የከረሜላ ምርቶችን በማመሳሰል ኹለት አምራቾች ቅጣት ተጣለባቸው

0
1008

ሎያል ኪንግ እና ዘ ዊነርስ የተሰኙ ኹለት ከረሜላ ፋብሪካዎች አዲስ ከረሜላ ፋብሪካ ከሚያመርታቸው ከረሜላዎች መካከል አንዱ የሆነውን የሜንታ ከረሜላ ማሸጊያ አመሳስለው በማምረት ለገበያ በማቅረባቸው ከዓመታዊ ገቢያቸው አምስት በመቶውን ለመንግሥት ገቢ እንዲያደርጉ ቅጣት ተላለፈባቸው።

የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን አስተዳደራዊ ችሎት ጥቅምት 4/2012 ባስቻለው ችሎት ፋብሪካዎቹ ማሸጊያ በማመሳስል ሎያል ሜንት እና ዜድ ሮሜ የተሰኙ ከረሜላዎችን በማምረት ኢ-ፍትኀዊ የንግድ ውድድር እና ለሸማቾች አደናጋሪ ምርቶችን በማምረት ጥፋተኛ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ ሲል ወስኗል።

አዲስ ከረሜላ ፋብሪካ ከሚያመርተው ሜንታ ከረሜላ ጋር በቅርፅ፣ በዲዛይን በምስል እና በማሸጊያው ቀለም በማመሳሰል ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚዎችን እና ነጋዴዎችን በማደናገር ፍትኀዊ ያልሆነ የንግድ ውድድር ተደርጎብኛል ሲል ለባለሥልጣኑ አቤቱታውን አስገብቷል።

ፋብሪካው ‹‹ከኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በንግድ ስያሜ የባለቤትነት መብት እንዳለን እየታወቀ አስመስሎ በማምረት በደንበኞቻችን ላይ ከተከሰተው መደናገር ባሻገር ለኪሳራ ዳርገውኛል›› ሲል አመልክቷል።

ተከሳሾችም በበኩላቸው ከሳሽ ከኢትዮጵያ እምሮኣዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ጥበቃ የተደረገለት ለንግድ ምልክቱ ነው እንጂ ለማሸጊያው ቀለም አይደለም፤ ሜንታ የሚለው ከረሜላ ሲታሰብ በማንኛውም ሰው አዕምሮ ውስጥ ሊመጣ የሚችለው አረንጓዴ ቀለም ነው፤ ሜንታን ያለ አረንጓዋዴ ቀለም ማሰብ አይቻልም። በመሆኑም ለአንድ ድርጅት ብቻ በባለቤትነት ሊሰጥ አይችልም፤ ፍትኀዊነትን የሚያጓድል ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

‹‹እኛ ከረሜላዎቹን የምናመርተው ከንግድ ሚኒስቴር በተሰጠን የራሳችን ስያሜ ነው፣ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የማሸጊያዎቹን ናሙና በመመልከት በሰጠው ምላሽ ሜንታ ከሚለው ከረሜላ ጋር ይመሳሰላል የሚል ነው እንጂ በሸማቹ ላይ መደናገርን ይፈጥራል የሚል አይደለም›› ሲሉ አቤቱታቸውን አሰምተዋል። ጽሕፈት ቤቱ ይመሳሰላል ቢል እንኳን ጉዳዩ ሊለይ የሚገባው ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት እንጂ በጽሕፈት ቤቱ አይደልም የሚል አቤቱታ ያሰሙት ድርጅቶቹ፣ ምርቱን ያሸጉበት ወረቀት አመልካች ከሚለው ጋር በስምም ይሁን በቀለም አይመሳሰልም ሲሉ ክሱን ተቃውመዋል።

የባለሥልጣኑ አስተዳደራዊ ችሎት ሜንታ የሚለው ቃል እና በሽፋኑ ላይ ያለው ምስል በንግድ ምልክትነት በአዲስ ከተማ ከረሜላ ፋብሪካ መመዝገቡን እና ጥበቃ እንደሚደረግለት አረጋግጧል። በሌላ በኩል ንግድ ምልክት ማለት ዕቃዎችን እና አገልግሎቶችን ለመለየት የሚያስችል የሚታይ ምስል ያለው ነው፣ ተከሳሾች የሚጠቀሙበት የንግድ ምልክት ከከሳሽ ጋር የሚመሳሰል በመሆኑ ነጋዴዎችን እና ሸማቾችን ማደናገሩ የማይቀር ነው ሲል ገልጿል።

ጉዳዩን ያየው የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን አስተዳደር ፍርድ ቤት ችሎት፣ ተከሳሾቹ ሎያል ኪንግ እና ዘ ዊነርስ ‹‹ሎያል ሜንት እና ዜድ ሎያል›› በሚል ስም ለሚያመርቷቸው ከረሜላዎች ከ ‹‹ሜንታ›› ከረሜላ ጋር የሚመሳሰል ማሸጊያ መጠቀማቸው ሸማቾችን እና ነጋዴዎችን የሚያደናግር እና የሚያሳስት በመሆኑ ኹለቱም ድርጅቶች ከ 2011 ዓመታዊ ገቢያቸው ላይ 5 በመቶ እንዲቀጡ የወሰነ ሲሆን፣ ምርቶቹንም ውሳኔው ከተላለፈበት ቀን ጀምሮ ከሜንታ ከረሜላ ማሸጊያ ጋር በማመሳሰል እንዳያመርቱ እና ለገበያ እንዳያቀርቡ ሲል ውሳኔ አስተላለፏል።
ዘገባው እስከተጠናቀረበት ጊዜም ከሳሽ፣ የባለሥልጣኑ አቃቤአን ሕጎችም ሆኑ ተከሳሾች ይግባኝ አላሉም።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here