የድኅረ ኮቪድ እንቅስቃሴ

0
780

የኮሮና ወረርሽኝ እየተባለ የሚገለጸው የኮቪድ 19 ቫይረስ ዓለማችንን ማዳረስ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል። በታኅሳስ ወር 2012 ላይ ቻይና ዉሓን ከተማ ተከስቶ ዓለምን ለማዳረስ ወራት ብቻ የፈጁበት ይህ ወረርሺኝ፤ እኛም አገር መጋቢት 4/2012 ከገባ ጀምሮ እስካሁን በርካታ ለውጦችን አምጥቷል።

በአንድ ጃፓናዊ ላይ ቫይረሱ ተገኘ ሲባል የነበረው የሕዝብ መረበሽ ቀስ በቀስ እየቀነሰ አሁን ያለንበት የመዘናጋትም ይባል የቸልታ ደረጃ ላይ ሊያደርሰን ቢችልም፣ በዚህ አጭር ሊባል በሚችል ጊዜ ለዘመናት ሲለፋባቸው የነበሩ ዘርፎች ላይ በቀላሉ ተፅእኖ ማሳደሩ ይታወቃል። በአገራችን ወረርሽኙ በተከሰተባቸው የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት፣ ቢሮ መግባት አቁመው ቤት ለመሥራት እንዲሁም በርካታ አገልግሎት ሰጪዎች ሥራቸውን ለማቆም ተገድደው ነበር።

የወረርሺኙ አድማስና ጉዳት እየሰፋ ሲመጣ አስቀድሞ የነበረው ፍርሀትና ጥንቃቄ ባይቀጥልም፣ መዘዙ ግን የከፋ እንደነበር የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑት አሁን ድረስ አይዘነጉትም። በስጋቱ ሳቢያ ከሥራ ገበታቸው የተፈናቀሉ፣ የገቢ ምንጫቸው የቀነሰባቸውና ጭራሹኑ ዘርፋቸውን ለመለወጥም የተገደዱ በርካቶች ነበሩ።

ከሁሉም በላይ በበሽታው ሳቢያ ቤተሰባቸውንና ወዳጆቻቸውን ያጡ መቼም ቢሆን የማይረሱትን ለውጥ እንዳመጣባቸው ግልፅ ነው። ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በዘመድ የተገለሉት ያስተናገዱትን ሁኔታ የሚረዱትን ያህል፣ ጠያቂ እንዳይኖራቸው ተከልክለው እስኪያገግሙ በለይቶ ማቆያ ተለይተው የከረሙም ወረርሺኙ አኗኗራቸው ላይ ያመጣውን ለውጥ በቀላሉ ማስተዋል ይችላሉ።

ይህን መሰል የአኗኗር ዘይቤ ለውጥም ይሁን የአስተሳሰብ መቀየርን ያስከተለው ኮቪድ፤ በኹሉም አገራት ማለት በሚቻል መልኩ ተመሳሳይ ሂደትን አልፎ ነበር። አገራቸውን ዝግ ካደረጉት ጀምሮ ኢኮኖሚያቸው እንዳይላሽቅ ሰግተው ፈራ ተባ እያሉ የተለመደ አሰራራቸውን ለማሻሻል የሞከሩም ነበሩ።

የአሜሪካው መሪ ጆ ባይደን ሠሞኑን ወረርሺኙ አብቅቶለታል ማለታቸውን ተከትሎ ብዙዎች አሁንም አስጊ ሆኖ አለ ሲሉ ንግግራቸውን ተቃውመውታል። በበርካታ አገራትም ወረርሺኙ ድጋሚ አገረሸ ተብሎ ክልከላዎች በድጋሚ እየተወሰኑ መሆኑም ይሰማል።

አሁን ላይ ሆኖ አጠቃላይ ወረርሺኙ አልፏል ብሎ ለግምገማ መቀመጥ ባይቻልም፣ በአንጻራዊነት ስጋቱ እንደመቀነሱ የነበረውን ሂደት አስተውሎ ለመማሪያ ይሆን ዘንድ የሂደቱን አንኳር ጉዳዮች እየለዩ ማየት ይቻላል።

የመጀመሪያው የወረርሺኙ ሂደት የነበረው በሽታው በበርካታ ሰዎች ላይ ሲገኝ ይፋ ላለማድረግ ፖለቲከኞች ይወስዱት የነበረው እርምጃ ነው። የፖለቲካ መበሻሸቂያ ያደረጉት ቻይናና አሜሪካ አንዳቸው አንዳቸውን ለመወረፊያ ስለተጠቀሙበት ኅብረተሰቡ አውቆ አስቀድሞ እንዳይጠነቀቅ ማድረጉ ይታወቃል። የቻይና መንግሥት ባለሥልጣናት ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖው እንዳይበረታባቸው ሲሉ ወረርሺኝ አይደለም ብለው መጀመሪያ መረጃውን ለማፈን በኋላም አቃሎ ለማሳየት ሲጥሩ ቆይተዋል።

የበሽታው መስፋፋት እርግጥ ሲሆንና አስጊነቱ ዓለም ዐቀፍ መሆኑን ሲረዱ፣ መረጃውን የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት በማድረግ ክልከላ ጀምረው ነበር። አውሮፓውያንና አሜሪካ እንዲሁም የብራዚል መንግሥት የተቀናበረ ውሸት ነው ብለው ዜናውን በማጣጣል በኋላ ላይ ዓለም እስኪያዝንላቸው ለማለቅ በቅተው ነበር። አውሮፓውያንም ዘግይተው እስኪያቆሙ ድረስ በሽታውን ሲያሰራጩ ቆይተው፣ በኋላ ላይ ገንዘብ ጥቅም የለውም ብለው በትነው በየቤታቸው ተከተው እስኪጠብቁ ድረስ ለከፍተኛ ጉዳት ዳርጓቸው ነበር።

ወረርሺኝ እንደሆነ ሲታወቅ የምሥራቁ ጎራ አገሮች በተለይ ሰሜን ኮሪያና በሽታው የተነሳባት ቻይና ቆፍጠን ያለ ትዕዛዝ አውርደው በወታደራዊ እዝ ተጠቅመው ዜጎቻቸውን ማዳን ሲችሉ፣ የምዕራቡ ዓለም አገራት በበኩላቸው የግለሰብ ነጻነትን መንፈግ ነው በሚል ላያዛልቃቸውና ላይገፉበት ተዘናግተው በመቆየታቸው ብዙ ዜጎቻቸውን አጥተዋል።

ልክ እንደጦርነት ኅብረተሰብን በጅምላ የሚጨርስ ወረርሺኝ ሲመጣ የአደጋ ጊዜ አዋጅ አውጀው ኹሉም አገራት በሚባል መልኩ የውጭ ዜጋ እንዳይገባባቸው በራቸውን ዘግተው ነበር። ቻይና ገበያዬን ይዘጋል ያለችውን ይህን እርምጃ ፈጥና በማከናወኗ ጉዳቷ አነስተኛ የነበረ ሲሆን፣ ሌሎች ዘግይተው በመወሰናቸው የከፋ ጉዳት አስተናግደዋል።

አፍሪካን በተመለከተ በተደጋጋሚ ጉዳቱ ከፍተኛ ይሆናል ተብሎ ቢተነበይም የታሰበው ሳይሆን በመቅረቱ ለጥናትና ምርምር የተዳረጉም ነበሩ። ሆን ተብሎ የተለቀቀ ቫይረስ ነው የሚሉትን ጎራ እያደር የሚቀላቀሉ አገራት በመብዛታቸውም፣ የመከላከያ ክትባት ለማምረትም ሆነ መድኃኒቱን ለመፈብረክ የነበረው ጥድፊያ ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳሳደረ የሚናገሩ ነበሩ።

ወረርሺኙ በተለያዩ አገራት እየተስፋፋ ዓለም ዐቀፍ ይዘት ሲኖረው በመጀመሪያ የተቋረጠው ዓለም ዐቀፍ በረራ ስለነበር በዘርፉ የተሰማሩ ብዙ ተቋማት ኪሳራ ውስጥ ወድቀው ነበር። ኢትዮጵያን የመሳሰሉ አገራት የሰው ማመላለሻዎችን ወደ እቃ መጫኛ አውሮፕላን በመቀየር የወቅቱን የገበያ እጥረት ለመቋቋምና ውጤታማ ሆኖ ለማለፍ በመሞከር ሌላው ሠራተኛ ሲቀንስ ባለበት ለመቀጠል ችለዋል።

በወረርሺኙ ምክንያት የመንገደኛ ማጓጓዣዎች ወደ እቃ መጫኛ ተቀይረው ስለነበር ወረርሺኙ ከቀነሰና ክልከላው ካበቃ በኋላ እንቅስቃሴ ወደነበረበት ሲመለስ ለማስተናገድ ቸግሮ ነበር። ከነበረው ተጓጓዥ በላይ ብዙ መንገደኛ የመጣባቸው የኢትዮጵያን የመሳሰሉ አገልግሎት ሰጪዎች በደንበኛ መብዛት ሳቢያ ትኬት የቆረጠ በእለቱ ሞልቷል ተብሎ ለመመለስ እስከመገደድ ደርሶ ነበር።

በርካታ አየር መጓጓዣ ኩባንያዎች ሠራተኛ ቀንሰው ስለነበር ኅብረተሰቡ ወደነበረበት ሂደት ሲመለስ መቋቋምና መልሰው ወደነበሩበት ቦታ በአንዴ ማደግ ስለተሳናቸው መስተጓጎል በየአገሩ ተፈጥሮ እንደነበር ይነገራል። ትክክለኛ ጥናት ተካሂዶ ያመጣው ለውጥ ይህ ነው ተብሎ ባይነገርም፣ በመጓጓዣውና በአገልግሎት ሰጪው ዘርፍ ላይ ያስከተለው ተፅእኖ ስር የሰደደና በቶሎ መቀልበስ ያልተቻለ እንደነበር አንዳንዶች ሲናገሩ ይደመጣል።

ወረርሺኙ ከፍተኛ ተፅእኖ ካሳደረበት የትራንስፖርት ዘርፉ ቀጥሎ የቱሪዝሙ ሴክተር እጅግ ተጎድቶ ወደነበረበት መመለስ እንደከበደው የተለያዩ አገራት ተሞክሮዎችን ከግምት በማስገባት የሚናገሩ አሉ። ኬንያና ግብፅን የመሳሰሉ ኢኮኖሚያቸው በቱሪዝም ላይ የተመሠረተ አገራት፣ ከነበረው አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣት የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ቢጥሩም ያን ያህል ውጤታማ አላደረጋቸውም ነበር።

ከቱሪዝም ጋር በተገናኘ የሚሠሩ ሆቴሎች፣ አስጎብኚዎችና ሌሎች ተቋማትም እጅግ ከመጎዳታቸው የተነሳ ወደነበሩበት ለመመለስ እንደማይችሉም የሚናገሩ አሉ። ብዙዎች መስካቸውን ለመቀየር እንደተገደዱና በባንክ እዳም የማይመለሱበት አዘቅት ውስጥ ገብተው ድጎማ የሚጠብቁም በርካቶች መሆናቸው ይሰማል።

በአገራችን ኢትዮጵያም የዘርፉ መዳከም በመንግሥት ሪፖርት ጭምር የተደገፈ ሲሆን፣ ላለፉት ኹለት ዓመታት የቀነሰው የጎብኚ ቁጥር ከጸጥታው ኹኔታ ጋር ተደማምሮ ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ እንዳደረገውና የብዙዎች እንጀራ አደጋ ውስጥ መውደቁ ሲነገር ተደምጧል።

የኮሮና ወረርሺኝ በርካታ ችግሮችን በየአገሩ ቢያስከትልም የድሃ አገሮችን ያህል የገዘፈ እንዳልሆነ ይነገራል። የበሽታው ቀጥተኛ ተጠቂዎች በአብዛኛው ያደጉ አገሮች ዜጎች ስለመሆናቸው ቢነገርም፣ በኢኮኖሚው መስክ ግን በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ይበልጥ መቀመቅ ውስጥ መክተቱን መመልከት ይቻላል።

በሽታው በተለያዩ አገራት መገኘት ጀመረ ሲባል ገና፣ ምርመራውን ማድረጊያ መሣሪያ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ድሃ አገራት ስላልነበረ ውጪ እያስላኩ ለማስመርመር ተገደው ነበር። በኋላ ላይ እጅግ በተጋነነ ውድ ዋጋ ገብቶ ቀስ በቀስ ቁጥሩ እየጨመረ ቢመጣም፣ በዋና ከተማና በየክፍለ አገር ከተሞች የነበረው ስርጭት ብዙ ያባባለ ነበር።

ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ለእንዲህ ዓይነት ክስተት በቂ የሆነ መሠረተ ልማትም ሆነ የሰው ኃይል አለመኖሩን ወረርሺኙ ያመላከተ ነበር። ጥድፊያው ብቻ ሳይሆን ማስክን፣ ሳኒታይዘርን፣ ጓንትንና ሶፍትን የመሳሰሉ መከላከያ ቁሳቁሶችን ለማግኘት የነበረ ግድያ እንዲሁም የነጋዴዎች ስግብግብነትን ያሳየ ክፉ ጊዜም ነበር።

ለበርካቶች የሥራ እድል ቢፈጥርም ማስክን የመሳሰሉ መከላከያዎችን ለማምረት የነበረ ጥድፊያ አስገራሚ ነበር። ብዙ ተቋማት ፊታቸውን በማዞር ከወረርሺኙ ተጠቃሚ ለመሆን የቻሉ ሲሆን፣ የመድኃኒት አምራቾችን ያህል የተጠቀመበት አልነበረም።

ፌጦና ነጭ ሽንኩርት፤ ሎሚና ዝንጅብል ይከላከላል እየተባለ ዋጋቸው እስኪጋነን ድረስ በአሉባልታ በበርካታ አገራት ውድ እቃዎች ሆነው ቆይተውም ነበር። ጨጓራቸው እስኪላጥ ዝንጅብል የደጋገሙ፤ ቆዳቸው እስኪመለጥም አስሬ እጃቸውን በሳኒታይዘር ሲሞልጩም የነበሩ ታይተዋል። ሞትን መፍራት የተለመደ ቢሆንም፣ ንፅሕና እጅግ ተፈላጊ የሆነበትና በተላላፊ በሽታ የሚያዘው ሰው ቁጥር ከወትሮ አሐዙ የቀነሰበት ጊዜ እንደነበር በባለሙያዎችም ተጠቅሷል።

ለዘመናት የነበረ የሰላምታ መንገድ በአጭር ጊዜ እንዲቀየር የተደረገበትና አሁንም ድረስ ባህል ሆኖ የሚቀጥል የሚመስል የሰላምታ መንገድንም ወረርሺኙ ወደ ዓለማችን ይዞ መጥቷል። መሳሳም ቀርቶ መጨባበጥ እስኪፈራ ድረስ ማኅበራዊ ሕይወታችንንም ያናጋ ነበር። ሰው ቤት ዘው ብሎ መሄድና መጠያየቅን ከነአካቴው ያስቀረ እንደነበርም የሚናገሩ አሉ።

ወረርሺኙ አሁንም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ኅብረተሰቡን እያጠቃ ቢሆንም፣ ልክ የሌለ ያህል የሚወሰደው ጥንቃቄ ቆሟል ማለት ይቻላል። አሐዛዊ መረጃን ተመርኩዘው አሁንም ብዙዎች እየሞቱ መሆኑን ባለሙያዎች ቢናገሩም፣ ካለፈው ሂደት ተምሮ የተሻለ ጥንቃቄ ለመውሰድ ይቅርና የነበረውንም ለማስቀጠል አዳጋች መሆኑን ለመመልከት ይቻላል።

ከወረርሺኙ ወቅት የተገኙ ጠቃሚ ተሞክሮዎችን ለማስቀጠል፣ የማይጠቅሙትንም ለማሻሻል ከወዲሁ መደበኛ ጥናት አካሂዶ ለሕዝብ ማሳወቅ እንደሚገባ ብዙዎች ይስማማሉ።

ቴክኖሎጂን መጠቀምን በተመለከተ በቻይና የተሠራውን የቫይረስ መኖርን የሚጠቁም ማስክን ማስተዋወቅም ጠቃሚ ነው። ግሪክ ሪፖርተር ላይ ይፋ የተደረገው ይህ ግኝት ዘመናዊ ዲጂታል ማስክን ለአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን፣ በአካባቢው ጉንፋን አምጪና የኮቪድ ቫይረሶች መኖራቸውን በ10 ደቂቃ ውስጥ ለግለሰቡ የሚጠቁምና ከቦታው እንዲርቅ የሚያደርግ ነው።

ማስኩ ለሌሎች አየር ላይ ተንሳፈው ከሰው ወደ ሰው ለሚተላለፉ በሽታ አምጪ ሕዋሶች መመርመሪያና ማሳወቂያ ተደርጎ ሊዘጋጅ እንደሚችልም ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል። በዝግ አካባቢዎች የበለጠ ውጤታማ ይሆናል የተባለው ይህ ማስክ መች ወደገበያ እንደሚቀላቀልም ሆነ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚያገለግል ባይጠቀስም፣ ከጥቅሙ አኳያ በዘላቂነት የሚቆይ ቴክኖሎጂ እንደሚሆን ተገምቷል።

አንዳንዶች ወረርሺኙ ቆሟል በሚል ሲዘናጉ ሌሎች ደግሞ አሁንም እየተሰራጨ መሆኑን ተረድተው ጊዜያቸውንና አቅማቸውን ለበሽታው መጥፋት እያዋሉት ይገኛሉ። በዘርፉ የሚደረጉ ምርምሮችም ሆኑ ግኝቶች ለኮሮና ቫይረስ ብቻ ሳይሆን ለወደፊት ሊመጡ ለሚችሉ ተመሳሳይ ወረርሺኞች እንደግብዓት ሊያገለግሉ የሚችሉ በመሆናቸውም ጥቅማቸው የጎላ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here