በአደባባይ በይፋ አይነገር እንጂ የጉራጌ ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ ለበርካታ ዓመታት የቆየ ነው። ይህን መለስ ብለው ያወሱት ግዛቸው አበበ፣ ይህ ጥያቄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጎልቶ መውጣቱና መነሳቱ እንደ አመጸኝነትም ሆነ ለአገር ሕልውና አደጋን እንደመደቀን ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይገባ ይገልጻሉ። ‹የጉራጌ ክልል መሆን አገርን የሚያፈርስ ከሆነ የኦሮሞም ሆነ የአማራ ክልል መሆን ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም። ብሔርን መሠረት ያደረገ የክልል አደረጃጀት ራሱ ነው ሊኮነን የሚገባው› ሲሉ፣ የጉራጌ ሕዝብ ጥያቄን በአሉታዊ መንገድ መነሳቱ አግባብ እንዳልሆነ ኹለተኛና የመጨረሻ ክፍል ጽሑፋቸው እንደሚከተለው አንስተዋል።
‹ሕልምሽን ያስምረው!› ብለው የተመኙላት አገር ሕልሟ ሰምሮ የዘመንን መለወጥ በሙሉ ደስታ ብታከብረው ምንኛ በታደለች ነበር። ግን አልሆነም። ወደድንም ጠላንም እንኳንና የዘመን ለውጥ መሽቶ ሲነጋ የምትወጣውን ፀሐይ ለማየት የጠሉ ወገኖች አሉን። ወደድንም ጠላንም አሁንም አገራችን ጦርነት ላይ ናት። በዚህም የተነሳ ልጇን የምታጣ እናት፣ መበለት የምትሆን ሚስት፣ ያለወላጅ የሚቀሩ ልጆች፣ ያለጧሪ የተተዉ በእድሜ የገፉ እናቶችና አባቶች እልፍ ናቸው።
በአገራችን ባህል ደግሞ እንኳን በራስ ላይ ደርሶ፣ ጎረቤት የተፈጠረ ሀዘንም የራስ ነው። በዓል እንኳ ቢሆን አከባበሩ ሌላ መልክ ይይዛል እንጂ በድለቃ አይከበርም። የዚህ ምክንያቱ በአንድ በኩል ሰው መሆን የሚባል ነገር ነው። በሰውነት ቋንቋ ሀዘንን መጋራት፤ ደስታንም መካፈል አግባብ ነው። በዛም ላይ ሰው ነንና የሚገጥመንን አናውቅም። ነገ በእኔ የሚባል ነገር አለ። ከዛ ሁሉ ባሻገር ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ነን። አንዳንድ እንደ ጸጋ የተሰጡን ማኅበራዊ እሴቶች አሉን። አበቃ!
አሁን በአገራችን ያለው ሀዘን የጎረቤት አይደለም፤ የራስ ነው። ከጦርነት አልፎ በየቦታው የሚደርሱ ጥቃቶች በየቀኑ ንጹሐን ዜጎችን እየነጠቁን ነው። ‹ምን ስሆን በሕይወት ተረፍኩ› እስኪሉ ድረስ ዘመድ ወገናቸውን አጥተው፣ ቤታቸው ፈርሶ፣ ያፈሩት ንብረት በእሳት ተበልቶ፣ በደረሰባቸው መከራ የሰውን ጭካኔ ይሁን ወይ የአምላካቸውን ዝምታ…ማን ላይ ምን ብለው ማማረር እንዳለባቸው እንኳ ግራ ገብቷቸው ለብቻቸው የቀሩ እጅግ ብዙ ናቸው።
አእምሯቸው ታውኮ፣ ልባቸው ተሰብሮ የመኖርን ምክንያት አጥተው የሚኳትኑ እህት ወንድሞቻችን፣ ዐይናቸው ማየት የሌለበትን ዐይቶ አእምሯቸው የታመመና መታመማቸውን እንኳ የማያውቁ ለጋ ሕጻናት…እልፍ ናቸው።
ይህ ሁሉ የጎረቤት ታሪክ አይደለም። ይህ የእኛ ቤት፣ የእኛ አገር ጉዳይ ነው። ያማል፤ ልብ ይሰብራል። እንኳንና ለመሳቅና ለመጨፈር ፈገግ ለማለት እንኳ ምቾት አይሰጥም። ራስ ወዳድነት ውጦን ግድ የለሽነትን ካልመረጥን በቀር፤ እየሆነ ያለውና የሆነው የሚያስበላ የሚያስጠጣ እንኳ አይደለም።
ግን በመጨረሻ ስጋ ሰውነትን ያሸነፈ ይመስላል። አዲስ አበባን ከሰሞኑ ስታዘባት፣ ጭፈራዋ ደርቶ ስመለከት አገር ሁሉ ሰላም የሆነ ይመስላል። ወይም ‹‹ምንም ልናደርግ ስለማንችል እስከጊዜው ዝም ብለን እንደልቅ›› የመሰለ ግብር ሲፈጸም ይታያል።
የዘመን ለውጥን የተከተሉ የሙዚቃ ድግሶች ከጣት ቁጥር በላይ ናቸው። ሙዚቀኞቹ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ይህን ጊዜ ማሳለፍ የቻሉ አይመስልም። ሁሉም ላይ ለመፍረድ ወይም በአንድ ለመጨፍለቅ አይደለም። ብዙዎቹ የምናከብራቸው ድምጻውያን ጭምር ናቸው።
አዎን! ሥራቸው ነው። ግን ደግሞ ሥራ ስለሆነ ብቻ ቢሆን ሁሉም ድምጻውያን የሙዚቃ ድግስ ባዘጋጁ ነበር። ሀብታችን የሚሉት ሕዝብ በከተማ የሚገኘው ብቻ አይደለም። የተጨነቀ ከሀዘን እንዲወጣ ታስቦም ከሆነ፣ የግድ በዓልን መጠበቅ ወይም እንዲህ በሆሆታ መሆን አይጠበቅበትም ነበር።
ይህን ማለቴ ሁላችን የሀዘን ማቅ ለብሰን ተስፋ የሌለ እስኪመስል እንሁን ስል አይደለም። ተስፋ ነውና ሰውን የሚያኖረው፣ ተስፋን እናጨልም ማለትም አይደለም። ግን ለሁሉም ነገር’ኮ ልክ አለው። ነጋዴው ብሶበታል፤ ጨፋሪና አስጨፋሪው እንደ ሰዶምና ገሞራ ዘመን ‹ትንሽ ጊዜ ይቀረናል!› እያለ ‹ጊዜውን ለመጠቀም› የሚራወጥ ይመስላል።
ድለቃችንም ከጦርነት የወጣንና አንዳች ያሸነፍነው ነገር ያለ እንጂ ቅንጣት እንኳ አስተዋጽኦ ሳናደርግ ለተሰጠን አዲስ ዘመን አቀባበል አይመስልም። ይህንንም ስል በፍረጃ አይደለም። ግን ሀይማኖተኛ በሚበዛባት አገር እንደውም ሲሆን የጽሞና ጊዜ ሰጥቶ፣ የተቸገሩና መከራ ላይ ያሉ ወገኖችን እያሰቡ ቢቻል በጎ አድራጎት በመፈጸም ካልሆነ በያሉበት ዱዓና ጸሎት በማድረስ ማሰብ በተገባ ነበር። ለሱ የሚሆነውን ትዕግስትና አቅም ያጣን እንደሆነ፣ ዝም ማለትን ማን ከለከለን?
በእርግጥ አንዳንድ ከጭንቀት የሚወለዱ ድንዛዜዎች እንዳሉ ይነገራል። ዐላይም አልሰማም ብሎ በራስ ዓለም ብቻ ለመዋኘት እንደመሞከር ያለ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች ጥቂት አይደሉም። ይህም እውነቱን ለመሸሽ የሚደረግ ጥረት ሲሆን፣ ግን ወደየትም ማምለጥ እንደማይቻል እሙን ነው።
ከአገር ወዴት መሄድ ይቻላል? ጋዜጠኛ፣ ገጣሚ እና ተርጓሚ ነብይ መኮንን ‹ሀገርህ ናት በቃ!› በሚል ግጥሙ እንዲህ ይለናል፤
ሀገርህ ናት በቃ፣
ይቺው ናት ኢትዮጵያ…ይቺው ናት ሀገርህ
ብቻዋን የተኛች ከዓለም ተደብቃ፣
አኪሯ ቀዝቅዞ፣
ያንቀላፋች ውቢት ያንተው የክት ዕቃ፤
ልቧን አታውልቃት አትጨቅጭቃት በቃ፤
አብረህ አንቀላፋ ወይ አብረሃት ንቃ።
በቃ! ያለው አማራጭ አብሮ አገር የምትሆነውን መሆን ነው።
ከተሞቻችን በዓልን ለመምሰል እንዲህ ሲፍጨረጨሩ፣ በርካታ አካባቢዎች ደግሞ ነዋሪዎቻቸው ጭንቀት ውስጥ ናቸው። በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ተፈናቃዮች በዓል መድረሱን እየረገሙ ይሆናል። የቀድሞ ሕይወታቸውን፣ የሞቀ ሰላማዊ ቤታቸውን እያሰቡ፣ የተለያቸውን የሚወዱትን ወገናቸውን እያስታወሱ በጥልቅ ሀዘን ውስጥ ይሆናሉ።
ከተሞቻችን ይህን አዲስ ዓመት እነዚህን ወገኖች በሚያስብ መልኩ ቢያደርጉትና ከሆሆታው ቀነስ ቢያደርጉ ጥሩ ነበር። ግን እንዳልኩት፤ በቁዘማ ይለፍ ማለት አይደለም። ምክንያቱም የሰውን ልጅ የሚያኖረው ተስፋ ነው፤ ሕይወትም በዛ ይቀጥላል።
በዓላት በዚህ ወቅት
የሥነልቦና ባለሞያ አይደለሁም። ነገር ግን ከዚህ ጋር በተገናኘ ካነበብኳቸውና ከዚህም ከአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ከቃረምኳቸው ጽሑፎች ለማጋራት ወደድኩ። በዚህም በተለያየ አደጋ ምክንያት የአእምሮ ሕመም የሚገጥማቸው ሰዎች በዓላት ላይ ምን ዓይነት ስሜት እንደሚፈጠርባቸው መመልከት ይቻላል። ይህን መነሻ አድርገን በከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችን ያሉበትን ሁኔታ ለአፍታ እናስብና ለመረዳት እንሞክር ዘንድ እንችል ይሆናል።
አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ድረ ገጽ ላይ አንድ ቃለመጠይቅ ተመልክቻለሁ። ይህም የሥነልቦና ባለሞያ ከሆኑ ቴዎድሮስ ድልነሳው ከተባሉ ሰው ጋር የተደረገ ቆይታ ነው። በዚህም ላይ በጦርነት ወቅት ስለሚከሰት ትራውማ ተነስቷል። በዛም መካከል ባለሞያው ስላነሱት ጉዳይ እኔ ከማብራራ እንደወረደ ላስቀምጠው፤
‹‹በጦርነት ወቅት አንድ ሰው ብቻ ሳይሆን ብዙ ሰዎች ይጎዳሉ፤ ቤተሰብ ነው የሚጎዳው። አባቶችና እናቶች ስለራሳቸው ላይሆን ይችላል የሚያስቡት፣ ስለልጆቻቸው ነው። እናት ተደፍራ ‹ልጄን እንዴት ዐያታለሁ!› ብላ ራሷን አጠፋች የሚል ታሪክ በሰፊው ሲነገር ነበር።
በጦርነት ጊዜ ይህ ሐሳብ ግለሰብ ለብቻው የሚጋፈጠው አይደለም፣ እንደ ቤተሰብና እንደ ማኅበረሰብ እንጂ። የሚሰቃየው ሙሉ ቀበሌ፣ ሙሉ ወረዳ ወይ ሙሉ ከተማ ነው። ብዙ ሀብት፣ ንብረት ይወድማል። ገንዘብ ላይ ኪሳራ አለ፣ መፈናቀልም አለ። መኖሪያ ቦታ ይታጣል፤ ደኅንነት ይጠፋል። ይህ ሁኔታ ለሕክምና እንኳ አይመችም። ወደ ትራውማ ሕክምና የምንገባው ሰውየው በልቶ ጠግቦ ሲያድር ነው። አለበለዚያ ኪሳራ ነው የሚሆነው። መልሶ ይደነግጣል፤ ይጨነቃል።
እንዴት እሆናለሁ ብሎ ቢያስብም ትክክል ነው፤ መፍራትና ማሰብ አለበት። ተፈጥሮአዊ ምላሻችን ነው። የትራውማ ምልክት አለ ወይ ብሎ ለመለየት ተረጋግቶ ሲቀመጥ፣ ቤቱ ሲመለስ ወይ መጠለያ አግኝቶ ሲረጋጋ ነው ሕክምና የሚጀመረው። አለበለዚያ ትራውማ ሳይሆን ፈርቷል ወይም ደንግጧል ነው። ይህ ደግሞ ትክክል ነው። ያ ሰው መጀመሪያ ራሱን መጠበቅ አለበት። አገሩ እየተታኮሰ፣ እናቱ እየተደፈረች ወይም ወንድሙ ውጊያ ላይ ሄዶ፣ ለምን ያ ሰው ይፈራል፣ ይደነግጣል ልንል አንችልም። ምክንያቱም ክስተቱ በሂደት ላይ ያለ ነው።
ነገሩ የሚነሳው ጦርነቱ ካበቃ ከ6 ወር በኋላ አሁንም ቤቴ ፈረሰ አልፈረሰ፣ አሁንም ገብተው እናቴን ደበደቡ ወይም ገደሉ፣ አሁንም የሆነ ነገር ተፈጠረ ብሎ የሚደነግጥ ከሆነ ነው። ‹ፖስት ትራውማ› ምልክቱ ያኔ ነው የሚፈጠረው።
…አንድ ቤተሰብ ውስጥ እናት ልጇ ወይም ባሏ ወታደር ሆኖ ሄዶ ሊሞት ይችላል፤ ራሷ ልትደበደብ፣ ልጇ ልትደፈር፣ ቤቷ ሊቃጠል፣ ንብረቷ ሊዘረፍና እርሷ ተሰድዳ ሌላ ቦታ እየኖረች ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ውስብስብ ትራውማዎች ይፈጠራሉ። በዚህ ምክንያት የሚፈጠር የአእምሮ ቁስለት በኋላ ላይ ለመፍታትም ይከብዳል። በጣም ጠንከር ያለ የሥነልቦና ድጋፍ የሚያስፈልገው ይሆናል።››
ባለሞያው በዚህ ምላሻቸው ውስጥ በጦርነት ወቅት ስለሚፈጠር ስሜትና የአእምሮ ሕመም እንዲሁም የልብ መታወክ አንስተዋል። ይህ ብዙ ወገኖቻችን አሁን ያሉበት ሁኔታ ነው።
እንደሚታወቀው ለሦስተኛ ጊዜ በጀመረው የኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል ጦርነት ገና ጥይት መተኮስ መጀመሩን ተከትሎ ቤት ንብረታቸውን ትተው ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው የወጡ ሰዎች አሉ። ለእነዚህ ሰዎች አዲስ ዓመት የወቅት መፈራረቅ እንጂ ከዛ የላቀ ትርጉም የለውም።
የእነርሱ አዲስ ዓመት ይህ ቀውስ አብቅቶ፣ ስጋታቸው ጠፍቶ ልጆቻቸውን በደኅና የሚያስተምሩበት ጊዜ ነው። የእነርሱ አዲስ ዓመት ልጆቻቸው ከክፍል ክፍል ተሻግረው ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱበት ጊዜ ነው። ኢትዮጵያም የምትናፍቀው አዲስ የሆነ ዘመንና ዓመት እንዲያ ያለው ነው።
ጄምስ ዜንደር የተባሉ በአደጋ ምክንያት በሚከሰት የመንፈስ ስብራት ወይም የአእምሮ ቁስል (trauma) ክብካቤና ጥበቃ ዙሪያ የሚሠሩ የሥነልቦና ባለሞያ ‹‹Mental Health and the Holidays›› በሚል ርዕስ ያወጡት ጽሑፍ አለ። በዚህም ላይ በበዓላት ሰሞን ነባር የሆነ የመንፈስ ስብራት ወይም አእምሮ ቁስለት ላይ የባሰ መጨናነቅ እንደሚፈጠር ይገልጻሉ።
በተለይም የሚወዷቸውን ሰዎች ያጡ፣ ከመኖሪያ ስፍራቸው የተፈናቀሉ፣ ለወትሮ በበዓል ሰሞን የለመዱት ሁሉ የቀረባቸውና ወደፊትም እንደዛ ያለውን ደስታ አናገኝም ብለው ተስፋ የቆረጡ በበዓል ቀን ደስተኛ ሆነው የማሳለፍ እድላቸው አነስተኛ ነው። እናም በዓልና ግርግሩ እንደውም የባሰ የሚያስጨንቅና ቶሎ እንዲያልፍ የሚሹት ኹነት ይሆንባቸዋል።
እንቋጭ
ድለቃችንን እንቀንስ። ሆሆታ ለጽሞና አይመችም። ያለጽሞና ደግሞ ሰው ማስተዋልና ወደ ልቡ መመለስ አይችልም። አዲስ ካመጣነው ከበዛ የግለኝነት አመል ለመላቀቅም ጽሞና ያሻል። እየሆንን ሳይመስለን መሆን የሌለብንን ብዙውን ሆነናል። ቤታችን ውስጥ አንዱ ክፍል እየተለቀሰ ሌላው ክፍል እየደለቁ መጨፈር ላይ ነን። እናስተውል!
ደግሞም እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ ብዙ የቤት ሥራ አለብን። ዛሬ በጥይት ከሚያልቀው ወገናችን በላይ ነገ የጥይቱ አሻራ ያረፈበት ጠባሳችን ብዙ ሕክምናን የሚፈልግ ነው። ትውልድ ይቀየራል፤ አዲስ ትውልድ ይመጣል። በዚህ ዘመን ተጀምሮ በዚህ ዘመን የሚያልቅ ጉዳይ አይኖርም። ይህን አርቆ ማሰብ ያሻል።
ከተሞች ምን በአደይ አበባ አሸብርቀው አገር ሰላም እንደሆነ እንዲሰማን ቢያደርጉም፤ ከላይ ለበስነው እንጂ ውስጣችን ያለውን ሀዘን አይሽረውም። የኢትዮጵያ አዲስ ዘመን የሕዝቧ ልብ ለፍቅርና ለአንድነት ብሎም ለይቅርታ ቀንቶ ሰላሟ ሲመለስ ነው።
በአሁኑ አዲስ ዓመት ተፈጥሮ ራሷን አድሳለች፤ ወቅት ተቀይሯል። እኛና ልባችን እንዲሁም የምንኖርባትን አገራችንን ግን ማደስና መቀየር ይቀረናል። አዲስ ዘመናችን ያንን የምናደርግበት ጊዜ ነው። ከዚህ በላቀ ግን በየእምነታችን በአካልም በልብም የቆሰሉ፣ በጭንቀትም ለታመሙ ሁሉ ብርታትና ጽናትን ከምናምነው እንለምን። ሰላም ይስጠን!



