የሕወሓት ጥቃት ንጹሐንን ዒላማ ያደረገ መሆኑ ተገለጸ

0
1113

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለሦስተኛ ጊዜ የቀሰቀሰው ጦርነት በተለይ ንጹሐን ሰዎችን ዒላማ ያደረገ መሆኑን ታማኝ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ጦርነቱ በተለይም ንጹሐን ሰዎችን ዒላማ አድርጓል ያሉት በራያ ቆቦ ከተማ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ የሚሠሩ ለደኅንነታቸው ሲባል ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ሠራተኛ ናቸው።

የመረጃ ምንጩ በራያ ቆቦ ወረዳ በተለይም አራዱም ዙሪያ በአንድ ቀን ከ20 የሚልቁ ንጹሐን ተገድለዋል ብለዋል። ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ጥቃቱ አለማቆሙን አንስተው፤ የሟቾች ቁጥር ከዚህ መጨመሩ አያጠራጥርም ነው ያሉት።

በደጋው በኩል በተኩለሽ፤ ሸዎች እና በርሃ ማርያም፤ አቦሔሜዳ፤ ድልድይ እና ሌሎች ቦታዎች እንዲሁ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወጣቶች በታጣቂ ቡድኑ ሕይወታቸው ስለመቀጠፉም ተነስቷል። ታጣቂ ቡድኑ የቤት ለቤት ዘረፋ፤ ግድያ እና አስገድዶ የመድፈር ድርጊቱን ከዚህ በፊት ሲያደርገው ከነበረው ጠንከር አድርጎታልም ብለዋል።

በጦርነቱ ቀጠና የሚገኙ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ ካባለፈው ጦርነት በላቀ ኹኔታ በአሁኑ ንጹሐን እየተገደሉ ነው ይላሉ። አዲስ ማለዳ ከየአቅጣጫው ያነጋገረቻቸው ከ10 በላይ የሚሆኑ የጦርነቱ ገፈት ቀማሾች፤ ታጣቂ ቡድኑ በአፋርና አማራ ክልል ጥቃት እየሰነዘረባቸው ባሉ ቦታዎች ገና ቁጥራቸው በትክክል የማይታወቅ ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።

በራያ ቆቦ ወረዳ ሸዎች ማርያም የሚገኙ አንዲት እናት ‹‹የ12 ዓመት ልጄን ገደሉብኝ። ታዳጊው ከሚሞት እኔ አፈር ብበላ ይሻለኝ ነበር። ሮጦ ያልጠገበ ልጄን ድፍት አደረጉት›› በማለት እያለቀሱ ተናግረዋል።

የራያ ቆቦ ዙሪያ ነዋሪዎች የአላውሃ ድልድይ በመሰበሩ ሰላም ወዳለበት ስፍራ ማለፍ እንዳልቻሉ አንስተዋል። በወርቄ በኩል ጦርነቱን በመመከት የሚገኙ አርሶ አደሮች በበኩላቸው፣ በታጣቂ ቡድኑ ከኹለት ቀን በላይ በ’ዙ-23’ የጦር መሣሪያ ተኩስ እንደተከፈተባቸው ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ ‹‹አርሶ አደሩ የከባድ መሣሪያን ጦር በክላሽ እየመከተ ይገኛል። መከላከያ ግን ዞሮ አላየውም›› ሲሉ ወቅሰዋል።

ከተኩለሽ ታዳጊ ከተማ በስተምዕራብ በኩል ጎረንጎሮ፤ አቦሔሜዳ በተሰኘ ስፍራ ሰሞኑን በተተኮሰ ከባድ መሣሪያ በርካታ ንጹሐን መሞታቸውና መቁሰላቸውም ተጠቁሟል። ቡድኑ በደጋማው የሰሜኑ ክፍል ጦርነቱን አስፋፍቷል የተባለ ሲሆን፤ በተለይም በጀመዶ ማርያም እና አዘዥ አምባ ትምህርት ቤት ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች ‹‹ከቤታችን ተፈናቅለን ጫካ ለጫካ ነው ያለነው እባካችሁ ድረሱልን›› ሲሉ ገልጸዋል።

በተያያዘም መዥገር አምባ፤ ድልድይ አስቂት በተሰኙ በደጋማው የሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ነዋሪዎች ንጹሐን ተገድለዋል ብለዋል።

ጦርነቱን ከእስከዛሬው ለየት የሚያደርገው የገጠሩ ነዋሪ ላይ ጭምር ያነጣጠረ መሆኑ ነው ይላሉ ነዋሪዎቹ። ከዚህ በፊት በነበረው ጦርነት በስፋት ጥቃት ሲደርስበት የነበረው የከተማው ነዋሪ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን የገጠሩ ነዋሪም ለመፈናቀል ተገዷል ብለዋል።

ሕወሓት የመንግሥትን የሰላም ድርድር ወደኋላ በመተው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባሳለፍነው ነሐሴ 18/2014 ጀምሮ ዳግም ጦርነት መቀስቀሱን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት መግለጹ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here