“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
ከዛሬ 3000 ዓመታት በፊት የተከናወነ ድርጊት መሆኑን በርካታ መዛግብት ይገልጻሉ። አንዲት ኢትዮጵያዊት ንግሥት ጥበብን ፍለጋ በርካታ ኪሎሜትሮችን አቆራርጣ ከጠቢብና ከጥበብ ዘንድ ደረሰች።ይህ ጊዜ ሴት ልጅ ጥበብን አጥብቃ ከፈለገችባቸው ጊዜያት መካከል አንዱ ነው። ይህ ጊዜ ሴት ልጅ ለእውቀት ያላትን ከፍተኛ ቦታ የሚያሳይ አይረሴ ክስተት ነው። ለጥበብ ፍለጋ መንገድ ጠራጊ ድንቅ ጊዜ።
“ኢትያኤል” የንግሥተ ሳባ ወይም የንግሥት ማክዳ ሌላው መጠሪያ ሥም ነው። ለጥበብ የቱንም ያህል መስዋዕትነት ሊከፈል እንደሚገባ ለዓለም ያስተማረ ድንቅ ሥም። ንግሥቷ በነጋድራስ ታምሪን አማካኝነት ባገኘችው ጥቆማ መሠረት ጊዜ ሳታባክን ያላትን የጥበብ ጥም ለማርካት ከኢትዮጵያ ተነስታ ወደ እስራኤል አቀናች። በጥበብ ለጥበብ ተጉዛ ሴትነቷ ሳይበግራት እውቀትን ፍለጋ ወደ አስቸጋሪው ጉዞ በጥበብ ደረሰች።
ጠቢቡ ሶሎሞንም ለጠቢብ የሚሆን “የእንኳን ደኅና መጣሽ” መርሐግብር አዘጋጀላት፤ ለጠቢብ የሚሆንም ማረፊያ ስፍራ ሰጣት። ኢትያኤልም በተደረገላት ነገር ሁሉ ተደሰተች። ጥበብን መፈለግ ምን ያህል እንደሚያስደስትም ተገነዘበች። ከጥበብ ፍለጋ ጉዞዋ ምህንድስናን እና የአገር አስተዳደር ጥበብን ይዛ መጥታም ለአገሯ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለች። በተጨማሪም የጠቢቡንም የእሷንም የበኩር ልጅ በመውለድ አገራችን ኢትዮጵያን ከሌላ አገር ጋር በስጋና በደም አስተሳስራለች።
ከዚህ ታሪካዊ ጉዞና ከንግሥቷ በርካታ ነገሮችን እንማራለን። የመጀመሪያው ጥበብን መጠማትን ነው። አንድ ሰው ከልቡ እውቀትን የሚሻ ከሆነ ለማንም አይንበረከክም፤ ለማንም እጁን አይሰጥም፣ ለምንም አይሸነፍም። ይህ እንዲሆን ግን ፍለጋው ጽኑ፣ ፈላጊውም ጽናት ሊኖረው ይገባል። ካለበለዚያ ፍለጋው ቢጀመርም ውጤቱ አመርቂ ድርጊቱም አጽዳቂ አይሆንም። በጥበብ የሚመራ ሕዝብ ጠቢብ ይሆናል።በጥበብ ያልተማራ ሕዝብ ጠባብ ይሆናል።
ሌላኛው ለአገር የራስን አስተዋጽኦ ለማበርከት የታለመን አስደሳች ሐሳብ ያመለክታል። በተለይ በአሁን ሰዓት በየቦታው ለሚታየው አገር የማፍረስ ፍሬ-አልባ ጉዞ፤ ይህ ሳባዊ ጉዞ መፍትሄው ነው። አገርን ለማሠልጠንና ከሥልጡናን ጎራ ለማሰለፍ ርቀትና እናግልት የጉዟችን እንቅፋት ሊሆኑ እንደማይገባ አመላካች ፍኖት ነው። ከራስ ክብር ይልቅ የአገርን ክብር ለማዘመን የታቀደ ልባዊ የሕይወት ጉዞ።
ለጥበብ ፈላጊ የሚሰጠውንም ክብር ያየንበት ጉዞ ነው። ጥበብን ፈላጊ ራሷ ጥበብ ታከብረዋለች፣ትፈልገዋለች። ንግሥቷም የገጠማት ይህ ነው፤ ጠቢቡ ሶሎሞን ለንግሥቷ የሚገባትን በሙሉ አድርጎላታል። ለጥበብ ወዳድነቷ የሚገባትን የክብር ቦታና ስጦታ አበርክቶላታል። ጥበብ ፈላጊዋን ታከብራለች፤ እሷም ወደ ፈላጊዋ ታመራለች። ኹለቱም ያለማንም ከልካይነት ይገናኛሉ፤ ታሪክ ይሠራሉ።
ደስታ ሽርካ (ደስታ ጠማኙ)
ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015


