ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ መንገደኞች ወደ ከተማይቱ ለመዝለቅ የብሔር ማንነታቸው እየታየ መሆኑ ሲሰማና ሲታይ ቆይቷል። የመንገደኞች እንግልትም እንግዳ ነገር እየሆነ አይደለም። ከከተማ ወደ ሌላ ከተማ በሚደረግ ጉዞ መካከልም በየቦታው ምን ሊያጋጥም እንደሚችልና ማን እንደሆነና ለምን እንደሆነ ባልታወቀ አካልና ምክንያት መንገድ ይዘጋል። ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም፤ ይህ መንገድ የመዝጋት አመል በከተማ መካከል የተለያዩ ሰፈሮች ውስጥም አለ ያለችው መቅደስ ቹቹ፣ በጉዳዩ ላይ እንደሚከተለው ሐሳቧን አጋርታለች።
እየለመድናቸው ከመጡና ከተጠናወቱን አመሎች መካከል ከተቀላቀለ ሰነባብቷል፤ መንገድ የመዝጋት ነገር። ከዚህ አካባቢ ከሆናችሁ፣ የዚህ አካባቢ ተወላጅ የሆናችሁ፣ የዚህ ብሔር አባላት እየተባለ እየተነጠለ ሰዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሻቸው ላይ በር ሲከፈትና ሲዘጋ እየተመለከትን ነው። በእርግጥ ነገሩን ጠቅለል አድርጎ ማንሳት ስለሚበጅ እንጂ በአብዛኛው ከመገናኛ ብዙኀን እንደተረዳነው ወደ አዲስ አበባ አትገቡም የሚባሉትና ከባድ ችግር የሚገጥማቸው የአማራ ብሔር ተወላጆች ናቸው። እንዴት ያለ ጉድ ነው?
የሞተ ዘመድን ቀብሮ መመለስ ወይ ለቀብር መሄድ፣ ለመማር ወይም ለሥራ አልያም ለዘመድ ጥየቃ፣ ንቅንቅ አትበሉ የተባልን ይመስላል። መዝናናትና አገር ማየትማ ቅንጦት ናቸው። አንዱ መንገድ ላይ አንድ ቡድን ወይም የመንግሥት ነኝ ያለ አካል መንገዱን ዘግቶ ‹አታልፉም!› ሊል ይችላል። በአንድ አገር ላይ ከዚህ የባሰ ስርዓት አልባ መሆን ከወዴት እንዳለ አላውቅም።
በዚህች በአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ላይ እንኳ በተደጋጋሚ የተዘገቡ ወደ አዲስ አበባ አትገቡም የተባሉ ዜጎች ቅሬታ ተቆጥሮ የሚያልቅ ዓይነት አይደለም። በአንድ በኩል ያለው የደኅንነት ስጋት ይህን እንዳስከተለ ሲነገር ይሰማል። በእርግጥም ይህ ጉዳይ እንደምክንያት ተጠቅሶ መንገድ መዝጋቱና ፍተሻውን ለመረዳት ሙከራ ብናደርግ እንኳ፣ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚመጡ ሰዎች ላይ በር መዝጋት አያስሄድም። የሚገርመው ደግሞ የአየሩ ጉዞ እንዲያ ያለ ክልከላ የለበትም።
ይህ ጉዳይ መች እልባት እንደሚያገኝ ለመገመት አይመችም። እየተራዘመ ኹለት ዓመታት የተጠጋው ጦርነት እንኳ ሄድ መለስ እያለ መጨረሻው እንዳይገመት ሆኗል። እንዲህ ያለው መንገድ የመዝጋትና የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት የማያከብር ስርዓት አልባነት ግን የባሰውን መች ሊቋጭ እንደሚችል አይታወቅም።
በቅርቡ መስከረም 21/2015 የተከበረውን የኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ ወደ አዲስ አበባ ከሚመጡ ሰዎች መካከል በአንዱ አቅጣጫ ያሉት እንዳይገቡ መደረጉ ይታወሳል። የዚህ ዓላማ ግልጽ ካለመሆኑ በላይ በፌዴራሉ መንግሥት በኩል የተሰጠ አንዳች አስተያየት አልነበረም። በእርግጥ በየቀኑ ስንት ንጹሐን የመኖር መብታቸውን እያጡ በግፍ ሲገደሉስ ምን ተሰምቶ ያውቅና!
ታድያ መንገዱን በተመለከተ የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን አነጋገርናቸው ያሏቸው የሚመለከታቸው የተባሉ ኃላፊዎች፣ ‹ስለሁኔታው አናውቅም። የምናውቀው ፍተሻ እንዳለ ብቻ ነው።› የሚል ዓይነት ምላሽ እንደሰጧቸው አስታውቀዋል። አሸባሪዎች እንኳ ለሠሩት ወንጀል ኃላፊነት በሚወስዱበት ጊዜ፣ መንገድ ዘጊው አካል ግን ‹እኔ ነኝ እንዳይገቡ የከለከልኩት፤ በዚህ በዚህ ምክንያት ነው› ብሎ ለመናገር አልደፈረም።
በእርግጥ የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት ለመጣስ ምክንያት መደርደር ዋጋ የለውም። ያም ሆኖ ግን ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ከግምት በማስገባት፣ የመንቀሳቀስ መብት ላይ ቁጥጥርና ክትትል ቢኖር እንኳ፣ ይህን በስርዓትና በአግባብ እንጂ የሰዎችን ደኅንነት ስጋት ውስጥ በመክተትና በማንገላታት መሆን አልነበረበትም።
እዚህ ላይ ያዝ አድርጌ ስሜቴን ላጋራችሁ። አንዳንዴ አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮች ሳይቀር ቅንጦት መስለው እንደሚታዩ ይሰማኛል። በየእለቱ ንጹሐን ዜጎች በግፍ እየተገደሉባት ባለች፣ ሞት ቤተኛ በሆነባት፣ ክፉ ዜናም እንደ አውሮ ዶሮ ድምጽ ማልዶ በሚሰማባት፣ የበጎቻቸው ነገር እንደማያስጨንቃቸው እረኞች የሆኑ፣ የዜጎቻቸው ደኅንነት ግድ የሚላቸው የማይመስሉ መሪዎች ምድር በሆነች፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆችና አዳጊዎች ከትምህርት ተፈናቅለው ‹ዋ!› ብለው መከራ እየተማሩ ባሉባት አገር፤ ‹መንገድ ተዘጋብን› ቅንጦት ሊመስል ይችላል።
ግን ይህ ከተስፋ ጋር የተገናኘ ነው። ሰው ‹ቢያንስ እንዲህ ነው…› እያለ በመከራው መካከል የሚጽናናበት አንዳች ነገር ያሻዋል። አሁን አሁን ‹ቢያንስ ወንድሜን ቀብሬአለሁ› እስኪባል ድረስ ዘመድን መቅበርም አንድ ትልቅ ነገር መሆን ላይ ደርሷል። እናም እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ዜጎች ላይ የሚደርሱ እንግልቶች ‹ቢያንስ…› የምንልባቸውን የሕይወት ክፍሎች ሳይቀር የሚነጥቁ ናቸው። በስንቱ እንበደል?
አቤቱታ የማያሰማ የለም፤ ስንቱ በሚመለከተው አካል እየተሰማ እንደሆነ ግን አናውቅም። የዜጎች ጩኸት መሪዎች ጋር ምን ምን እንደሚል እንጃ! ቋንቋ ተቀያይረን አልያም እንደ ባቢሎን ግንብ ሠሪዎች ቋንቋችን ተደበላልቆብን መግባባት ትተን ከሆነም አላውቅም። አልያም ‹ከዚህ የባሰ ስንት አንገብጋቢ ጉዳይ አለብን!› እያሉ እንደሆነስ? ማን ያውቃል። ‹ተዉአቸው! አሁን ይረሱታል!› እየተባልን ከሆነም አይታወቅም። እንጂ እንዲህ ጩኸት የበረከተበት ዘመንን ይህ ትውልድ ዐይቶ የሚያውቅ አይመስለኝም። እንዴት ነው ያልተሰማው?
መንገዶች የተዘጉት በአካል ብቻ ሳይሆን እንዲህ በአንደበትና በጆሮ መካከልም ይመስለኛል። በመንግሥት በኩል መናገር ብቻ፣ በሕዝብ በኩል መጮኽ ብቻ። ‹ግመሎቹ ይሄዳሉ፣ ውሾቹ ይጮኻሉ› የሚለው ብሂል ለሁሉም ጉዳይ ይሠራል እንዴ? ግመሎቹ ወዴት ነው የሚሄዱት፣ ውሾቹስ ለምንድን ነው የሚጮኹት ብለን መጠየቅ አይገባም? ሁሌም ግመሎች ወደ ትክክለኛው መንገድ ተጓዥ ብቻ፣ ውሾችም ያለምክንያት ግመል ስላዩ ብቻ የሚጮኹ ናቸውን? እንደውም ጩኸታቸው የሚቀሰቅስ፣ የሚጣራ፣ ንቁ የሚል አይደለምን?
ሰሚና አድማጭ ከመንግሥት ጀምሮ ያለ አይመስልም። ሁሉም አስተያየት አለው፤ ሁሉም ተናጋሪ ነው። ስለዚህ የመግባቢያው መንገድም በዚህ የተነሳ ተዘግቷል። ሁሉም ተንታኝና አስረጂ ነው፤ ስለዚህ መፍትሔ ከየት ይመጣል? ሁሉም ‹እኔ ነኝ ትክክል› ይላል፤ ስለዚህ እርማት አድርጎ መላ ማግኘት እንዴት ይቻላል? ይሄ የሌሎች ሐሳብ፣ የሰዎች ዕይታ እና አስተያየት ወደ ጆሯችን እንዲገባ አለመፍቀድም መንገድ መዝጋት ነው። በተለይ ይህን ድርጊት አገር የሚገዛና የሚያስተዳድር መንግሥት ሲያደርገው በእጅጉ ኪሳራው ይጨምራል። በእርግጥም ደግሞ ከሕዝብ ወደ መንግሥት ጆሮ የሚያደርሱ መንገዶች ብዙውን ጊዜ ዝግ ናቸው።
የልቦናም ሆነ የአካላዊ፣ መልዕክት እና አቤቱታን ወደ ልብ የሚያቀርቡ መንገዶች ይከፈቱ። መርጦ መስማት ይብቃ። ‹ሰው ከሰው አያንስም፤ አይበልጥም› የሚለውን መሠረታዊ ጉዳይ ዓለም በተማረባትና የጥቁርና የነጮችን ልዩነት በሰውነት ኃይል ድል ባደረገች አገር፣ ሰውን በሚናገረው ቋንቋ ለይቶና ብሔሩ መርጦ መቀበል ወይም መግፋት ይብቃ።
መንግሥትም ዝም አይበል! ዝም ማለት እንደመስማማት አይደለ? በመንገድ መዘጋቱ ተስማምቷል፣ በሚደርሰው ብሔር ተኮር ጭቆና እና በደል ቅሬታ የለውም፣ የሚታየውን ግፍና በደል አይቃወምም ማለት ነው። ወይም ለመቃወም የሚያስችለውን አቅም እና ሥልጣን የሚገዳደር ኃይል አለበት ማለትም ነው። ያም ብቻ ሳይሆን፣ እጁ አለበት ለማለትም ያስደፍራል። እንዲያ ከሆነ ደግሞ ‹አባቱ ዳኛ…› ይሉት ብሂል ይመጣልና፣ ሁሉም ነገር ዋጋ ያጣል። አቤቱታን ለማን እናቅርብ የሚለውም እንደ አዲስ ጥያቄ ሆኖ ይነሳል ማለት ነው። እንግዲህ ባልተሰጠ መልስ ባዶውን ቦታ በዚህ ሁሉ ልንሞላው እንችላለን ማለት ነው።
በነገራችን ላይ፤ ይህን እንደ አገር በብሔራዊ ደረጃ የሚፈጸም ስርዓት አልባ የሚያሰኝ ድርጊት፣ በከተማችን አዲስ አበባ ውስጥ በየጓዳው የሚታይ ነው። እኔ በቅርብ የማውቀውን የራሴን ሰፈር ልጥቀስ። በሰፈራችን ካሉ የመኖሪያ ቤቶች በሮች ይለቅ የሚበዛው የተወሰኑ በቅርብ ያሉ ቤቶች ሰብሰብ ብለው በጋራ የሚያስቀምጧቸው አጥሮችና በሮች ናቸው።
በቅርብ በማውቀው ‹በዚሀ ጋር አትለፉ› እያሉ ድንጋይ እየደረደሩ መንገድ ከሚዘጉ የአንዳንድ ሰፈር ነዋሪዎች በተጨማሪ፣ ገንዘብ አዋጥተው አጥርና በር የሚያስገነቡ እና ያስገነቡ አሉ። ይህን የሚያደርጉት ‹የጋራ ደኅንነታቸውን› ለመጠበቅ እንደሆነ ቢናገሩም፤ መንገዱ የብዙኀን ነውና መንገዱን ዘግቶ አታልፉም እናልፋለን የሚል ንትርክ መፈጠሩ አልቀረም። እርግጥስ መንገደኛ በየት በኩል ይለፍ?
ወትሮ በረጃጅሙ የሚሠሩ የፍጥነት መቀነሻዎች ነበሩ አወዛጋቢ የነበሩት። እንደው ፍጥነት መቀነሻውን ያሠሩት ሰዎች ቤት ነፍሰጡር ሴት ብትኖር ያንን ያደርጉት ይሆን ብዬ ጠይቄ አውቃለሁ። አንቡላንስ እንዲገባ ግድ ቢልስ እንዴት ይሆናል ብዬም አስባለሁ። ሰው እንዴት ነገሮችን በሚገባ ማገናዘብ ይሳነዋል ያሰኛል።
በእነዚህ የሰፈር የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ የሚደረጉ መንገድ የመዝጋት አመሎች በተለይ ምሽት ላይ ይበረታሉ። ያም በሩ ጋር እንደሚቆሙ የጥበቃ ባለሞያዎች የግል ጠባይ የሚወሰን ቢሆንም፣ እንደልብ የመንቀሳቀሱ ነገር ግን ውሃ በልቶታል። ከዛም ባሻገር ዋናውን የአስፋልት መንገድ ሊያስተነፍሱ የሚችሉ መንገዶች ሳይቀር በአካባቢው በሚኖሩ ግለሰቦች የግል ፍላጎት ተዘግተው ማየት ቅር ያሰኛል።
ይህን በሚመለከት የክፍለ ከተማ አስተዳደርና ወረዳዎች አጥሮችና በሮች እንዲነሱ የማድረግ ኃላፊነት ወስደው ያስፈጽማሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። እንግዲህ ቸልታ የበረታበት፣ መርሳት ያየለበትና ገንዘብ ገዢነቱን እያጣጣመ ያለበት ጊዜ ነውና፤ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል። ለዚህም ብዙ ምስክሮች በየሰፈሩ እንዳሉ አልጠራጠርም።
እና የልባችን በር ይከፈት፤ አይዘጋ። እርስ በእስር እንድንግባባ ያደርጋልና ወደ ቀደመ አንድነታችን ሊመልሰን ይችላል። ለመስማትና ለማዳመጥም ዝግ አንሁን፣ አንዳችን ሌላችንን ተረድተን ለውጥ የምናመጣው ስንደማመጥ ብቻ ነው። የከተማ መግቢያና መውጫ መንገዶቻችንም ይከፈቱ፣ ለመከፈትም ሆነ ለመዘጋት የሰውን ብሔርና ማንነት አይለዩ፤ እነዚህ የየግል የኑሮ ሩጫችንን የምንጓዝባቸው ናቸው። ቢያንስ ይህን እንኳ አንነፈግ! ቢያንስ ይህን መንገድ የመዝጋት አመል እንኳ እንተው። ብዙ ከዚህ የባሰ ፈተናና ችግር አለብን እና በዚህ ላይ ጊዜና ጉልበት፣ አቅምና መንፈስ አናባክን። ቸር ያሰማን!
ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015



