ፓውንድ 115 ብር ደርሷል
የአንድ ዶላር የጥቁር ገበያ ምንዛሬ በባንክ ከሚመነዘረበት ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ 105 ብር እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ማለዳ በግብይቱ ላይ ባደረገችው ክትትል ተመልክታለች።
አሁን ላይ ዶላርና ፓውንድ በባንክ ከሚመነዘሩበት ዋጋ እጥፍ በሆነ ዋጋ በጥቁር ገበያ እየተመነዘሩ ነው። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ አንድ ዶላር በባንክ 52 ብር 63 ሳንቲም የሚመነዘር ሲሆን፣ ከጥቁር ገበያ ጋር ያለው ልዩነት 52 ብር 37 ሳንቲም ነው። የአንድ ፓውንድ የባንክ ምንዛሬ 57 ብር ከ 13 ሳንቲም ሲሆን፣ በጥቁር ገበያ ከሚሸጥበት ዋጋ ጋር ያለው ልዩነት 57 ብር ከ87 ሳንቲም ነው።
እስከ መስከረም 26/2015 ድረስ አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ከተማ የጥቁር ገበያ በሚከናወንበት ብሔራዊ አካባቢ ተገኝታ፣ በገበያው ላይ ተሳትፎ ያላቸውን ሰዎች እንደ መንዛሪ ሆና በመቅረብ ባደረገችው ማጣራት የጥቁር ገበያ ምንዛሬው ዋጋ መንዛሪው በሚያቀርበው ዶላር ብዛት የሚወሰን ነው። በዚህም የአንድ ዶላር የጥቁር ገበያ መሸጫ ከ98 ብር እስከ 105 ብር ሲሆን፣ አንድ ዶላር መንዛሪ ከ100 ዶላር እስከ እስከ 500 ዶላር ካቀረበ ከ98 እስከ 100 ብር ይመነዘርለታል።
የጥቁር ገበያ ዋጋው እንደየ ዶላሩ ብዛት የሚመወሰን ሲሆን፣ የዶላሩ ብዛት ከ500 እስከ 1 ሺሕ ከሆነ የአንድ ዶላር ምንዛሬ ዋጋ እስከ 103 ብር ይታሰባል። ከ1 ሺሕ ዶላር በላይ ላቀረበ ባለ ዶላር የጥቁር ገበያ ነጋዴዎቹ ያለማቅማማት በአንድ ዶላር 105 ብር አስልተው እንደሚከፍሉ አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ ባደረገችው ክትትል ታዝባለች።
የጥቁር ገበያ ምንዛሬ ዋጋው ዶላር አቅራቢው እንደሚያቀርበው ብዛት ዋጋው ከፍና ዝቅ የሚል ቢሆንም፣ ግብይቱ በተዋረድ የሚሠራ መሆኑን ተከትሎ በጥቁር ገበያ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች “ዋናዎቹ” የሚሏቸው አካላት አሉ። በዚህም በቀጥታ “ዋናዎቹ” ከሚሏቸው አካላት ጋር ግንኙነት ያላቸው ወይም የገዙትን ዶላር ለ“ዋናዎቹ” የሚያቀርቡት ገዢዎች ዋጋ ከፍ አድርገው ይገዛሉ። ይህ የሆነበት ምክንያት የጥቁር ገበያ ዶላር ግብይት ሰንሰለቱ፣ በአንድ ገዢ በቀጥታ ወደ “ዋናዎቹ” ሲደርስና ብዙ ቅብብሎሽ ሲኖርበት በሥራው ላይ በተሰማሩ አካላት ትርፍ ላይ ልዩነት ስላለው መሆኑን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
በጥቁር ገበያ የዶላር ዋጋ በሚጨምርበት ፍጥነት አብዛኛውን ጊዜ የተጋነነ ጭማሪ የማይታይበት የፓውንድ ጥቁር ገበያ ዋጋ፣ በባንክ ከሚመነዘርበት ዋጋ ከእጥፍ በላይ አድጎ አንድ የእንግሊዝ ፓውንድ 115 ብር እየተሸጨ ነው። ፓውንድ በጥቁር ገበያ ላይ ያለው የምንዛሬ ዋጋ መጠን የሚወሰነው እንደ ዶላር እንደ ብዛቱ ቢሆንም፣ በብዛት አንድ ፓውንድ 115 ብር የሚመነዘረው እስከ 2 ሺሕ ፓውንድ በአንድ ጊዜ ሲቀርብ ነው።
በኢትዮጵያ የዶላር ምንዛሬ በሕጋዊ መንገድ በባንክ ከሚደረገው ግብይት ይልቅ፣ ከባንክ ውጪ በጥቁር ገበያ ወይም በትይዩ ገበያ የደራበት ሁኔታ በተለይ ባለፉት ተከታታይ ሦስትና አራት ዓመታት ተስተውሏል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የጥቁር ገበያ አንድ ዶላር በባንክ እና ከባንክ ውጪ የሚመነዘርበትን ዋጋም በከፍተኛ ፍጥነት እያሰፋው ቀጥሏል።
የውጪ ገንዘቦች የጥቁር ገበያ ዋጋ ከባንክ ምንዛሬ በሰፊ ልዩነት ያደገው የውጪ ምንዛሬ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ስለመጣ ነው ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደ ምክንያት ያነሳሉ። እንደ ብሔራዊ ባንክ፣ ገንዘብ ሚኒስቴርና የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የውጪ ምንዛሬ እጥረት መኖሩን በተለያየ አጋጣሚ ሲገልጹ ነበር። ይኸው እጥረት የውጪ ገንዘቦችን ለተጋነነ የጥቁር ገበያ ከማጋለጡ ባሻገር፣ በመንግሥት ከሚሠሩ የልማት ሥራዎች እስከ ግሉ ዘርፍ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ስለመሆኑ በተደጋገሚ ይሰማል።
በተያያዘ አርብ መስከረም 27/2015 የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፤ 391 የሚደርሱ ሕገወጥ የሐዋላ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የባንክ ሒሳባቸው መዘጋቱን እና የግለሰቦቹን ሥም ዝርዝር ለፍትሕ ሚኒስቴር በመላክ ክስ የመመሥረት ሂደት መጀመሩን አስታውቀዋል። በሕገ ወጥ መልኩ በጥቁር ገበያ በተሰማሩ አካላት ላይ የተጠናከረ እርምጃ ይወሰዳልም ብለዋል።
‹‹በባንክ ቤቶች ውስጥ ያሉ የባንክ ኃላፊዎችና ሠራተኞችም በሕገወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አሉ። በእነዚህ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል።›› ማለታቸውም ተጠቅሷል። ባንኩ ይህን ሕገወጥ ድርጊት ለሚጠቁሙ ዜጎች የወሮታ አከፋፈል ሥርዓት መዘጋጀቱንም ይፋ አድርጓል።
ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015



