የብድር አገልግሎት ለአንድ ዓመት እንደተቋረጠባቸው የልማት ባንክ ሠራተኞች ተናገሩ

0
770

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንደማንኛውም ባንክ ለሠራተኞች ሲሰጠው የነበረውን የብድር አገልግሎት አንድ ዓመት ለሚሆን ጊዜ እንዳቋረጠባቸው የባንኩ ሠራተኞች ገለጹ።

ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ሠራተኞች፣ ከዓመት በላይ የቤትና የመኪና ብድር አላገኘንም ብለዋል። አንድ ሥሜ ባይጠቀስ ያሉ ቅሬታ አቅራቢ በበኩላቸው ‹‹ባንኩ የሪፎርም ሥራውን ለማጠናቀቅ ከአምስት ጊዜ በላይ ቃል የገባ ቢሆንም ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ የሠራተኛውን ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም ማሻሻያዎች በዚሁ ሰበብ ታፍነዋል›› ሲሉ ጠቅሰዋል።

የባንኩ ሠራተኞች በተያያዘ ያደረባቸው ቅሬታ ባንኩ የደረጃ እድገትና የብር ቦነስ እንደሚሰጥ የገባውን ቃል አለመፈጸሙ ጋር በተገናኘ መሆኑ ተነስቷል።

ባንኩ በ2014 በጀት ዓመት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፋን ተከትሎ ሐምሌ ወር ላይ ለሠራተኛው በአጭር ጊዜ የቦነስ ጭማሪ እንደሚያደርግ በማስታወቂያ ሲገልጽ ቆይቷል። ይሁን እንጂ እስካሁን (ይህ ዘገባ እስከተዘጋበት ጊዜ) ድረስ የቦነስ እና የእርክን ጭማሪው በተገባው ቃል መሠረትና በወቅቱ ተፈጻሚ አለመሆኑ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ነው ሠራተኞቹ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

በመሆኑም ልማት ባንክን እስከ አሁን ድረስ ከግልም ሆነ ከመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ቦነስ ያልሰጠ ባንክ እንደሚያደርገው ቅሬታ አቅራቢዎቹ አያይዘው ገልጸዋል። ልማት ባንክ ለሠራተኞች የሚያደርገውን የቦነስና የእርከን ጭማሪ ከኹለት ወር በላይ ማዘግየቱም ተመላክቷል።

ይህን ተከትሎም ሠራተኞች ቀደም ሲል ከኹለት ወር በፊት የተገባው ቃል ተግባራዊ እንዲሆን በመጠየቃቸው፤ ለአዲስ ዓመት በዓልና ለትምህርት ቤት ወጪ በማለት የአንድ ወር ደመወዝ በአምስት ወር እንዲከፈል ተፈቅዶ ነው ሠራተኞች በዓልን ያሳለፉት ተብሏል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በተያያዘም ባንኩ የደመወዝ ጭማሬውና የእርከን ማሻሻያው በ15 ቀናት ውስጥ ምላሽ ያገኛል ሲል ቃል መግባቱን አስታውሰው፤ ከተጠቀሰው ጊዜ እንዳያሳልፍባቸው ጠይቀዋል።

ሆኖም ግን የቦነስ ጭማሪውን መስጠት ሲገባ ከደመወዝ ላይ ብር መቁረጥ በመጀመሩ ሠራተኛው በተወደደ ኑሮ ተደራራቢ ችግር ላይ እንደሚወድቅ ባንኩ ሊገዘነብ ይገባል የሚል አስተያየትም አንስተዋል።

አክለውም የሠራተኛ ማኅበሩና ሌሎች የባንኩ ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ምላሽ እንዲሰጧቸው በአዲስ ማለዳ በኩል ጠይቀዋል።

ባንኩ ለአንድ ዓመት የብድር አገልግሎት ማቆሙን በተቋሙ ውስጥ የሚገኙ የሠራተኞች ማኅበር ተጠሪ ይበልጣል ያየ አስታውቀዋል። ልማት ባንክ እንደማንኛውም ባንክ ለሠራተኞቹ የቤትና የመኪና መግዣ የሚሆን ብድር ይሰጣል ያሉት ይበልጣል፤ አገልግሎቱ በመቋረጡ ሠራተኞች ቅሬታ እንዳላቸው አልደበቁም።

አንድን ነገር ለመግዛት ከዓመት በፊት በነበረው ዋጋ ዘንድሮው ማግኘት እንደማይቻል ጠቅሰው፤ የአገልግሎቱ መቋረጥ ዘርፈ ብዙ ችግር እንዳስከተለ አንስተዋል።

ባንኩ አገልግሎቱን ያቋረጠው ለመከልከል ሳይሆን የጀመረው ሪፎርም በመኖሩና ገና ባለመጠናቀቁ ነውም ብለዋል። በልማት ባንክ ከኹለት ሺሕ በላይ ሠራተኛ መኖሩን ጠቅሰው፣ ጥያቄውና ቅሬታቸው የኹሉም ሠራተኞች እንጂ በማኅበር የተደራጁት አባላት ብቻ አይደለም ነው ያሉት።

አክለውም፤ በሠራተኞች ማኅበሩ በኩልም ቢሆን ቅሬታቸውን ለባንኩ እንዳሳወቁና ለጥያቄያቸው ምላሽ እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሠራተኞች ያነሱትን ቅሬታ በተመለከተ ምን ምላሽ እንዳላቸው አዲስ ማለዳ የባንኩን ባለሥልጣናት ለማነጋገር ጥረት ብታደርግም፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here