በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ኹለት ወረዳዎች የኮሌራ በሽታ መከሰቱን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
ተላላፊ በሽታው በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን መከሰቱን በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የባክቴሪያ በሽታ ቅኝትና ምላሽ ቡድን መሪ ሞቲ ኢዶሳ (ዶ/ር) ተናግረዋል። በሽታው የተከሰተው በሀረና ብሉክ እና በርበሬ ወረዳ መሆኑን ቡድን መሪው ጠቁመዋል። ቡድን መሪው መረጃውን ለአዲስ ማለዳ እስከገለጹበት ጊዜ ድረስ ከኹለቱ ወረዳዎች ኹለት ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ 115 ሰዎች በኮሌራ በሽታ ተይዘዋል ተብሏል።
በሀረና ብሉክ ወረዳ ዘገባው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አንድ ሰው በበሽታው ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን፤ በተደረገው የላብራቶሪ ምርመራ መሠረት 69 ሰዎች ኮሌራ በሽታ እንደተገኘባቸው ቡድን መሪው አብራርተዋል።
የኮሌራ በሽታ የተከሰተውና በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለው የሀረና ብሉክ ወረዳ አጎራባች በሆነችው በርበሬ ወረዳም ጭምር መሆኑ ተጠቅሷል። በመሆኑም በበርበሬ ወረዳ እስካሁን አንድ ሰው መሞቱንና በወረዳው በተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ 48 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተጠቁሟል።
ተላላፊ በሽታው የተከሰተው በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በሚገኙ ኹለት ወረዳዎች ብቻ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በዞኑ ኮሌራ ከተከሰተ አንድ ወር ማስቆጠሩም ተመላክቷል። በዞኑ ኮሌራ የተከሰተው ከአንድ ወር በፊት ነው ያሉት ቡድን መሪው፤ እስካሁን ግን በቁጥጥር ስር እንዳልዋለ ተናግረዋል።
በአገር ደረጃ ኮሌራ በሽታ ላለፉት ስድስት ወራት ጠፍቶ እንደነበር ቡድን መሪው አስታውሰዋል። ከባሌ ዞን ውጪ ያሉ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሌሎች ቦታዎች ግን ከበሽታው ነጻ መሆናቸውን ከተቋሙ በተገኘው መረጃ ማወቅ ተችሏል።
በተለይም ላለፉት ኹለት ዓመታት በመሠረተ ልማትም ሆነ በጤና ዙሪያ በርካታ ሥራዎች በመከናወናቸው በሌሎች አካባቢዎች ኮሌራ እንዳይከሰት ማድረግ መቻሉም ተነስቷል። ስጋት በነበረባቸው በአማራ፤ ደቡብና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በጉዳዩ ዙሪያ ሪፖርት እንደተደረገና ሪፖርቱ ሲታይም በኮሌራ የተያዘ ሰው እንደሌለ መረጋገጡን ቡድን መሪው ገልጸዋል።
በባሌ ዞን ብቻ ችግሩ የተከሰተበትን ብቸኛ ምክንያት፣ በሽታው ጥቃት እያደረሰባቸው በሚገኙ ቦታዎች የመሠረተ ልማት ችግር በመኖሩ ሳይሆን እንዳልቀረ ተመላክቷል።
“በሽታው በተለይም በሀረና ብሉክ ወረዳ በየዓመቱ ይከሰታል። አንዴ ተከስቶ ብዙ መሠረተ ልማት ላይ ካልተሠራ ደግሞ ወቅቱን ጠብቆ ይነሳል። በመሆኑም ለበሽታው መከሰት የውሃ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ የመሠረተ ልማት አለመሟላት ጋር የሚገናኝ ነው የሚሆነው።›› ብለዋል ቡድን መሪው።
አክለውም ኮሌራ የተከሰተበትን ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅ ግን ገና በጥናት ላይ ስለመሆናቸው ጠቁመዋል። በመሆኑም ተላላፊ በሆነው ኮሌራ በሽታ ሰለባ ላለመሆን ማኅበረሰቡ ከቻለ ወራጅ ውሃን ለመጠጥ ባይጠቀም ይመከራል ተብሏል። የወንዝ ውሃን ለመጠቀም አስገዳጅ ኹኔታ ካጋጠመ ደግሞ የውሃ ኬሚካሎችን መቀላቀል እንዲሁም ውሃውን አፍልቶ መጠቀም እንደሚገባ ቡድን መሪው አሳስበዋል።
ለዚህም የወንዝ ውሃን ለመጠቀም አስገዳጅ በሚሆንባቸውና በተለይም ኮሌራ በተከሰተባቸው ቦታዎች የውሃ ማከሚያ ኬሚካል አቅርቦት እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን፣ በበሽታው የተያዘ ሰው በአስቸኳይ ሕክምና ካገኘ በሽታው ወደ ሌላ ሰው እንዳይተላለፍ ማድረግ ይቻላል ተብሏል። ምልክቱ የታየባቸው ሰዎች በፍጥነት በአቅራቢያቸው በሚገኝ ጤና ጣቢያ ሄደው መታከም እንዳለባቸውም ተመላክቷል።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በዓለም ላይ በየዓመቱ ከ1.3 እስከ 4 ሚሊዮን ሰዎች በኮሌራ የሚያዙ ሲሆን፣ በበሽታው ከሚያዙት ሰዎች መካከል ዓለም በየዓመቱ ከ21 ሺሕ እስከ 143 ሺሕ ሞት ታስተናግዳለች።
ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015



