አርብ መስከረም 20 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የሀረሪ ክልል ጤና ቢሮ ከ20 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ በክልሉ ለሚገኙ ጤና ተቋማት ድጋፍ አደረገ።
የህክምና ቁሳቁሶቹ በክልሉ ያለውን የጤና አገልግሎትን ጥራትን ለማሻሻል ያግዛል ተብሏል።
በህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ርክክቡ ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን አብዱላሂ እንዳሉት፤ የተደረገው ድጋፍ በክልሉ ያለው የጤና አገልግሎት በተለይም የእናቶችና ህፃናትን ጤና አገልግሎት ለማሻሻል እንዲሁም የጤና መድህን ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎችን የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል።
ለዚህም የግብዓት እጥረት ያለባቸውን ተቋማት በጥናት በመለየት ክፍተቱን መቅረፍ የሚያስችል የህክምና ቁሳቁስ አከፋፍለናል ብለዋል።
የተደረገው ድጋፍም አልትራሳውንድ፣ የሆስፒታል አልጋና ሌሎች የላቦራቶሪ መሳሪያዎች ስለመሆናቸው ጠቁመዋል።
መሳሪያዎቹ ለታለመላቸው አላማ በማዋል ህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
ድጋፉ ለ15 የጤና ተቋማትና ሆስፒታሎች የተደረገ ሲሆን የህክምና ቁሳቁሶቹም ከጤና ሚኒስትር፣ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩትና ከለጋሽ አካላት የተገኘ መሆኑን ተጠቁሟል።



