የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመንግሥት ሠራተኞች የቤት ኪራይ ድጎማን ተግባራዊ አደረገ

0
3791

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለው ወቅታዊ የኑሮ ውድነት ለመንግሥት ሠራተኞች የቤት ኪራይ ድጎማ አበል እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

የመንግሥት ሠራተኞች የሚያነሱትን የኑሮ ውድነት ለማቃለል እንዲቻል የቤት ኪራይ ድጎማ፣ ሙያዊ የሥራ ኃላፊነት አበል፣ የሞባይል ካርድና የትራንስፖርት አበል ጭማሪ እንዲደረግ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ነሐሴ 27/2014 የውሳኔ ሐሳብ ማሳለፉን አዲስ ማለዳ ውሳኔው ተግባራዊ እንዲደረግ ለክፍለ ከተሞች ከተላለፈው ማስፈጸሚያ ተመልክታለች።

የቤት ኪራይ አበል ድጎማውም በአሁኑ ሰዓት በከተማ አስተዳደሩ ካለው የቤት ችግር አንጻር የቤት ኪራይ በየጊዜው በመጨመሩም የመንግሥት ሠራተኞች በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ በመሆናቸውና ለረጅም ዓመታት ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብበት የነበረውን ችግር በተወሰነ መልኩ ለማቃለል ታሳቢ የተደረገ መሆኑም በማስፈጸሚያ ሰነዱ ላይ ተመላክቷል።

አዲስ ማለዳ የተመለከተችው የማስፈጸሚያ ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ የቤት ኪራይ ድጎማና አበል ክፍያ ቀደም ሲል የተፈቀደላቸው የሥራ መደቦች ላይ የተመደቡ ማለትም የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ዲኖችና አሠልጣኞች፣ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራን፣ ምክትል ርዕሰ መምህራን እና መምህራን፣ አቃቤ ሕግ ባለሙያዎች፣ የከተማ አስተዳደሩ ፍርድ ቤቶች ዳኞች እና የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ዳኞችን አያካትትም።

የኃላፊነት አበል ክፍያ ተፈጻሚ የሚሆነውም በሆስፒታል እና ጤና ጣቢያዎች በሥራ ኃላፊነት ከቡድን መሪ ጀምሮ በተመደቡት እና በአማካሪ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሠራተኞች ነው። ሰነዱ አክሎም የትራንስፖርት አበል ተፈጻሚ የሚሆነው በአስተዳደር ፍርድ ቤት ዳኞች፣ በሆስፒታልና ጤና ጣቢያ ከቡድን መሪ ጀምሮ በተመደቡት እና በአማካሪ ላይ ነው። የሞባይል ስልክ ክፍያ አበል ተፈጻሚ የሚሆነው በአስተዳደር ፍርድ ቤት ዳኞች፣ በሆስፒታል እና ጤና ጣቢያ ከቡድን መሪ ጀምሮ በተመደቡት እና በአማካሪ ደረጃ መሆኑን መረጃው ያትታል።

አዲስ ማለዳ የከተማ አስተዳደሩ ሠራተኛ ከሆኑ ሰዎች እንደሰማችው፣ ደሞዛቸው ከ4 ሺሕ ብር በታች ለሆነ ሠራተኞች የቤት ኪራይ 1 ሺሕ 500 ብር ጭማሬ ተደርጓል። በውኔው መሠረት እርሳቸው የሐምሌና የነሐሴ ወር ክፍያ መስከረም ወር ላይ እንደተፈጸመላቸው ጠቅሰዋል።

ደሞዛቸው ከ4 ሺሕ ብር በላይ ለሆነ ሠራተኞችም ከተደረገው የቤት ኪራይ ድጎማ በተጨማሪ፣ ለጽዳትና የጥበቃ ሠራተኞች እንደየሁኔታው የወተት አበል ተብሎ ተጨማሪ ብር ያገኛሉ።

የተፈቀደው ጥቅማ ጥቅም በከተማ አስተዳደሩ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ እውቅና የተቀጠሩ የኮንትራት ቅጥር ሠራተኞችንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል።

በዓመት ፈቃድ፣ በወሊድ ፈቃድ፣ በሀዘን ፈቃድ፣ በሕመም ፈቃድ፣ በረዥም ጊዜ ትምህርትና በአጭር ጊዜ ሥልጠና ከመደበኛ ሥራ ውጭ ለሆነ ሠራተኛ የቤት ኪራይ ድጎማ አበል ክፍያ የሚፈጸም ሲሆን፣ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ከ30 ቀናት በላይ ከመደበኛ ሥራ ውጪ ለሆነ ሠራተኛ የኃላፊነት አበል፣ የስልክ ክፍያ አበል እንዲሁም የትራንስፖርት አበል ክፍያ መፈጸም የተከለከለ ነው ተብሏል።

የተፈቀደው የቤት ኪራይ ድጎማ አበል እና የጥቅማ ጥቅም አበል ክፍያ ከሥራ ግብር ነጻ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here