የፈተናው ፈተና

0
1369

ሰሞኑን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያስገባቸውን ፈተና የሚፈተኑ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች የፈተና እና የአፈታተን ነገር ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህም ይኸው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተና ራሱ ፈተና የበዛበት ሆኗል።

የፈተና መሰረቅና የጉዳዩ ፖለቲካዊ መልክ መያዝ ብዙዎችን ሲያሳስብና ሲያነጋግር ቆይቷል። ይህንን ተከትሎ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ‹ተማሪዎችን ከፈተና ስርቆትና ኩረጃ በመጠበቅ ተረጋግተው እንዲፈተኑ ያስችላል› ያለውን የአፈታተን ሥርዓት አስተዋውቋል። በዚህም የመፈተኛ ቦታው ዩኒቨርሲቲ፣ ፈተናው ደግሞ በተለያዩ 12 ኮዶች የተዘጋጀ መሆኑ ነው ይፋ የተደረገው።

ይህን ተከትሎም ማኅበራዊ ሚድያው ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ታይቷል። በተለይም ተማሪዎች ስልካቸውን ይዘው የማይገቡ መሆኑና ወላጆችም ልጆቻቸውን በምን ልናገኛቸው ነው ብለው የመስጋታቸው ነገር መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።

የተፈታኝ ተማሪዎች ወላጆችም ሆኑ ተፈታኝ ተማሪዎቹ ራሳቸው ተጨንቀው እንዳሉ በተደጋጋሚ ሲናገሩም ተስተውሏል። በዚህ ሥርዓት መሠረት ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሲደረግ፣ ተፈታኞች የፈተናው ጊዜ እስኪጠናቀቅ በዛው ይቆያሉ። ማደሪያና ምግባቸውም በዛው ይሆናል። ከዚህም በተጓዳኝ ፈታኞች በሙሉ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ናቸው። ይህ ሁሉ ለተፈታኞቹ አዲስና የመጀመሪያቸው ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁበት የተወሰነ መሆኑም ሳያስጨንቃቸው አልቀረም።

ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸውን ፈተና በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለመፈተን የተዘጋጁት ተማሪዎች፣ የፈተና ክፍሎቹ የወንበሮች አቀማመጥ ምን ሊመስል እንደሚችል የሚያሳዩ ምስሎችና እያጋሩ ታይተዋል። ከዚህ ባለፈ ከአፈታተኑ ጋር በተገናኘ ከተነሱ ስጋቶች መካከል የፈተና ሥርዓቱ ‹ወላድ ለሆኑ ተፈታኝ እናቶች ምን አስቧል? ልጆቻቸውን ይዘው ፈተናው ወደሚሰጥበት ጊቢ መግባት ይችላሉ ወይ?› የሚለው ይገኝበታል።

በሌላ በኩል አፈታተኑ ላይ ሳይሆን የትምህርት ጥራቱ ላይ ብታተኩሩ ይሻላል የሚሉ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ተስተውሏል። በትምህርት ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ተቋማት መጀመሪያ ራሳቸውን እንዲያጸዱ ሐሳብ የሰጡም አልጠፉም። ‹ኧረ እንደው የዚህ ፈተና ማለቂያ ቀን ናፈቀኝ› ብለው ገና ፈተናው ሳይጀመር ፍጻሜውን ለማየት የጓጉ መሆናቸውን የጠቀሱም አሉ።

ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ‹ይሄ እንደውም አድቬንቸር ነው። ከቤት ወጥተው ዩኒቨርሲቲ ሄድው ይፈተናሉ። ይህ አዲስ ነገር ነው።›› ሲሉ ተማሪዎቹ ሁኔታውን እንደልምድ እንዲወስዱት መክረዋል። እንዲሁም የፈተና አሰጣጥና የልጆቻቸውን ደኅንነት በሚመለከት ወላጆች እንደሚያምኗቸው ተስፋ እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል።

ወላጆች የልጆቻቸው ደኅንነትና ጤንነት፣ በሰላም መግባትና መውጠት እንዲነገራቸው የሚያስችል አሠራር መኖሩንም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ነገሩ ፈተና ለበዛበት ይኸው የ12ኛ ክፍል ፈተና ምን ያህል መፍትሔ እንደሚሆን፣ የሚወጣበትን ጊዜ፣ ጉልበት እንዲሁም ወጪ የሚክስ ስለመሆን አለመሆኑም ጊዜ ዳኛ ሊሆን ቀን እየተቆጠረ ነው። ለተፈታኞች ሁሉ፣ መልካም ፈተና!


ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here