‹‹በጃንሆይ ዘመን…›› ይላሉ አንድ አዛውንት፣ እርሳቸው አዘውትረው ከጎጃም አዲስ አበባ በእግር ጉዞ ይመላለሱበት የነበረውን የአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሲያስታውሱ። ‹‹በዚያ ጊዜ በጎጃም አድርጎ አዲስ አበባ ያውም በእግር ለመሄድ ፈታኝ የነበረው አባይን መሻገር ብቻ ነበር። ትልቁ ወንዝ ድልድይ ስላልነበረው የምንሻገረው በዋናተኛ ነበር። ለዚህም በአንድ ሰው አንድ ጠገራ ብር የምንከፍል ሲሆን፣ ወዲያ ማዶና ወዲህ ማዶ አንጋች (ጠመንጃ የታጠቀ) በተጠንቀቅ ቆሞ ይጠብቃል።
ለምን ሲባል ሽፍታ እንዳይገድለን ተብሎ ሳይሆን ውሃው ውስጥ እንዳለን አዞ ብቅ ያለ እንደሆን ለመምታት ነው። ወንዙን በሰላም የተሻገርን እንደሆነም የፈለግነው ቤት የእግዜር እንግዳ ጠይቀን እያረፍን አዲስ አበባ እንገባ ነበር።›› በማለት ያስታውሳሉ።
ቀጠሉና፤ ‹‹ጉዳያችንን ጨርሰን ስንመለስም ያለምንም ስጋት ነበር በስድስተኛው ቀን ቤታችን የምንደርሰው። ከዚያ በኋላ ደግሞ ጃንሆይ ድልድዩን አሠርተው መኪናም ሲገባ እጅግ ወደ አዲስ አበባ መጓዝ ቀላል ሆነ። በእግር መመላለስም ተረት ሆኖ ቀረ። ሰሞኑን የምንሰማው ግን እጅግ አስነዋሪና በዚህ ዘመን ይሆናል ተብሎ የማይታመን ነው።›› በማለት አከሉ።
‹‹አዲስ አበባ ጉዳይ የሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የለም። አዲስ አበባ መግባት ፈተና ሆኗል፣ ሰዎችም ታፍነው እየጠፉ ነው ሲባል ስሰማ፣ ሰው እያደረ እየሠለጠነ ይሄዳል እንጂ ከ50 ዓመት በፊት ከነበረው የባሰ ይሆናል ወይ እላለሁ›› ሲሉም የወቅቱን፣ ስጋት ውስጥ የወደቀውን የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት ይገልጻሉ።
‹ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ› በሚለው የአፄ ኃይለሥላሴ መጽሐፍ፣ በአንድ ወቅት በአገሪቱ ዜጎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ገብተው እንደነበር በመጥቀስ፣ ይህን ለማስቆም አንድ መላ መዘየዳቸውን ያወሳሉ።
ይህም አንድ ሰው ከአንድ ቦታ ተነስቶ ወደ ሌላ ቦታ በሚንቀሳቀስበት ወቅት አደጋ የደረሰበት እንደሆን፣ አደጋ የደረሰበትን ቦታ የሚያስተዳድረውን የመንግሥት አካል ተጠያቂ የሚያደርግ ጽኑ ሕግ ነው። ይህንን ሕግ በማውጣትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩ ተፈቶ ዜጎች እንደፈለጉ መንቀሳቀስ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ወቅትም ዜጎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በአብዛኛው በስጋት የተሞላ ሲሆን፣ በብዙ ቦታዎችም ሰላማዊ ሰዎች በታጣቂዎች ሲገደሉ እንዲሁም በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሳይቀር እንግልት ሲደርስባቸው ማየት የተለመደ ነው።
ይህም ማእከላዊ መንግሥቱ ለዜጎች ሰላምና ደኅንነት የሰጠው ቦታ እምብዛም ከመሆኑ የተነሳ፣ አካባቢያቸውን እንዲያስተዳድሩ ሕጋዊ ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት ድክመት መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።
ብዙ ጊዜ በርካታ ዜጎች እየተገደሉ እና እየተፈናቀሉ ያሉት ከመሐል አገር ራቅ ካሉ ቦታዎች የሆነ ቢመስልም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለይ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ዜጎችም ‹ዛሬስ ምን ይገጥመን ይሆን?› ብሎ ከመጨነቅ ባለፈ ድብደባና እንግልት ተፈጸመብን በማለት መናገር ከጀመሩ ውለው አድረዋል።
በመስከረም ወር ኹለተኛ ሳምንት፣ በተለይ አባይን ተሻግረው ወደ መዲናዋ የሚገቡ መንገደኞች ላይ የተለያዩ ችግሮች መፈጠራቸው ሲገለጽ ነበር። ረቡዕ 11/2015 ከደብረ ማርቆስ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ ከነበሩ መንገደኞች መካከል አንዲት እናት፤ ‹‹አዲስ አበባ ልንደርስ ትንሽ ቀርቶን ሳለ ጫንጮ መግቢያ ላይ መኪናውን ካስቆሙ በኋላ ሴቶችን፣ ሀዘንተኛ የሆኑትንና ሽማግሌዎቹን አሳልፈው ወጣቶችን መልሰዋቸዋል።›› በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ በብዛት አብረቅራቂ የለበሱ ሰዎች ከጥቂት ፖሊሶች ጋር በመሆን ነው ብለዋል።
ቀደም ብሎ በደብረ ብርሃን በኩል ወደ አዲስ አበባ በሚገቡ ሰዎች ላይ ይደርስ የነበረው እንግልት የተሻሻለ ቢመስልም፤ ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ድርጊት ተፈጥሮ በማያውቅበት የጎጃም መስመርም የዜጎች እንቅስቃሴ ስጋት ውስጥ ገብቷል።
አዲስ ማለዳም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በዚህ መስመር ያለውን እንቅስቃሴ እንደታዘበችው፣ መንገዱ ሰላም አይደለም በማለት ጉዟቸውን ሲሰርዙ የነበሩ በርካቶች ናቸው። ጉዞ ከመጀመራቸው በፊትም መንገድ ላይ ታግተው የጠፉ እንዲሁም የተደበደቡ በመኖራቸው በዚህ ወቅት ወደ አዲስ አበባ መጓዙ ተገቢ አይደለም የሚል ስጋታቸውን የሚገልጹም ብዙዎች ናቸው።
ሌላኛው ተጓዥም በዚህ ሰዓት ‹መንግሥት ይደርስልኛል፣ ሕግ ያድነኛል የማንልበት ሁኔታ ውስጥ ገብተናል። የጸጥታ ኃይሉ በራሱ በመንግሥት ከተሰጠው ተልዕኮ ሌላ ምን ዓላማ እንዳለው ማወቅ አንችልም። ምን ያደርጉን ይሆን ብለን የምንሰጋው እኮ ማንንም ሳይሆን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላትን ነው።›› ሲሉ ተናግረዋል።
ተጓዦች ጫንጮ ላይ ለፍተሻ ረዥም ጊዜ የሚያጠፉ ሲሆን፣ መታወቂያ የሌላቸውና ኖሯቸውም ያላሳደሱ ናቸው የተባሉ ብዙ ወጣቶችም ከመኪና ወርደው በጸጥታ ኃይሎች እጅ ውስጥ ሆነው አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።
‹‹እነዚህ ወጣቶችም ወደመጡበት እንዲመለሱ ይደረጋሉ? እንዲመለሱ የሚደረግ ከሆነስ አዲስ አበባ ሊገቡ ጥቂት ሲቀራቸው ከመመለስ ይልቅ ለምን ጉዞ ሲጀምሩ ወይም አባይን ሲሻገሩ ተፈትሸው እንዲመለሱ አልተደረገም?›› የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ሆኖም ‹ወዳልታወቀ ቦታ ይወሰዳሉ› የሚሉ መላምቶችን ከመስማት በቀር በአንድ ቦታ ተሰብስበው ሲጠበቁ ስለነበሩ ወጣቶች ስለሚሰጠው ውሳኔ የታወቀ ነገር የለም።
ይህ መስመር ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል ከሚያስገቡት ብቸኛ ኹለት የየብስ መስመሮች ዋናው በመሆኑ፣ በቀንም በማታም የማያቋርጥ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ነው። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በማታ ለሚጓዙ አካላት የማይታሰብ ሆኗል።
ይህም በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል የማይባል መሆኑ መገመት አያዳግትም። ብዙዎች እንደሚሉትም በቀን የሚደረገው እንቅስቃሴም አንድ ጊዜ ሰላም ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ የፈለገ አካል ተነስቶ አታልፉም የሚልበት ደረጃ ደርሷል።
አልፎ አልፎም የአዲስ አበባ መታወቂያ ሳይኖራቸው አባይን ተሻግረው የመጡ መንገደኞችን አናሳልፍም የሚሉ የጸጥታ አካላትም ከተሳፋሪዎች ብር ተዋጥቶ እንደሚሰጣቸውና እንደሚያሳልፉም ተሰምቷል።
በመሆኑም በወለጋ፣ በደቡብ (በአማሮ፣ ቡርጂ፣ ጉጅ…) እና ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በሰሜን ራቅ ብሎ ይሰማ የነበረው የዜጎች ሞትና እንግልት ቀስ በቀስ አድማሱን እያሰፋ በኹሉም አካባቢዎች እየተዳረሰ በመሆኑ መንግሥት ለዜጎች ሰላምና ደኅንነት ከምንም በፊት ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት የማይወተውት አካል ያለ አይመስልም።
ችግሩ በአንድና በኹለት የጉዞ መስመሮች የተገደበ ሳይሆን ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ አዲስ አበባ በሚመጡ መንገደኞች ላይም ተመሳሳይ ችግሮች እንደሚከሰቱ ሲነገር ይሰማል።
በዚህም በየቦታው ሕገወጥ የፍተሻ ኬላዎችን በማቋቋም ሕዝብን የሚያሰቃዩ አካላት ከመብዛታቸው ሌላ፣ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከልም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመጠቀም በብልሹ አሠራር የተጠመዱና የሕዝብን እንቅስቃሴ የሚያውኩ ስለመኖራቸው ይነገራል።
ተያያዥ የመብት ጥሰቶች
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ መስከረም 12/2015 አስቸኳይና በቂ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በሚል ባወጣው መግለጫ፤ በዚህ ወቅት በብዙ ቦታዎች በርካታ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ እንደሆነ አመላክቷል።
የጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እና ሌሎችን መታሰር ጨምሮ፣ ፖሊስ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ በመሻር የዜጎችን የዋስትና መብት እንደሚከለክል ብሎም በደቡብ፣ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች በበርካታ ዜጎች ላይ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየደረሱ መሆኑን በመግለጫው ሳይጠቅስ አላለፈም።
በመሆኑም ተቋሙ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው የማያባራ ስቃይ ከዓለም ዐቀፍ እና ከአገር ውስጥ ሕጎች ጋር በእጅጉ እንደሚቃረን አስገንዝቧል። በተያያዘም የሰብዓዊ መብቶች ዓለም ዐቀፍ መግለጫ (UDHR) እና የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም ዐቀፍ ቃልኪዳን (ICCPR) ኹለቱም ስምምነቶች በአንቀጽ ዘጠኝ ላይ ማንም ሰው በዘፈቀደ ሊያዝ እንደማይችል፣ ማንም ሰው ከሕግ ውጪ እንደማይያዝ፣ እንደማይታሰር እና የግል ነጻነቱን እንደማያጣ ይደነግጋሉ ሲል አስቀምጧል።
በተመሳሳይ የአፍሪካ ቻርተር በሰዎች እና ሕዝቦች መብቶች ስምምነት አንቀጽ ስድስት ላይ በተመሳሳይ ማንም ሰው የነጻነትና የአካል ደኅንነት መብት እንዳለው፤ ይህንንም መብት ከሕግ አግባብ ውጪ እንደማያጣ እና ማንም ሰው በዘፈቀደ ሊታሰር እንደማይገባ ይገልጻል። በተጨማሪም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥትም እንዲሁ በአንቀጽ 17 ላይ የነጻነት መብትን ሲያብራራ ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም ሲል እንደሚደነግግም ነው ያመላከተው።
ስለሆነም መንግሥት የዜጎች ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንዲያከብር፣ የታሰሩ ሰዎች በአፋጣኝ ፍትህ እንዲያገኙ እንዲያደርግ እና በፖሊስ የፍርድ ቤትን ውሳኔ አለማክበር ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ፣ በጦርነትና ግጭቶች ሳቢያ የተፈናቀሉና በረሃብ እየሞቱ ላሉ ዜጎች አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ብሎም በየጊዜው በታጣቂዎች እየተገደሉ ያሉ ዜጎችን ሕይወት መታደግ እንዲችልና ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን ተጠያቁ በማድረግ በዘላቂነት ማኅበረሰቡ ደኅንነት ተሰምቶት መንቀሳቀስ ይችል ዘንድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ መስከረም 16/2015 ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ኡሙሩ ወረዳ በርካታ ንጹሐን በታጣቂዎች መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።
ከነሐሴ 25/2014 ጀምሮ ባሉ ተከታታይ ሦስት ሳምንታት በተፈጸሙ ጥቃቶችም ከ100 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል ያለ ሲሆን፣ በርካቶችም የቤት እንስሶቻቸውን ጨምሮ ሀብት ንብረታቸውን ተዘርፈው እንደተፈናቀሉ ነው ኮሚሽኑ የገለጸው።
ስለሆነም ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ሲያሳስብ እንደቆየው አሁንም የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥታት በአካባቢው ብሔርን መሠረት አድርገው የሚፈጸመው ጥቃቶችን ለመከላከል እየወሰዱት ያለውን እርምጃ፤ ችግሩን በሚመጥን ደረጃ በማሳደግ የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ሲል በድጋሜ አሳስቧል።
የአንድ አገር መንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስጠበቅ መሆኑ ይታመናል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥትም በአገሪቱ በርካታ በጎ ለውጦችን አስመዝግቤያለሁ፣ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅም ሌት ተቀን እተጋለሁ የሚል ቢሆንም፣ በብዙ ቦታዎች መንግሥት ይድረስልን በማለት ጩኸታቸውን የሚያሰሙ ዜጎችን ከመጨፍጨፍና ከመፈናቀል የሚታደጋቸው አካል አልተገኘም።
ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015


