በአደባባይ በይፋ አይነገር እንጂ የጉራጌ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ ለበርካታ ዓመታት የቆየ ነው። ይህን መለስ ብለው ያወሱት ግዛቸው አበበ፣ ይህ ጥያቄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጎልቶ መውጣቱና መነሳቱ እንደ አመጸኝነትም ሆነ ለአገር ሕልውና አደጋን እንደመደቀን ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይገባ ይገልጻሉ። ‹የጉራጌ ክልል መሆን አገርን የሚያፈርስ ከሆነ የኦሮሞም ሆነ የአማራ ክልል መሆን ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም። ብሔርን መሠረት ያደረገ የክልል አደረጃጀት ራሱ ነው ሊኮነን የሚገባው› ሲሉ፣ የጉራጌ ሕዝብ ጥያቄን በአሉታዊ መንገድ መነሳቱ አግባብ እንዳልሆነ ኹለተኛና የመጨረሻ ክፍል ጽሑፋቸው እንደሚከተለው አንስተዋል።
ክፍል ኹለትና መጨረሻው
በአምባገነናዊ አገዛዘዝ ስር በከረሙ በብዙ አገራት እንደሚደረገው በኢትዮጵያም የዴሞክራሲ፣ የአገር ሉዓላዊነትና የሕዝቦች ሰላም ነቀርሳ የሆኑ የቀድሞው አምባገነናዊ ስርዓት ዋና ዋና ሰዎች በቀድሞው ቦታቸው ካሉና በነገሮች ላይ ሁሉ ያላቸውን የወሳኝነት ሚና ይዘው ከቀጠሉ ነገሮች ሁሉ ታጥበው ጭቃ ከመሆን አልፈው መሄድ አይችሉም። አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ትልቅ መሰናክል ይህ መሆኑን መጠራጠር አይገባም። ለምን የለመድኩት ጥቅማ ጥቅም ይቀርብኛል ከሚሉት ግለሰቦች ጀምሮ፣ በሠሩት ወንጀል እንዳይጠየቁ እስከሚሰጉት ግለሰቦች ናቸው ከሕወሐት ኢሕአዴግነት ወደ ብልጽግና ኢሕአዴግነት የተሸጋገሩት።
በእርግጥ አንዳንዶቹ ከተላላኪነት ወደ ላኪነት ሲለወጡ፣ ብዙዎች በዚያው በተላላኪነት ደረጃቸው ቀጥለዋል። ነገሮች በዚሁ ከቀጠሉ ነጻና እውነተኛ ምርጫ ማካሄድ፣ የቤተመንግሥት ይሁን የወረዳና የቀበሌ ሥልጣንን በሰላማዊ መንገድ መቀባበል፣ ሥልጣንንና ሹመትን ችሎታንና ብቃትን መሠረት አድርጎ በመስጠት አገርን ማሳደግ፣ ከፍተኛውን ሆነ ዝቅተኛውን ሥራ ለተገቢው ባለሙያ በመስጠት አገርን በሰላም መምራትና ማበልጸግ የሕልም እንጀራ ሆነው ይቀራሉ። ውሸት፣ ዝርፊያ (ሙስና)፣ የብዙኀኑ መራብና መደህየት፣ የጥቂቶች ከልክ በላይ ጠግቦና ተሸቀርቅሮ መኖር ይቀጥላል።
እነዚህ ነቀርሳ መሰል ችግሮች ችላ ተብለው ምርጫ ማካሄድ፣ የክልልነት ወይም የዞንና የወረዳ ጥያቄዎችን አጋንኖ በመመልከት፣ የሚጠጣና ንጽህናን መጠበቂያ ውኃ ማግኘት ከባድ በሆነበት ከተማ የሚደንስ ውኃ ተሠራ እያሉ በማጨብጨብ ወዘተ… ጊዜን ከማባከን አልፎ የትም አያደርስም። ብልጽግናም ሆነ የአገር ሉዓላዊነትና አንድነት በዚህ አይረጋገጡም። ወድቀትም አይቀሬ ነው። እነዚህን የሰላም ጸር እና የዴሞክራሲ መርዝ የሆኑ ችግሮችን ረስቶ ጉራጌዎች ክልል እንሁን አሉ ብሎ ነገሮችን ማጦዝ ምን የሚሉት መጃጃል እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
የሕወሐቱ ኢሕአዴግም ሆነ ብልጽግና ሆኛለሁ የሚለው ቁጥር ኹለት ኢሕአዴግ ተቀናቃኞቻቸውንም ሆነ በትንሽ ልዩነት ለየት ያለ አቋም የያዙ ጓዶቻቸውን ለማዳከም፣ ለማስፈራራትና ለመምታት ሲፈልጉ ‘ሕገ-መንግሥቱን መተላለፍ’ ወይም ‘ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን ለመናድ መሞከር’ የሚል ውንጀላ መለጠፋቸው የተለመደ ዘዴ ነው። ነገር ግን፣ የሕወሐቱ ኢሕአዴግም ሆነ ብልጽግና ሆኛለሁ የሚለው ቁጥር ኹለቱ ኢሕአዴግ፣ ብልጽግና ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን በመሸራፍና ሕገ-መንግሥቱ ለሕዝቦች አጎናጽፏቸዋል የሚባሉትን መብቶች በአደባባይ፣ ዐይን ካወጣ ማንአለብኝነት ጋር ሲነጥቋቸው ማየትም የተለመደ ነገር ነው። ሕገ-መንግሥታዊ ናቸው የሚባሉ የሕዝቦች መብቶች ከሚጣሱባቸው በርካታ አጋጣሚዎች መካከል እንደኛው የክልልነት ጥያቄዎችን ማንሳት ነው። እነዚህን መሰል ጥያቄዎች እስከ 2010 ታፍነውና የጭፍጨፋ መንስኤዎች ሆነው ቀጥለዋል።
ለውጥ መጣ ከተባለበት ከ2010 የመጨረሻ ወራት ጀምሮ እነዚሁ ጥያቄዎች ሲነሱ በአፈ ጮማነት ደልሎ ለማለፍ መሞከር፣ ጥያቄ ያነሱ ወገኖችን በመከፋፋል ጥያቄው እንዲከሽፍ ማድረግ፣ በዚህ ካልተሳካም የቆየው ኢሕአዴጋዊ ክፉ ባህሪ አገርሽቶ ጥያቄዎችን በጉልበት ለማፈን መሞከርና ደም የሚያፋስሱ እርምጃዎችን በመውሰድ ሕዝቦችን ጸጥ ለማሰኘት ጥረት ማድረጉ ባለበት ቀጥሏል። ይህ የአፈናና ሕዝቦችን ጥያቄ የመደፍጠጥ አሠራር ሰፍኖ በሚታይበት ጊዜ ነው አገር እየተሻገረች ነው፣ ብልጽግና እየመጣ ነው ወዘተ… የሚሉ ቡረቃዎች የሚታዩትና የሚሰሙት።
በእርግጥ መሻገሩንም እየተሻገርን ሊሆን ይችላል! ነገር ግን ‘የምንሻገረው ከየት ወደ የት ነው?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ወደ ብልጽግናና ዕድገት እየተሻገርን ነው የሚለውን የብልጽግና ቡድን መግለጫ የሚቀበሉ ሰዎች ባይታጡም፣ ከመጥፎ ወደ በጣም መጥፎ ዘመን እየተሻገርን ነው የሚሉ ወገኖች መኖራቸውም የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህ ወቅት ወደ የት እየተሻገርን ነው ብሎ በግርምት ቆም ብሎ የመጠየቁን ተራ የጉራጌ ሕዝብ እንዲሆን አድርጎታል።
ደቡብ ኢትዮጵያ ተብሎ በሕወሐት/ኢሕአዴግ በተጠረነፈው ክልል ውስጥ የሚነሳው የክልልነት ጥያቄ እንደቀጠለ ነው። የሲዳማ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ የኋላ ኋላ ምላሽ ቢያገኝም፣ የሲዳማ ሕዝብ የመረጠን ወኪሎቹ ነን ባዮቹ የደኢሕዴን ሹማምንት ራስ ወዳድነትንና አድርባይነትን በማስቀደማቸው ጥያቄው ለመክሸፍ ተቃርቦ እንደነበረ አይዘነጋም። የዞኑ አመራሮች ሕዝቡን በተለይም ወጣቶቹን የሚያጋፍጥ አቋም በመያዛቸው የብልጽግና አፈሙዝ ወደ ሲዳማ ሕዝብ አቅንቶ፣ የሕዝቡ በተለይም የአንቂዎቹና የወጣቶቹ ጽናት ሸብረክ ባለማለቱ ጉዳዩ በርከት ያለ የሕይወት ግብርን ካስከፈለ በኋላ ሲዳማ ክልል እውን መሆኑ የሚረሳ አይደለም።
ተመሳሳዩ ጥያቄ በወላይታ ሕዝብ ቀርቦ የወላይታ አመራሮች ከሕዝባቸው ጎን ቆመው መታገላቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። የወላይታ ዞን አመራሮች ከሕዝባቸው ጎን መቆማቸው የሚያስመሰግናቸውና ታሪክም ሲዘክረው የሚኖርና የማይረሳ ቆራጥነት ነው። ቢሆንም ቀድሞውንም ቢሆን ክልሎቹን እንዳሻው የጠፈጠፈው ሕወሐት ገና ከመጀመሪያው የወላይታን ሕዝብ የክልልነት መብትን የነፈገ እሱ መሆኑ እየታወቀ፣ ሕወሐት በሌሎች ሕዝቦች ላይ እንዳደረገው በፌዴራሊዝም ሥም በወላይታ ሕዝብ ላይም የእጅ አዙር አገዛዙን ጭኖ የኖረ መሆኑ ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ የወላይታ ዞን አመራሮች ለፌዴራሊዝም ስብሰባና ስለ ወላይታ ክልልነት ለመምከር የሚል አጠያያቂና ግራ አጋቢ ጉዞ ወደ መቀሌ አድርገው ነበር።
በዛም ከሕወሐት ጋር በመሞዳሞዳቸው፣ አንዳንድ የወላይታ አንቂዎችና ምሁራን ከልክ ያለፈ መወድስ ለሕወሐት እያሰሙ ለብልጽግናዎች ያላቸውን ንቀትና ጥላቻ ማሳየታቸው እንደ ጥቃት ተቆጥሮ ጥርስ እንዲነከስባቸው፣ ወደ ዘብጥያ እንዲወረወሩና የወላይታ የክልልነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያጣ አድርጓል።
የብልጽግና ቡድን ለሕገ-መንግሥቱ መከበር እንደቆመ፣ ሕገ-መንግሥቱ ብዙ ሕይወት ተከፍሎበት የተገኘ ሰነድ ስለሆነ ጥብቅና እንደሚቆምለት በተደጋጋሚ የተናገረ ቢሆንም፣ ሕገ-መንግሥቱን መሠረት ያደረጉ የክልልነት ጥያቄዎች በተነሱ ቁርጥ ጥያቄዎቹን በክፉ ዐይኑ ማየቱን ቀጥሎበታል። በሌላ በኩል ደግሞ በሕገ-መንግሥቱ ላይ የተደነገገ አካሄድ ባይሆንም፣ የክልልነት ጥያቄ ከሚያቀርቡ ሕዝቦች ጋር እልህ የተጋባ የሚመስለው ብልጽግና፤ ክላስተር የተባለ የክልል ፈጠራ ስርዓት የዘረጋ መስሎ እየታየ ነው።
ቀደም ብሎ የተከናወነው ደቡብ-ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምሥረታና አሁን ደግሞ ቀሪውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወደ ኹለት ክልል ለመገምደል የተጀመረው ሂደት ይህን እልኸኝነት የሚያሳይ ይመስላል። እልኸኝነቱ ብልጽግና አከብረዋልሁ ከሚለው ሕገ-መንግሥት ጋር በሚጻረር መልኩ የሕዝቦችን፣ የብሔሮችንና የብሔረሰቦችን መብት የሚያፍን ነው።
ጉዳዩ በጩኸት ባይስተጋባም፣ የጉራጌ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ ለበርካታ ዓመታት ሲቀነቀን የቆየ ነው። አሁን ወቅቱ ደቡብ ኢትዮጵያ የሚባለው ክልል ከመፈራረስ የማይድን መሆኑ በግልጽ የሚታይበት ጊዜ ነውና የጉራጌ ሕዝብ አጋጣሚውን የራሱን እድል በራሱ እንዴት ሊወስን እንደሚገባ ለማጤን መነሳሳቱ እንደ አመጸኝነትም ሆነ ለአገር ሕልውና አደጋን እንደመደቀን ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም። የብልጽግና ቡድን፣ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የጉራጌ ተወላጅ ያልሆኑ አክቲቪስቶችና ዩቲዩበሮች የጉራጌን ሕዝብ የልብ ትርታ ማዳመጥ ሲገባቸው፣ ጥያቄውን ኢትዮጵያን የማፈረስ አንድ እርምጃ አድርገው ወሬአቸውን ሲቆልሉበት እየሰማን ነው።
የጉራጌ ክልል መሆን አገርን የሚያፈርስ ከሆነ የኦሮሞም ሆነ የአማራ ክልል መሆን ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልምና የጉራጌን ሕዝብ ጥያቄ ሊያጣጥሉና በአሉታዊ መንገድ እንዲታይ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ‘አገሪቱን ማፍረስ ያለብንማ እኛ ብቻ ነን’ ብለው እየተሟገቱ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
የሕወሐት/ኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት በሙሉ ቁመናው ሰፍኖ በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ በዘር (በጎሳ) ላይ ተመሥርቶ የተከለለ ክልልን ወይም ዞንን ወይም ወረዳን ለማግኘት መነሳሳት አይቀሬ ጉዳይ ነው። አንዱ በዘሩ ተከልሎ ጥቅሙን ሲያሳድድ ሌላውን እድሜ ልክህን የበይ ተመልካችና ተፐውዘህ ኗሪ ሁን ማለት ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይደለም። አንዳንዶች ነገሩን ሊገልጹ እንደሚሞክሩት ጉዞው አንድ ብሔር አንድ ክልል ወይም ሰማንያ ኹለት ክልል የማዋለድ ነው የሚሆነው።
ሌላው አማራጭ ደግሞ አገሪቱን ክልል በሚባሉ ትልልቅ ግዛቶች የተሸነሸነች ብቻ ለማድረግ ከማሰብ ለትንንሽ ብሔረሰቦች ወይም ጎሳዎች ራሳቸውን በራሳቸው በቋንቋቸው የሚያስተዳድሩበትና የሌሎች ብሔረሰቦች ጥገኛ ሆነው እንደ እንጀራ ልጅ ከሚቆጠሩበት አከላለልና አገዛዝ ነጻ እንደሆኑ አድርጎ እንዲሰማቸው የሚያደርግ አወቃቀር መፍጠር ተገቢ ነው። ይህን መሰል ነገርን ታሳቢ ማድረግ የሚገባው ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያን ብሔራዊ የሆነ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ያላት አገር ማድረጉ፣ የአንድ ብሔር ተወላጅ ወደ ሌሎች ሕዝቦች ክልል ሄዶ ገዥ ወይም አስተዳዳሪ ማድረጉና የመሳሰሉት፣ በፌዴራሊዝም ሥም በሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት እንደ ነውር፣ እንደ ጭቆና፣ እንደ አሀዳዊነት፣ በእነሱ ቋንቋ ከተጠቀምክ የእነሱ ተገዥ (የእነሱ ባሪያ) ሆንክ የሚል ዓይነት ስሜት በከባዱ ያረበበ በመሆኑ ነው።
አሁንም አሁንም፣ ደግሞና ደጋግሞ ሕዝቦች የየራሳቸው ክልል እንዲኖራቸው የሚፈልጉት ለምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። የክልል ጥያቄዎች በተነሱ ቁጥር የበጀት ችግርን ከማውሳት፣ አገርን ሊበትኑ ነው ብሎ ሕዝቦችን ከማማት ወጣ ብሎ የሕዝቦችን የልብ ትርታ ማዳመጥ ተገቢ መሆኑን ለራስ መንገር ይገባል። በተለይ ደግሞ ሕወሐት ብሔራቸውን በክልል ያደራጀላቸው አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞችና ምሁራን ሌሎች ሕዝቦች እነሱ በጸጋ የተቀበሉትን ወይም ይቅርብን ብለው ያልተቃወሙትን መብት ሌሎች ሲመኙት ሰበባ-ሰበብ እየደረደሩ ነገሩን በመቃወም መተቸትም ይሁን አደገኛነቱን ለመተንተን መጣደፍ አይገባቸውም።
ማንኛውም ወገን፣ ይህ ክልል የሚባለውን የቋንቋና የዘር አደረጃጀት የሚፈቅድ ሕገ-መንግሥት በሥራ ላይ እስካለ ድረስ አንድ ብሔረሰብ ብቻውን ተነጥሎ ክልል መሆኑ በብዙ መንገድ ያንን ብሔረሰብ እንደሚጠቅመው፣ የክልሉን ሀብትና የሥራ ዕድል ያለ ብዙ ተቀናቃኝ ቋንቋውን ለሚችሉ አባላቱ ብቻ እያከፋፈለና እያዳረሰ ተጠቃሚነቱን ሊያሰፋ እንደሚችል፣ ድህነትንና ሥራ አጥነትን በእጅጉ ሊቀንስ እንደሚችል ስለሚያውቅ የሚያነሳው መሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው።
ይህን መሰሉ አስተሳሰብ ስስታምነት ነው ሊባል ቢችልም፣ ስስታምነቱ ሕገ-መንግሥታዊ መሆኑን፣ በዚህ ስስታምነት ትልቅ የሕዝብ ቁጥርና ሰፋፊ ምድር የያዙ በርካታ ብሔረሰቦች እየተጠቀሙበት መሆኑን፣ እነዚህ የየራሳቸውን ክልል ያገኙ ትልልቅ ብሔረሰቦች የሌሎችን ትንንሽ ብሔረሰቦች የሥራ አጥነትና የሀብት ችግር ለማቃለል በጭራሽ እንዳያስቡ ተደርገው የተደራጁ መሆኑን፣ ይህን ዘመናዊ ስስታምነት ሊገታ የሚችል ሕግና ሕገ-መንግሥት እንዳይኖር መደረጉንና የመሳሰሉት አሳማኝና ወሳኝ ምክንቶች ትንንሾቹ ብሔረሰቦችንም በስስታምነቱ እንዲጠቀሙበት መገፋፋቱና ማነሳሳቱ አይቀሬ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። አሠራሩ ሕገ-መንግሥታዊ መብት ተብሎ ከጸደቀና በሥራ ላይ ከዋለ ደግሞ ስስታምነቱን የፈቀደው ሕገ-መንግሥቱ ነው ማለት ይቻላል።
ከዚህ ሌላ ግን አንድ ብሔር ብቻውን ክልል ሲሆን በቋንቋው በሁሉም ዘርፍ መጠቀሙን፣ ቋንቋውንና ባህሉን ማሳደጉን ወዘተ… ከሌሎች በተለይ ደግሞ ተረኞች ነን ከሚሉ ወገኖች የሚደርስበትን ጣልቃ ገብነትና ተጽዕኖ በእጅጉ እንደሚቀንስለት ታሳቢ ማድረጉ ሊዘነጋ አይገባም። አሁን በገሃድ እንደሚታየው የየራሳቸው ክልል የተሰጣቸው ትልልቅ ብሔረሰቦች በአቅራቢያቸው የሚገኙ ትንንሾቹን ብሔረሰቦች ለመዋጥ፣ ምድራቸውን ለመጠቅለል፣ የተፈጥሮ ሀብታቸውን ለመሻማት፣ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን በማጥፋት ሕልውናቸውን አደጋ ላይ ለመጣል የሚያስችላቸው ሰፊ ዕድል ያለ መሆኑንና በርካታ ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑንም መዘንጋት አይገባም።
የቋንቋ ፌዴራሊዝም እስከሰፈነና ጎሳ ተኮር ‘የግዛት’ አደረጃጀት እስከቀጠለ ድረስ ክልልን የማጥራቱ ሥራ በግልጽም ሆነ በስውር መካሄዱ ቀጣዩ እርምጃ መሆኑ አይካድም። የጎሳ ክልልነቱ መብት ሲገኝ የብሔረሰቡን ቋንቋ የክልሉ የሥራ ቋንቋ ማድረግ የመጀመሪያው ሥራ ነው። ከዚያም በመጀመሪያ ከፍተኛ የሹመትና የሥልጣን ቦታዎችን፣ የየትንንሽና ትልልቅ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊነቶችን ጨምሮ የዚያን ክልል ቋንቋ ከማይችሉ ሰዎች ማጽዳትና በክልሉ ተወላጆች መሙላቱ ቀጣዩ ሥራ ይሆናል።
ይህን መሰሉ ክልልን የማጽዳት ሥራ ኅብረተሰቡን በቋንቋው ማገልገል ይገባል በሚል ምክንያት ወደ ታችኞቹ የሥራ እርከኖችም ጭምር መውረዱ አይቀሬ ነው። የማስተማር፣ የሕክምና፣ የፍርድ ቤት፣ የፖሊስ ወዘተ…የሥራ መስኮች ቀስ በቀስ በብሔረሰቡ ተወላጆች ሊሞሉ የሚገባቸው የሥራ ዕድሎች ይሆናሉ። ክልሉ የክልልነት መብት እንዳገኘ ከሌሎች ብሔረሰቦች ለሚመጡ ወገኖች ክፍት ሥራ ዕድል የማግኘት አጋጣሚያቸው በይፋ ዜሮ ይሆናል። በስውርና በውስጥ ለውስጥ አሠራር ደግሞ የዚያን ክልል ቋንቋ ቢችልም፣ የዚያ ብሔረሰብ ተወላጅ ካልሆነ የሥራ ዕድልን እንደሚሻማ አረም ተቆጥሮ በዘዴ ገለል ይደረጋል። ይህ አሠራር ሕወሐት/ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ በትግራይና በኦሮምያ ክልሎች በሰፊው መተግበሩ የሚረሳ አይደለም።
የትግራይ ክልል መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች የሠራተኞች ስታትስቲካል መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በክልሉ በሥራ ላይ የሚሰማሩ ትግረኛ ተናጋሪ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊያን ብዛት በፍጥነት እያሽቆለቆለ መጥቶ በብዙ መሥሪያ ቤቶች ቁጥሩ በዜሮ ወይም በአንድ፣ በኹለትና በሦስት የተገደበ ወደ መሆን ደርሷል። አዳዲስ ሠራተኞች ሲቀጠሩ የክልሉን የሥራ ቋንቋ መቻል ከመመዘኛዎቹ አንዱ ስለሚሆን፣ የሌሎች ብሔረሰብ ተወላጆች የሆኑ ነባር ሠራተኞችም ቋንቋውን ባለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን ቋንቋውን እየቻሉም የሥራ እድገትና የትምህርት እድል ማግኘት ፈተና ስለሚሆንባቸው ወደየክልሎቻቸው መሄድን እንደ ተገቢ አማራጭ አድርው ለማየት ይገደዳሉ።
በዚህም ክልሉን የማጥራት ሥራው ይቀላጠፋል። ‘የሌሎች ክልል ተወላጆች በክልላችን ኮታና በጀት ተምረው፣ ፈጥነውም ይሁን ዘግይተው ወደ ክልላቸው መሄዳቸው አይቀርም’ በሚል በአብዛኛው ትክክለኛ በሚሆን ግምታዊ አስተሳሰብ የመማርና የማደግ እድል ይነፈጋሉ። ይህ ደግሞ ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ ዜጎችን ወደ ክልሌ ልሂድ ብለው እንዲነሳሱ ያደርጋል። ይህም ክልልን ለማጥራቱ ዘመቻ ስኬት ትልቅ አስተዋጽዋ ይኖረዋል።
ፌዴራላዊ በሚባሉት መሥሪያ ቤቶችም ሆነ በግል የሥራ መስኮችም ተመሳሳዩ ዘመቻ ይካሄዳል። ቴሌን፣ ባንክ ቤቶችን፣ መብራት ኃይልንና ሪፈራል ሆስፒታሎችን በመሳሰሉ መሥሪያ ቤቶች ከሕዝባዊ አገልግሎት አሰጣጥና ከቋንቋ ጋር በተገናኘ በበርካታ የሥራ ቦታዎቻቸው ክልልን ለማጥራት የሚያስችሉ አመቺ ቀዳዳዎች መኖራቸው ግድ ነው። የክልሉን ቋንቋ የማይችል ሰው በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ፌዴራላዊ መሥሪያ ቤቶች በከፍተኛ ይሁን በመለስተኛ የኃላፊነት ቦታ ቢመደብ እንኳ ኑሮውንና የሥራ ዘመኑን አሸማቃቂ የሚያደርጉ፣ የመገለል ስሜትን የሚያጭሩ አጋጣሚዎች በርካታ ስለሚሆኑ ነገሩ ‘እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው’ ወይም ‘ሂድ አትበለው እንዲሄድልህ አድርገው’ የሚባለው ዓይነት ከመሆን የዘለለ አይሆንም። በዚህም ክልሉ ይጠራል።
ክልሉ የሌሎች ብሔረሰቦችን ተወላጆች የሚቀጥረው አስገዳጅ ሁኔታዎች ካሉ ብቻ ነው። ለምሳሌ በሥራ በከፍተኛ፣ በመካከለኛና በዝቅተኛ መስኮች የክልሉን ቋንቋ የሚችሉ የባለሙያዎች እጥረት ሲያጋጥም። በትግራይ ክልል ሆስፒታሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የኤፈርት ኩባንያዎች ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች ከሚታየው በተለየ መልኩ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች ተሳትፎ በመጠኑም ቢሆን ሰፋ ያለ ሆኖ ይታያል።
ክልልን የማጥራቱ ዘመቻ የትግራይ ክልልን ያህል በየትኛውም ክልል ተሳክቶ ማየት አይቻል ይሆናል። ይህ የሆነው ከግንቦት 1983 በኋላ በተካሄዱ የማጥራት ሥራዎች ብቻ ሳይሆን ትግራይ ክፍለ አገር በነበረበት ጊዜም የጦርነት ቦታ ስለነበረ የሌሎች ብሔረሰቦች ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው ትግራይ ተወላጆችም የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ወደ ትግራይ ላለመመደብና ወደ ሌሎች ክፍላተ አገራት ለመሄድ ከፍተኛ ግብግብ ውስጥ ይገቡ እንደነበረ የሚረሳ አይደለም።
እስከ 1983 ባለው ጊዜ እጅግ በጣም ብዙ ኤርትራውያንና ተጋሩ ወደ ሌሎች ክፍላተ አገራት ሰላማዊ ኑሮን ለመምራት በመፍለሳቸው ምክንያት በሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞችና በአንዳንድ የገጠር መንደሮች ትግራዋይና ኤርትራዊ ጎረቤት ማግኘት የተለመደ ነገር ሆኖ ነበረ። እስከ 1983 በዩኒቨርሲቲዎች፣ በኮሌጆችና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አማካኝነት ተመራቂዎች ለሥራ የሚሰማሩበት ክፍለ አገር የሚወሰነው ዕጣ በማውጣት ነበረ። በዚህ ዕጣ ወደ ትግራይ ወይም ወደ ኤርትራ ለመሄድ ‘ዱብ ዕዳ’ የገጠማቸው ተመራቂዎች የአንድና የኹለት ወር ደሞዛቸውን በመስጠት ጭምር የቦታ ቅይይር ያደርጉ እንደነበረ ማስታወስ ተገቢ ነው።
በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጦርነት ይካሄድ የነበረው በኤርትራ የነበረ ቢሆንም፣ ከኤርትራውያኑ ይልቅ የትግራይ ተወላጆች ከክፍለ አገሩ ርቀው ለመኖር ያላቸው ፍላጎት ከፍ ያለ ሆኖ መታየቱ ትንሽ ግርምት የሚያጭር ነበር። ይህ የሰሜኑ ጦርነት በመንግሥታዊ ሥራዎች ብቻ ሳይሆን በግል የሥራ መስኮችም ጭምር ወደ ትግራይ ክፍለ አገር ሄዶ ለመሥራት ማሰብን አደገኛ አድርጎት ስለነበረ ከግንቦት 1983 በፊትም ቢሆን በትግራይ የሚኖሩ የሌሎች ክፍላተ አገራት ተወላጆችን እዚህ ግባ የማይባል አድርጎት ቆይቷል። በዚህ ላይ ከግንቦት 1983 ጀምሮ ክልሉን የማጥራት ዘመቻው ሲጨመርበት ትግራይ ክልል ጠርታለች ሊባል በሚያስችል መልኩ ትግራይ የተጋሩ ብቻ መኖሪያ ሆናለች ማለት ይቻላል።
ከግንቦት 1983 በኋላ በተለይም ከ1984 ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ከተሞች የትግራዩን የመሰለ ክልልን የማጥራት ዘመቻ ጉልበትን በቀላቀለ መልኩ አልፎ አልፎ ሲተገበር መታየቱን መካድ አይቻልም። ተማሪዎች ‘ነፍጠኛ አያስተምረኝም’ ከሚሉባቸው በአንዳንድ የኦሮምያ ከተሞች ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተባረሩ ወይም ሰግተው የሸሹ ነፍጠኛ የተባሉ መምህራን ወደ ሌሎች ክፍላተ አገራት ለመመደብ የትምህርት ሚኒስትርን ግቢ ማጣበባቸው የተለመደ ክስተት ነበረ። መምህራኑ ነፍጠኛ የተባሉት አማራ ስለሆኑ ሳይሆን ኦሮሞ ባለመሆናቸው ብቻ ነበረ። ስለዚህ አማሮች ብቻ ሳይሆኑ ትግሬዎች፣ ወላይታዎች፣ ጉራጌዎች፣ አገዎች ወዘተ… የነፍጠኛነት ታርጋ እየተለጠፈላቸው ከኦሮምያ ተባርረዋል።
ይህን መሰሉ ክልልን የማጥራትና በክልል ብቸኛ ተጠቃሚ ለመሆን መቻል እንደ ልዩ በረከት በሚቆጠርበት በዚህ የኢሕአዴግ ጊዜ ብዙ ብሔረሰቦች በአንድ ክልል ታጭቀው በዚያ የተጠረነፉት ሁሉም ሕዝቦች የጋራ መግባቢያ ይኑራቸው ተብሎ የክልሉ የሥራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑና አማርኛ የሚችል ሁሉ ወደ ክልሉ እየገባ የሥራ ዕድልና ሀብት መሻማቱ እንደ መርገም መቆጠሩ ማንንም ሊገርመው አይገባም። በብዙ ቦታዎች መርገምቱ ቅሬታን መውለዱ፣ ሲዳማን በመሳሰሉ ዞኖች ቅሬታው አገርሽቶ በአቶ መለስ ዘመን የተከሰተውን የመሰለ የሎቄ ጭፍጨፋ የሚባለውን እልቂት በሲዳማ ሕዝብ ላይ ማስከተሉም የሚረሳ አይደለም።
ይህን የመሰለው ቅሬታ መፈጠሩ፣ ቅሬታው አመጽ መውለዱና ገዥ ነኝ የሚለው ቡድን የሰጠሁህን ተቀብለህ ኑር ብሎ መቆጣቱ፤ ከዛም አሻፈረኝ ያለው ከገዥው ቡድን ጋር መጋጨቱ ቀጣይ የሕዝቦች ክፉ እጣ መሆኑ ሊስተባበል አይገባውም። የሕወሐት/ኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት እና የዘርና የጎሳ ክልል አከላለል ሰፍነው በሚኖሩበት ዘመን፣ ብሔራዊ ቋንቋ መጠቀምና ሥራ ላይ መዋሉ እንደ ጭቆና በሚቆጠርበት ጊዜ፤ ክልል የመሆን ጥያቄ ማቆሚያ የሚኖረው አይመስልም። ይህን መሰሉ አገራዊ ሁኔታ መስፈኑ የአገር ውስጥ ተወዛጋቢዎችን ብቻ ሳይሆን ጎረቤት አገራትን ከዕለታት አንድ ቀን ልዩ ጥቅም እናገኛለን ብለው ያልሙ ዘንድ የሚያነሳሳ፣ ኢትዮጵያ ተዳክማና ፈራርሳ እነሱ ትልቅ አገር ሊሆኑ የሚችሉበትን በረከት በቅርቡ ሊያመጣ እንደሚችል የሚያስቡ ተስፈኛ የሚያደርጋቸው መሆኑ ግልጽ ነው።
ጅቡቲ የአዋሽ ተፋሰስ የተባለ አዲስ ካርታ የማዘጋጀቷ ጭምጭታ በሚሰማበት ጊዜ፣ ሱዳን የእኔ ነው ያለችውን መሬት በጉልበት ወስዳ ቤኒሻንጉልን ለመረከብ መቀላወጥ መጀመሯን ይፋ ባደረገችበት ጊዜ፣ የኦጋዴን ምድር የታላቋ ሶማሊያ አካል ነው ባይ መንፈስ ቢያንቀላፋም ጨርሶ አለመሞቱ በሚታወቅበት ጊዜ፣ በትግራይ ረፈረንደም ይካሄድና ታላቋ ትግራይ እውን ትሁን የሚሉ ወገኖች ጊዜው አሁን ነው ብለው የመገንጠል እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ጊዜ፣ አንዳንድ ስደተኛ የኦሮሞ ተወላጆች በአንድ በኩል ለሕወሐት እያጨበጨቡ በሌላ በኩል የኦሮሚያን ወደ ኬንያ መጠቅለል ማቀንቀን በጀመሩበት ጊዜ የእነ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እየተሻገርን ነው ማለት፣ አክቲቪስትና ምሁራን ባይ ሴቶችና ወንዶች የጉራጌን ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ ትልቅ ችግር አስመስለው የተቃውሞ ዘመቻ መጀመራቸው ‘አገሬ ሰው አጣሽ ወይ?!’ ብሎ ለመጠየቅ ወይም ለማዘን በር የሚከፍት ነው።
ግዛቸው አበበ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ይገኛሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014



