የኦነግ አመራሮች አቀባበል ላይ አምባጓሮ በመፍጠር የተጠረጠሩት ወጣቶች የዋስትና ጥያቄ አቀረቡ

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በአዲስ አበባ የፖለቲካ አመራሮችን ለመቀበል በተዘጋጀው አቀባበል መርሃ ግብር ላይ አምባጓሮ በመፍጠር ከተከሰሱ ወጣቶች መካከል ዘጠኙ የዋስትና ጥያቄ አቀረቡ።

ከመስከረም 4 እስከ 7/ 2010 ዓ.ም መንግሥት በውጪ ያሉ የፖለቲካ ኀይሎች ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ ባቀረበው ጥሪ መሰረት የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር አመራሮች መግባታቸውን ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት ከአዲስ አበባ ወጣቶች ጎራ በመሆን አምባጓሮ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉት 17 ግለሰቦች መካከል ዘጠኙ እንዲከላከሉ ብይን መሰጠቱን ተከትሎ ነው የዋስትና ጥያቄው የቀረበው።

ከሳሽ አቃቤ ሕግ ‹‹የእርስ በእርስ ግጭት ላይ በመሳተፍ›› ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ያቀረበውን ክስ ወደ ‹‹አምባጓሮ›› የቀየረው ፍርድ ቤቱ፣ ክስ እና ምስክር ሰምቶ ካገባደደ በኋላ አንድ ተከሳሽ በቸልተኝነት ሰው በመግደል ወንጀል እራሱን እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል። ስድስት ተከሳሾች በከባድ አንባጓሮ ክስ ቢቀርብባቸውም ፍርድ ቤቱ በአምባጓሮ እንዲከላከሉ በይኗል። ኹለት ተከሳሾችም በተመሳሳይ በከባድ ውንብድና ክስ የቀረበባቸው ሲሆን ፍርድ ቤቱ በውንብድና እንዲከላከሉ ሲል ብይን ሰጥቷል።

ክስ ከተመሰረተባቸው 17 ግለሰቦች ስድስቱ ባለመቅረባቸው ምክንያት ክሳቸው የተቋረጥ ሲሆን የተፈጠረውን ግጭት ሽፋን በማድረግ የስርቆት ወንጀል በመፈጸም የተከሰሱትን ግለሰብ በነፃ አሰናብቷል።

ከኦሮሚያ ክልል የኦነግን አመራሮች ለመቀበል የመጡ ወጣቶች የፓርቲውን አርማ ለመስቀል እንዲሁም ቋሚ ቀለሞችን በሚቀቡበት ወቅት ከቀናት በፊት ወደ ሃገር የገቡትን የግንቦት ሰባት አመራሮች ለመቀበል በመዲናዋ አዲስ አበባ የተሰቀሉ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ባንዲራዎችን እንዲሁም በተመሳሳይ የተቀቡ ቀለሞችን አትቀይሩ በሚሉ ወጣቶች መካከል በተፈጠረው ግጭት ነው አቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተው።

ከዋዜማው መስከረም 04/2010 ጀምሮ የተጀመረው ግጭቱ በተለይም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ፣ አዲስ ክፍለ ከተማ እንዲሁም ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ግጭቱ ተንሰራፍቶ የታየባቸው ናቸው ሲል ማስረጃውን ያቀረበው አቃቤ ሕግ፣ በዚህም የሰው ሕይወት እንዲጠፋ፣ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንዲደርስ እንዲሁም በንብረት ላይ ከፍተኛ ጥፋት ለመድረሱ ምክንያት ሆነዋልም ብሏል።

ብይኑን ተከትሎ ሐሙስ ጥቅምት 2012 ተከሳሾቹ የዋስትና ጥያቄ ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን በማግስቱ አቃቤ ሕግ አስተያየቱን እንዲያቀርብ በተጠየቀው መሰረት መልስ ሰጥቷል። በውንብድና የከተከሰሱት ኹለት ተከሳሾች የተጠቀሰባቸው አንቀፅ ዋስትና የማያስከለክል በመሆኑ በዋስ ቢለቀቁ ተቃውሞ የለኝም ያለው አቃቤ ሕግ፣ ሌሎች በቸልተኝነት የሰው ነፍስ በማጥፋት ወንጀል የተከሰሱት ግለሰብን ጨምሮ ሌሎች ሰባት ተከሳሾች ግን በዋስ ሊፈቱ አይገባም ሲል ተቃውሟል።

የተከሰሱበት አንቀፅ ከ 15 ዓመት በላይ በሆነ ፅኑ እስራት የሚስቀጣ በመሆኑ እና ተከሳሾች የተጠረጠሩበት ወንጀል ምክንያት የሞተ ሰው በመኖሩ በሕጉ መሰረት ዋስትና ቢሰጣቸው ተቃውሞ እንዳለው ጠቅሷል። በዋስትና ጉዳዩ ላይ የግራ ቀኙን አስተያየት የሰበሰበው ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት ለሰኞ ጥቅምት 17/2012 ቀጠሮ ሰጥቷል።

በተመሳሳይ በመስከረም 2010 በቡራዩ ከተማ የተቀሰቀሰው ግጭት በሰው ሕይወት፣ አካል እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦችን ጨምሮ ከ መስከረም 4 እስከ 7/ 2010 በተፈፀሙ ግጭቶች በተከሰሱ ግለሰቦች ላይ ክስ እና ምስክር የመስማት ሒደት ተጠናቆ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ መሰጠቱን አዲስ ማለዳ ከፌዴራሉ ፍርድ ቤት ያገኘቸው መረጃ ይጠቁማል።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here