።
ለመሆኑ ያ የሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ስለምን ታጠፈ? መንግሥት የደረሰበትን መደምደሚያ ቢነግረን ጥሩ ነበር። በእርግጥ ከላይ ያለው ሥያሜ ተነስቶ በውስጥ የሚሠሩ ሥራዎች እንዳሉ ግልጽ ነው። የሥራዎቹን መዳረሻ ግን መፈተሽ አለብን። እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚል ግብ ካለ፤ የሀገር ሀብት በከንቱ እየፈሰሰ ነው። በጎም ተሠራ መጥፎ፣ ስኬት የሚለካው ከተነሱበት ግብ አንጻር ነውና።
እኔ ግን እላለሁ፤ ልዩነት አለ ካልን፤ ስለ እኩልነት ማውራት የለብንም። ፈጣሪ “የሰውን ልጅ በአርዓያው እንደ አምሳሉ ፈጠረ” ስንል ስለተፈጠረ አንድ ሰው ሳይሆን ለቁጥር ስለምናታክት ሰዎች ነው። ይህም በመፈጠራችን እንድንበላለጥ ሳይሆን ልዩነታችንን መሠረት አድርገን እንድንደምቅ፤ “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት” ስንባልም ልዩነታችንን እንጠቀምበት ዘንድ ነው።
“አንተ የምታውቀኝ ታጥቄ፤ እሷ የምታውቀኝ አውልቄ” እንዲሉ አፄ ቴዎድሮስ በአንድ የምናድረው ከልዩነታችን ጋር ነውና በዚሁ ልዩነታችን መድመቅ የውዴታ ግዴታችን ነው። በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት ማለት ይህም አይደል?!
ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014


