በኢትዮጵያ ብሔራዊ የፊደል ቀን ሊከበር እንደሆነ የመርሃ ግብሩ አዘጋጆች ለአዲስ ማለዳ በላኩት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
‹‹ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሕዝቦች እንዲኖራቸው የሚመኙት ጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት ናት›› ያሉት አዘጋጆቹ፤ ልዩ የሆኑት የኢትዮጵያ ፊደላት ለአገራችን የጥንት ሥልጣኔ የማያጠራጥር ኪዳን መሆናቸውን ያሳያሉ ብለዋል።
‹‹የቅርሶቻችንን እና ታሪካችንን ጠቀሜታ በውል የተገነዘቡት የሠለጠነው ዓለም አገሮች፣ የእኛን ጥንታዊ ቋንቋዎችም ሆኑ ፊደላትን በታላላቅ የምርምር ተቋሞቻቸው ውስጥ እንዲጠኑ ሁኔታዎችን አመቻችተዋል›› ያሉት አዘጋጆቹ፣ ይህንንም ገቢራዊ ለማድረግ ያነሳሳቸው በጥንታዊ ድርሳናት ውስጥ ትኩረት ተነፍጓቸው የኖሩት ጥበቦች እና እውቀቶች በተግባር ቢመነዘሩ የሚያበረክቱትን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ቀድመው ማጤን በመቻላቸው ነው ሲሉ ገልጸዋል።
አዘጋጆቹ አሁን ኢትዮጵያ የምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ፣ የጥንት አባቶቻችንን ዘመን ተሻጋሪ ጥበብ ለመዘከር የሚያስችል ማኅበረሰባዊ ስክነት ውስጥ እንዳንገባ አደርጎናል ብለዋል። ‹‹በዚህ ድንግዝግዝ ድባብ ውስጥ ሆነንም ቢሆን እንደ ሕዝብ ለዚህኛው ዘመን የተሻገሩትን ድንቅ ስጦታዎች እውቅና መስጠት ፋይዳው ዘርፈ ብዙ እንደሚሆን እናምናለን›› ሲሉም ጠቅሰዋል።
‹‹ያለፉትን ጊዜያት ማስታወስ፣ አሁን ያለውን ማኅበረሰብ እንደማስተሳሰር ይቆጠራል።›› ሲሉ በመግለጫቸው የጠቀሱት አዘጋጆቹ፣ ስለዚህም የኢትዮጵያ የፊደል ቀን በየዓመቱ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ሊከበር ይገባል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መሀይምነትን ለማጥፋት ከዚህ በፊት የተደረጉትን ጥረቶች እንደ መነሻ በመያዝ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ ንቅናቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው ያሉት አዘጋጆቹ፣ የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣትና በማስተባበር ‹‹ጥንታዊ ሥልጣኔ ያላትን አገር ወደሚገባት ስፍራ ለማድረስ እንጥራለን›› በማለት ገልጸዋል።
‹‹ቀኑን በደመቀ ሁኔታ በየዓመቱ ለመዘከር ተዘጋጅተናል።›› ያሉት የመሰናዶው አዘጋጆች፣ በዚህ ዓመት ለሚከበረው የመጀመሪያው ቀን ጥቅምት 17/2015ን እንደመረጡ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።
በዚሁ ቀንም ‹‹ያለፈውን፣ የአሁኑን እና የወደፊቱን በማስተሳሰር፤ ሀገራዊ መስተጋብር በመፍጠር ፊደላትን የሚያክል ማን አለ?›› በሚል መነሻ የኢትዮጵያ የፊደል ቀን በአገር ዐቀፍ ደረጃ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከብሮ እንዲውል በማሰብ የፊደላትን ሚና የሚያሳዩ የተለያዩ ትምህርታዊ የሆኑ ጥናታዊ ጽሑፎች፣ ምሁራዊ መጣጥፎች፣ ሥነ-ጥበባዊ ሥራዎች፣ ሙዚቃ እንዲሁም በተለያዩ ምሁራን ቀኑን አስመልክቶ የሚደረጉ ንግግሮችን ያካተተ መድረክ እንደሚኖር ታውቋል።
‹‹ይህ ቀን እንደ አገር በራሳችን መንገድ ከፍ ማለት የምንችል መሆናችንን የምናሳይበትና ለራሳችን እውቀቶች የምንሰጠው ቦታ ከፍ ያለ እንዲሆን መነሻ የምናደርግበት በመሆኑ ኹሉም የኅብረተሰብ ክፍል ቀኑን በማክበር ለዓላማው ያለውን ቀናኢነት እንዲያሳይ›› ሲሉም አዘጋጆቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
አዘጋጆቹ ይህንን ቀን በራሳቸው ተነሳሽነት ለማዘጋጀት እንደተነሱና ቀኑን አገራዊ ለማድረግ በማሰብ በርካታ ጥረቶችን ካደረጉ በኋላ ጥቅምት 17/2015 ለመጀመሪያ ጊዜ ለማክበር መወሰናቸውን ለአዲስ ማለዳ ከላኩት መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።<
ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015



