የህዳሴው ግድብ እና ዓለም ዐቀፍ ሕግ

0
1135

የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የተለያዩ ውዝግቦችን እየተሻገረ አሁን ካለበት ደረጃ ደርሷል። ግብጽም የአባይ ውሃ ብቸኛ ተጠቃሚ ነኝ በማለት፣ የውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ የተለያዩ ሕጎችና ስምምነቶችን በመጥቀስ በተለያየ መንገድ እንቅስቃሴዎችንም ስታደርግ ተስተውሏል። ስንታየሁ ግርማ ይህን ነጥብ በማንሳትና የኢትዮጵያን እውነት በመጥቀስ፣ የሕዳሴውን ግድብ ከተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ሕጎች አንጻር እንደሚከተለው አስቃኝተዋል።

የአሜሪካው ሁቨር ግድብ እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1930ዎቹ በአሜሪካ ተከስቶ የነበረው የኢኮኖሚ ድቀት ወቅት በአሜሪካ የተገነባ ግድብ ነው። ግድቡን ለመገንባት በ10 ሺሕ የሚቆጠሩ አሜሪካኖች የተሳተፉ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰውተዋል። ግድቡ ለኔቫዳ፣ ለአሪዞንያ እና ካሊፎርኒያ ለመሳሰሉ የምእራብ ግዛቶች ዋነኛ የኃይል ምንጭ ሲሆን፣ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎች መናኽሪያ በመሆን ለአሜሪካ ብልፅግናም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሥያሜውን ያገኘውም ሐርፐርት ሁቨር ከተባሉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነው።

ነፍሳቸውን ይማርና ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ለዋሽንግተን ፖስት በአንድ ወቅት ሲናገሩ፤ እንደ ሁቨር ግድብ ሁሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ኢትየጵያን ወደ ሥልጣኔ ማማ በመመለስ ታሪክ ይጻፍለታል ብለዋል። ኢንጅነር ስመኝ በወቅቱ እንዳሉት ሁቨር ግድብ ለአሜሪካ ስኬት አሰተዋጽኦ ይኖረዋል።

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ግድቡ ሁሉንም በፍትሐዊነት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ብትገልፅም፣ ግብፅ  በተደጋጋሚ እና በተከታታይ እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ መግለጫዎችን ስትሰጥ እና ድርጊቶችን ስታከናውን እየታየችው ነው። ሰሞኑንም ይኸው የቀጠለ ይመስላል።

ግብፅ የህዳሴው ግድብ እንደሚጠቅማት እና ጉልህ ጉዳት /No significant harm/ እንደማያደርስ ብታውቅም፣ የኢትዮጵያን እድገት እና ልማት በአዎንታዊ መልኩ ልታየው እና ልትቀበለው አልቻለችም። የመጀመሪያው ምክንያት ለጥቁር ሕዝብ መኖሪያ ለአፍሪካ ካላት ዝቅተኛ አመለካከት ይነሳል። ኹለተኛ የኢትዮጵያ መልማት በአፍሪካ እና በዓለም ተቀባይነቷን እያሳደገ በመምጣት፣ በቀጣይ አባይን የመጠቀም አቅም ያድጋል፤ ለሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ዐይን ይገልጣል። ይህም ግብፅን ይጎዳል የሚል ከንቱ ስጋት አለባት።

በሦስተኛ ደረጃ የግብፅ አብዮት መሠረታዊ እና መዋቅራዊ ችግሮች አሁንም አልተፈቱም። ችግሮቹ ተፈተዉ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እስኪሰፍን ገዢዎቹ አባይን የትኩረት ማስቀየሻ ያደርጉታል።

አንዳንድ ግብጻውያን የቅኝ ገዢ ውሎችን በመጥቀስ ናይልን የመጠቀም ዓለም ዐቀፍ መብት የእነሱ ብቻ እንደሆነ ይገልጻሉ። የአባይ ወንዝን በተመለከተ የመጀመሪያው ስምምነት የተካሄደው እ.ኤ.አ. በ1891 ነበር። በዚህ ስምምነት መሠረት ጣሊያን በአታባራ ወንዝ ላይ ግድብ ላለመሥራት ከእንግሊዝ ጋር እንደተስማማች የሚያነሱ አሉ። ፕሮፌሰር አሊ አብደላ አል ግን በስምምነቱ በግል ቋንቋ ያልተቀመጠ ነው ይላሉ። ፕሮፌሰር አሊ በሱዳን የኡምዱርማን ዩኒቨርሲቲ መምህር ናቸው።

ኹለተኛው ስምምነት እ.ኤ.አ. በ1902 እንግሊዝ፣ ጣሊያን እና አፄ ምኒልክ የአባይን ወንዝ ላለማስቀረት እንደተስማሙ የሚያስቀምጡ አሉ። ይህን ስምምነት በወቅቱ እንግሊዝ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ስላላጸደቁት ተቀባይነት የለውም የሚሉ አሉ። የእንግሊዝኛው እና የአማርኛው ፍቺዎች የተለያዩ በመሆናቸው ኢትዮጵያ እንዳላጸደቀችውም ፕሮፌሰር አሊ ይናገራሉ።

የ1929 እና የ1959 ስምምነት ለታሪካዊ መብት ዋነኛዋቹ መነሻዎች ናቸው። በእነዚህ ስምምነቶች መሠረት፡-

ግብፅ እና ሱዳን ጠብታ ውሃ ሳያስቀሩ ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ተከፋፍለዉታል፣

ሌላ ይገባኛል የሚል አገር ከመጣ ከኹለት አገራት እኩል እንዲቀነስ ተስማምተዋል፣

ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ የሚሠራ ግድብ ድምፅ በድምፅ የመሻር መብት አጎናጽፏታል፣

በሌሎች አገሮች በወንዙ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ለመከታተል የሚያስችል የቴክኒክ ቡድን ለማቋቋም ተስማምተዋል። (ከላይ የተጠቀሱትን ሃሳቦች ከዓለም ዐቀፍ ሕግ እና ተቀባይነት ካለው መርህ አንፃር ማየቱ ተገቢ ነው።)

በመጀመሪያ ደረጃ ግብፅ እና ሱዳን በ1929/በ1959 እኩል ተጠቃሚ ናቸው ብሎ መውሰድ ተገቢ አይደለም። በ1929 ስምምነት ግብፅ ሱዳንን አላማከረችም። ምክንያቱም በወቅቱ ሱዳን የግብፅ አንድ የግዛት አካል ተደርጋ ስለምትወሰድ ነበር። በ1959 ስምምነት ደግሞ የሱዳን ውሃ ባለሙያዎች አስተያየት ግምት ውስጥ ሳይገባ የሱዳን ባለሥልጣናት ግብፅን በመፍራት እንደፈረሙት ፕሮፌሰር አሊ ታሪክን በመጥቀስ ይከራከራሉ።

ከሁሉም በላይ በስምምነቱ የታችኛው የተፋሰስ አገራት በተለይም 86 በመቶ የውሃ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ሐሳቧ አልተካተተም። የስምምነቱም አካል አይደለችም። አንድ ስምምነት ተቀባይነት ያለው ዓለም ዐቀፍ ሕግ ሊሆን የሚችለው ስምምነቱን በፈረሙት እና ባጸደቁት አካላት መካከል ብቻ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የተፋሰስ አገራት በኹለቱ ስምምነቶች የመገዛት ግዴታ የለባቸውም።

ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ተቀባይነት ያሉት የእኩል ተጠቃሚነት እና ከፍተኛ ጉዳት ያለመድረስ መርሆዎች ናቸው። በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት የ1929 እና የ1959 ስምምነት የተፋሰሱ ዘጠኙን አገራት ያገላል። በመሆኑም፣ ውሎቹ ከላይ የተጠቀሱትን መርሆዎች የሚጥሱ በመሆናቸው በዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰብ እና ጉዳይም ወደ ገላጋይ ቢሄድ ተቀባይነት አይኖረውም። ስምምነቶቹ በይዞታቸው የእኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሳይሆን የሚያገሉ (Discriminatory) በመሆናቸው፤ በዓለም ዐቀፍ ሕግ ተቀባይነት የላቸውም። ለነገሩ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመላክም ኢትዮጵያ መስማማት ይኖርባታል።

እ.ኤ.አ. ሜይ 21/1997 የተመድ ለመጓጓዣነት የማይውሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ዙሪያ ባወጣው ስምምነት (ኮንቬንሽን) መሠረት፣ ሁሉም የተፋሰስ አገራት ወንዙን በሚጠቀሙበት ጊዜ የእኩል /ፍትሐዊ/ አጠቃቀም መርህን በዋነኝነት መከተል እንዳለባቸው ያስቀምጣል። እኩል የመጠቀም መብት መርህን በተመለከተ አንዳንዶቹ በሁሉም ሀገራት እኩል ማከፋፈል ነው በማለት ይተረጉሙታል። ይህ ግን በአብዛኛው ተቀባይነት የለውም። በኮንቬንሽኑ አንቀጽ 6 መሠረት የእኩል/ፍትሐዊ/ሚዛናዊ መርህ የሚከተሉትን መስፈርቶች የሚይዝ ነው፤

የጂኦግራፊ፣ የሃይድሮ ግራፊክ፣ የሃይድሮሎጂክ፣ የኢኮሎጂካል እና ሌሎች የተፈጥሮ ሁኔታ መመዘኛዎች፣

በተፋሰሱ በሚገኙ አገራት ያለው የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ፍላጎቶች፣

አንድ አገር ውሃውን ሲጠቀም በሌላኛው ተፋሰስ አገር ላይ ያለው ተፅዕኖ፣

በጥቅም ላይ ያለ እና እምቅ የውሃ አቅም፣

ውሃውን ለመጠበቅ፣ ለመከላከል፣ ለመበልፀግ ያለው ጠቀሜታ እና ለዚህ የሚውለው ወጪ፣

አማራጭ የውሃ ምንጮች

በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት አገራት መከፋፈል እንዳለባቸው ኮንቬንሽኑ ያስቀምጣል። በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት ያልተከፋፈለ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ አጠቃቀም በድርጅቱ ተቀባይነት አይኖረውም። ለእነዚህ መመዘኛዎች ቀረቤታ ያላቸው የቅኝ ግዛት ውሎች ሳይሆኑ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት /የኢንቴቤ ስምምነት/ ነው። ስለዚህ ለግብፅ እና ሱዳን በዘላቂነት የሚያዋጣቸው በትብብር ማዕቀፍ ስምምነት መሠረት መፈረም ነው።

በ1997ቱ የተመድ ኮንቬንሽን መሠረት ከእኩል ተጠቃሚነት በተጨማሪ ጉዳት ያለማድረስ መርህ ሌላኛው መመዘኛ ነው። የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ በግብፅ ላይ ትርጉም ያለው ጉዳት እንደማይደርስ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ አስቀምጣለች። እንዳውም የግድቡ ሥራ ሲጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፍትሐዊ አጠቃቀም የሰፈነ ቢሆን ኖሮ የግድቡን ወጪ ሥራን 20 በመቶ ሱዳን፣ 30 በመቶ ግብፅ ሊሸፈኑ ይገባ ነበር።

ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ በኢትዮጵያ የሚሠራ ግድብ ትነትን በመቀነስ ተጨማሪ ውሃ ያስገኛል። በኢትዮጵያ የሚሠራ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ የታችኛው የተፋሰስ አገራት ከጎርፍ እና በደለል ከመሞላት ይከላከላል። የተመጠነ የውሃ ፍሰት ዓመቱን ሙሉ እንዲኖር ያስችላል። በተመጣጣኝ ዋጋ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ያስችላል ይላሉ፤ አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ምክራቸውን ሲለግሱ። ዘላቂው ስትራቴጂ የአባይን ወንዝ በዘላቂነት ለመጠቀም ውሃው የሚከማችበትን እና አስዋን ግድብ ከፍተኛ ትነት ካለበት ግብፅ እና ሱዳን ይልቅ ወደ ቀዝቃዛው የኢትዮጵያ ክፍል ማሸጋገር ነው ይላሉ።

አንዳንድ ግብፃዊያን ሌላኛው የሚያቀርቡት  የመከራከሪያ ነጥብ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሊትር ውሃ የመጠቀም ታሪካዊ መብት አለን፤ ይህም ተለምዷዊ ዓለም ዐቀፍ ሕግ ሆኗል የሚል ነው። እንደ ልምድ ተቀባይነት ያለው ተለምዷዊ ዓለም ዐቀፍ ሕግ ተቀባይነት የሚኖረው ተቃዋሚ ወገን ሳይኖር ሲቀር ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም መብት እንዳላት ለግብጽ እና ለሌሎችም በየጊዜው ከማሳወቋም በላይ ቅኝ ገዢዎች እና ግብጽ ኢትዮጵያን በማግለል የተዋዋሉትን ስምምነቶች በተደጋጋሚ ለአገሪቱ እና ለዓለም ዐቀፍ ተቋማት፤ ለሊግ ኦፍ ኔሽን እና ለተመድ በጽሑፍ መግለጿ ይታወቃል። በተለይ አፄ ምኒልክ እና አፄ ኃይለሥላሴ ተቃውሟቸው በጽሑፍ ሰፍሮ ይገኛል።

ስለዚህ ታሪካዊ መብት የሚባለውን ኢትዮጵያ ተቃውሞዋን የገለጸችበት ስለሆነ፣ በዓለም ዐቀፍ ሕግ ተቀባይነት አይኖረውም። በተጨማሪም በ1978 በቬና በጸደቀው ኮንቬንሽን መሠረት አገራት ከቅኝ ግዛት ሲላቀቁ መውረስ ያለባቸው ድንበር እንጂ ሌሎች መብቶችን እና ግዴታዎችን እንዳልሆነ ያስቀምጣል። የቅኝ ገዢዎች ውል /ስምምነት/ በየጊዜው ካለው የሰው ልጅ ፍላጎቶች ጋር የሚያያዙ እና የሚሻሻሉ መሆን ይኖርባቸዋል። ውል ሳይሆን መቅደም ያለበት የሰው ልጅ ፍላጎት ነው።

በ1920ዎቹ እና በ1950ዎቹ ያሉ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ጋር አንድ እና ያው ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህ ውሳኔዎች በየጊዜው ከሰው ልጅ ፍላጎት ጋር እየተሻሻሉ መምጣት ይገባቸዋል። በቅኝ ገዢዎች አማካኝነት የተገቡትን ስምምነቶች የማክበር ግዴታ የለባቸውም። ከግዴታ የነጹ አገራት መሆን እንዳለባቸው ኮንቬንሽኑ ይደነግጋል።

ሲጠቃለል፣ የአባይን ወንዝ በተመለከተ ለኤሌክትሪክም ሆነ ለሌላ አገልግሎት የሚውል ዓለም ዐቀፍ ሕግ ኢትዮጵያን የሚደግፍ እንጂ የሚከላከል አይደለም። የኢትዮጵያም መንግሥት ግድቡን ማኅበራዊ ካፒታላችንን ለመገንባት የበለጠ ቢጠቀምበት ይመከራል።

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ስንታየሁ ግርማን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይችላሉ፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here