ሐሙስ መስከረም 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኬኒያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ (ዶ/ር) ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የኬኒያዉ ፕሬዚዳንት በአዲስአበባ በሚኖራቸው የሥራ ቆይታ የኹለቱን አገራት ትብብር እና ቀጠናዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዊሊየም ሩቶ በዛሬው ዕለት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገር አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት የማስጀመሪያ ሥነ ስርዓት ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በነሀሴ 3/2014 በተካሄደው የኬኒያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ መስከረም ወር ላይ በተከናወነው የፕሬዝዳንቱ በዓለ ሲመት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መገኘታቸው ይታወሳል።
ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ከበዓለ ሲመታቸው በኋላ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝታቸውን ከኢትዮጵያ መጀመራቸውም ታውቋል።



